ስፖርት - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት
በሻምፒዮንስ ሊጉ ማንችስተር ሲቲ በቦዶ ግሊምት ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናገደ
Jan 20, 2026 53
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መርሐ ግብር የኖርዌዩ ቦዶ ግሊምት ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 1 አሸንፏል። ማምሻውን በአስፕማይራ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ካስፐር ዋርትስ ሆግ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ጄንስ ፒተር ሃውግ ቀሪዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ራያን ቸርኪ ለሲቲ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። የማንችስተር ሲቲው አማካይ ሮድሪ በ62ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በጨዋታው ማንችስተር ሲቲ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም ቦዶ ግሊምት ግልጽ የግብ እድሎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር። በውድድሩ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ቦዶ ግሊምት በስድስት ነጥብ ደረጃውን ከ32ኛ ወደ 26ኛ ከፍ አድርጓል። በአንጻሩ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ማንችስተር ሲቲ በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ሲቲ በሁሉም ውድድሮች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በተያያዘም ማምሻውን በተደረገ ሌላኛው መርሐ-ግብር ክለብ ብሩዥን ካይራት አልማቲን 4 ለ 1 ረቷል። ምሽት አምስት ላይ በሳን ሲሮ ስታዲየም ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
መቀሌ 70 እንደርታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አገኘ
Jan 20, 2026 60
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጊት ጋትኩት እና ፍፁም አለሙ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሀብታሙ ሸዋለም ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘገበው መቀሌ 70 እንደርታ በ16 ነጥብ ደረጃውን ከ18ኛ ወደ 16ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። በአንጻሩ በሊጉ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ዛሬ ቀን ላይ በተደረገ የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ዛሬ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በበዓሉ ምክንያት ያልተካሄደ ሲሆን በቀጣይ በሚገለጽ ጊዜ በተስተካካይ መርሃ ግብር እንደሚደረግ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋሩ
Jan 20, 2026 59
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታው የተካሄደው በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ነው። ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ14 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ባህር ዳር ከተማ በ21 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። በተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ሴኔጋል በፊፋ የዓለም ሀገራት ወርሃዊ ደረጃ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ አለች
Jan 20, 2026 71
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ):- የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ወርሃዊ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃን ይፋ አድርጓል። በዚህም የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድሏ ሴኔጋል ሰባት ደረጃዎችን በማሻሻል ከነበረችበት 19ኛ ደረጃ ወደ 12ኛ ከፍ ብላለች። በፍጻሜው ሽንፈት ያስተናገደችው ሞሮኮ ደግሞ ከ11ኛ ወደ 8ኛ ከፍ ብላለች። በውድድሩ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ናይጄሪያ 12 ደረጃዎችን በማሻሻል 26ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አልጄሪያ 28ኛ፣ ግብጽ 31ኛ፣ ኮትዲቯር 37ኛ፣ ካሜሮን 45ኛ፣ ቱኒዚያ 47ኛ፣ ማሊ 54ኛ፣ ደቡብ አፍሪካ 60ኛ እና ቡርኪና ፋሶ 62ኛ ደረጃን ይዘዋል። ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር በነበረችበት 147ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ስፔን፣ አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ብራዚል ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ፖርቹጋል እና ኔዘርላንድስ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ሳን ማሪኖ የመጨረሻውን 210ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የቡድን ጥንካሬ፣ የሚደረገው ጨዋታ ያለው ወሳኝነት፣ የጨዋታ ውጤትና ከጨዋታ በፊት የሚጠበቅ ውጤት ፊፋ የሀገራትን የእግር ኳስ ደረጃ የሚለከባቸው መመዘኛዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
Jan 20, 2026 73
አዲስ አበባ፤ ጥር 12 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ። ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ያሸነፈው ጨዋታ ብዛት ሁለት ብቻ ነው። ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ ሰባት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ13 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። በሊጉ ካከናወናቸው 15 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ጎሎችን አስተናግዷል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ጨዋታው መቀሌ 70 እንደርታ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው። ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ወላይታ ድቻ በ13 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ20 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ባህር ዳር ከተማ በ15ኛ ሳምንት ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ሁለቱም ቡድኖች ወደ ማሸነፍ መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በበዓሉ ምክንያት እንደማይካሄድ እና በቀጣይ በሚገለጽ ጊዜ በተስተካካይ መርሃ ግብር እንደሚደረግ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል። የ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። ሲዳማ ቡና ሊጉን በ30 ነጥብ እየመራ ነው። የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ አቤል ያለው በስምንት ግቦች እየመራ ነው።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Jan 20, 2026 143
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሰባተኛ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይካሄዳሉ። ምሽት 5 ሰዓት ላይ በሳን ሲሮ ስታዲየም ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል። ኢንተር ሚላን እስከ አሁን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች 12 ነጥብ በማግኘት 6ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው አርሰናል በ18 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፈ ብቸኛው ክለብ ነው። ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ4ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 3 ጨዋታዎች አርሰናል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ ኢንተር ሚላን ድል ቀንቶታል። ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ በአውሮፓ መድረክ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024/25 ነበር። በወቅቱ ኢንተር ሚላን ሃካን ቻላንኦግሉ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል። ኢንተር ሚላን የሴሪ አ እና አርሰናል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪ ናቸው። የጣልያኑ ክለብ 3 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል። የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ሻምፒዮንስ ሊግን አሸንፎ አያውቅም። ሁለቱ ክለቦች በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሌሎች መርሐ-ግብሮች ስፖርቲንግ ሊዝበን ከወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ፣ ሪያል ማድሪድ ከሞናኮ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ኮፐንሃገን ከናፖሊ፣ ቪያሪያል ከአያክስ እና ኦሎምፒያኮስ ከባየር ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ቦዶ ግሊምት ከማንችስተር ሲቲ እና ካይራት አልማቲ ከክለብ ብሩዥ ይጫወታሉ።
ሳዲዮ ማኔ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ
Jan 18, 2026 158
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የሴኔጋሉ ሳዲዮ ማኔ የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኗል። በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል። ሴኔጋል አዘጋጇ ሞሮኮን 1 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች። የሴኔጋሉ ኮከብ ሳዲዮ ማኔ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ አምስት ግቦች በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። የሞሮኮው ያሲን ቦኖ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል። የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አግኝቷል። በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ (ዶ/ር)፣ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የአዘጋጇ ሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፋውዚ ሌክጃ ተገኝተዋል። ሞሮኮ የቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ለኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ አስረከባለች። ሶስቱ ሀገራት በጣምራ 36ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን እ.አ.አ በ2027 ያዘጋጃሉ። በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 52 ጨዋታዎች 121 ግቦች የተቆጠረበት ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበት ሆኗል።
ሴኔጋል 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች
Jan 18, 2026 180
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ሴኔጋል ሞሮኮን 1 ለ 0 አሸንፋለች። ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ብራሂም ዲያዝ በጭማሪ ሰዓት ላይ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አልተቀመበትም። የፍጹም ቅጣት ምቱን ውሳኔ በመቃወም የሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳ ለቀው በመውጣታቸው ጨዋታው ተቋርጦ ነበር። የሴኔጋል ተጫዋቾች ተመልሰው ከገቡ በኋላ ጨዋታው የቀጠለ ሲሆን ዲያዝ በቄንጠኛ መንገድ (ፓኔካ) ፍጹም ቅጣት ምት ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ የሴኔጋል ኤድዋርድ ሜንዲ አድኖበታል። ጨዋታው ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል። ፓፕ ጌይ በ94ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ሴኔጋልን አሸናፊ አድርጋለች። ውጤቱን ተከትሎ ሴኔጋል ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫን አንስታለች። ሴኔጋል ከዋንጫው በተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያው እና የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አግኝታለች። ሽልማቱ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ትልቁ ነው። ሴኔጋል እ.አ.አ በ2019 በግብጽ የተዘጋጀውን 32ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳቷ የሚታወስ ነው። አዘጋጇ ሞሮኮ ከ50 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ የማንሳት ህልም አልተሳካም። ሞሮኮ ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ1976 በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው። ሞሮኮ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ እና የአራት ሚሊዮን ሽልማት አግኝታለች። የአትላስ አንበሶች በውድድር ጨዋታዎች ከሁለት ዓመት በኋላ ተሸንፋለች። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የ32 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል። ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ደማቅ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ተደርጓል። ከታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ተጠናቋል።
በፕሪሚየር ሊጉ ኤቨርተን አስቶንቪላን አሸነፈ
Jan 18, 2026 93
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኤቨርተን አስቶንቪላን 1 ለ 0 አሸንፏል። ማምሻውን በቪላ ፓርክ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቲዬርኖ ባሪ በ59ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግቡን አስቆጥሯል። በጨዋታው ላይ አስቶንቪላ ብልጫ ቢወስድም ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ኤቨርተን የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴው አሸናፊ አድርጎታል። በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ኤቨርተን በ32 ነጥብ ከ12ኛ ደረጃ ወደ 10ኛ ከፍ ብሏል። ኤቨርተን ከ10 ዓመታት በኋላ አስቶንቪላን በሊጉ ማሸነፍ ችሏል። በአንጻሩ በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አስቶንቪላ በ43 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። አስቶንቪላ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ የማድረግ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ዛሬ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ዎልቭስ ከኒውካስትል ዩናይትድ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር በብራይተን እና ቦርንማውዝ መካከል ነገ ይደረጋል።
አስቶንቪላ ከኤቨርተን ጋር ይጫወታል
Jan 18, 2026 116
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ አስቶንቪላ ከኤቨርተን በቪላ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። አስቶንቪላ በ43 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ኤቨርተን በ29 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ81ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 80 ጨዋታዎች አስቶንቪላ 40 ጊዜ ድል ሲቀናው ኤቨርተን በ22ቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 18 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በ80 ጨዋታዎች አስቶንቪላ 102 ግቦችን ሲያስቆጥር ኤቨርተን 79 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው ግንኙነት አስቶንቪላ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ኤቨርተን ለመጨረሻ ጊዜ አስቶንቪላን በሊጉ ያሸነፈው እ.አ.አ ማርች 1 2016 ሲሆን በወቅቱ የ3 ለ 1 ድል ተቀዳጅቷል። ቡድኖቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። አስቶንቪላ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ያደርጋል። ኤቨርተን ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ቶኒ ሃሪንግተን ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል። በሌላኛው መርሃ ግብር ዎልቭስ ከኒውካስትል ዩናይትድ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአፍሪካ ዋንጫን ማን ያነሳል? ሴኔጋል ወይስ አዘጋጇ ሞሮኮ?
Jan 18, 2026 553
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ መርሃ ግብር ሴኔጋል እና ሞሮኮ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። አሸናፊው ሀገር ከዋንጫው በተጨማሪ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ ካዝናው ያስገባል። የብሄራዊ ቡድኖቹ ጨዋታ ምሽት አራት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይካሄዳል። ጨዋታው የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል። በግማሽ ፍጻሜው ሴኔጋል ግብጽን፣ ሞሮኮ ናይጄሪያን በማሸነፍ ለዋንጫው ፍልሚያ ቀርበዋል። የፍጻሜ ተፋላሚ ሀገራቱ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ሽንፈት አላስተናገዱም። ሴኔጋል በውድድሩ ላይ እስከ አሁን ስድስት ጨዋታዎችን አድርጋ አምስቱን ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይታለች። በጨዋታዎቹ ላይ 12 ግቦችን ስታስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዳለች። አዘጋጇ ሞሮኮ ካደረገቻቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል አራቱን ስታሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥታለች። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ የተቆጠረባት አንድ ጎል ብቻ ነው። ሞሮኮ በውድድሩ ላይ ዝቅተኛ የግብ መጠን የተቆጠረባት ሀገር ናት። ሴኔጋል እና ሞሮኮ በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 33 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሞሮኮ 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ሴኔጋል በሰባቱ ስታሸንፍ በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ሞሮኮ በጨዋታዎቹ ላይ 41 ግቦችን ስታስቆጥር፣ ሴኔጋል 17 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች። ሁለቱ ሀገራት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ ኦገስት 2025 በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ጣምራ አዘጋጅነት በተካሄደው ስምንተኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን)ላይ ነበር። በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ሞሮኮ ሴኔጋልን በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች። ሞሮኮ በፍጻሜው ማዳጋስካርን በመርታት ዋንጫውን አንስታለች። ሀገራቱን በዘንድሮው ውድድር ከሚያመሳስላቸው ጉዳዮች አንዱ ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ ጥንካሬያቸውን እና አቅማቸውን እያሳደጉ መምጣታቸው ነው። ሴኔጋል ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት፣ ማጥቃት እና መከላከል ላይ ተመጣጣኝ ሚዛን በመስራት የሚጫወተው የአማካይ ክፍል፣ የማጥቃት አቅም እና በድንቅ ብቃት ላይ የሚገኘው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ የጥንካሬዎቿ ማሳያ ናቸው። በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ጥገኛ መሆን እና ለፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተጋላጭ መሆን እንደ ድክመት ይነሳል። አዘጋጇ ሞሮኮ ቅርጹን የጠበቀ እና በቀላሉ ሰብሮ መግባት የማይቻል የተከላካይ ክፍል ገንብታለች። የቀኝ እና ግራ መስመር ተመላላሽ ተጫዋቾች የማጥቃት ብቃት፣ በክህሎት የተሞላው የአማካይ ክፍል እና ከተለያዩ አማራጮች ግብ ማስቆጠር መቻሏ እንደ ጥንካሬ የሚነሳ ነው። በጣም ጥንቃቄ የታከለበት የሞሮኮ የኳስ ቅብብል በጣም ተጭነው እና ፍሰትን ለማበላሸት በሚጫወቱ የተጋጣሚ ቡድኖች ለአደጋ የተጋለጠ ሲሆን ይህም የማጥቃት አቅምን ሲቀንስ ታይቷል። ሞሮኮ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በጥልቀት የሚጫወቱ ቡድኖችን አስከፍታ ለመጫወት ስትቸገር ለመመልከት ተችሏል። በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው ሳዲዮ ማኔ የሴኔጋል ቁልፍ ተጫዋች ነው። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የውድድሩ ክስተት የሆነው የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል። ጨዋታው በታክቲክ የታጠረ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ሴኔጋል እ.አ.አ በ2022 በካሜሮን አስተናጋጅነት የተካሄደውን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳች ሲሆን ውድድሩን ለሁለተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ትጫወታለች። ተጋጣሚዋ ሞሮኮ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1976 ባዘጋጀችው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብቸኛ አህጉራዊ ድሏን ማሳካት ችላለች። ከ50 ዓመታት ራሷ ያዘጋጀችውን ዋንጫ ለመውሰድ ትፋለማለች። አሸናፊው ሀገር ከዋንጫው በተጨማሪ የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል። ይህም ከ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የ43 በመቶ ብልጫ እንዳለው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል። ሁለተኛ የሚወጣው ሀገር የአራት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል። አጠቃላይ ለተሳታፊ ሀገራት የ32 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይበረከታል። ከታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጠናቀቃል።
የሊጉ መሪ አርሰናል እና ኖቲንግሃም ፎረስት አቻ ተለያዩ
Jan 17, 2026 110
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኖቲንግሃም ፎረስት እና አርሰናል ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ማምሻውን በሲቲ ግራውንድ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ብልጫ ወስዶ የተጫወተው አርሰናል ያገኛቸውን የግብ እድሎች አለመጠቀሙ ሶስት ነጥብ እንዳያገኝ አድርጎታል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጋብርኤል ማርቲኔሊ የሳተው ግልጽ የግብ እድል ተጠቃሽ ነው። ተጋጣሚው ኖቲንግሃም ፎረስት ወደ ኋላ አፈግፍጎ የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት ስልት ይዞ በመግባት ግብ ሳይቆጠርበት ወጥቷል። ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ አርሰናል ነጥቡን ወደ 50 ከፍ አድርጓል። ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል። አርሰናል ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈ ሲሆን ግብም ማስቆጠር አልቻለም። ኖቲንግሃም ፎረስት በሊጉ በ22 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ናይጄሪያ ግብጽን በማሸነፍ በአፍሪካ ዋንጫው ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች
Jan 17, 2026 84
አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ ናይጄሪያ ግብጽን በመለያ ምት አሸንፋለች። ማምሻውን በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል። ጨዋታው ቀጥታ ወደ መለያ ምት አምርቷል።በዚህም ናይጄሪያ 4 ለ 2 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። የነሐስ ሜዳሊያም አግኝታለች። ግብጽ አራተኛ በመሆን ጨርሳለች። በጨዋታው ናይጄሪያ የግብ እድል በመፍጠር፣ ግብጽ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበሩ። ናይጄሪያ ሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አንስታለች። ግብጽ ውድድሩን ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ስኬታማዋ ሀገር ናት።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ተለያየ
Jan 17, 2026 85
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሐ- ግብር ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ መስፍን ታፈሰ ለሲዳማ ቡና ግቦቹን አስቆጥሯል። አቡበከር ሳኒ እና ሙጂብ ቃሲም ለአዳማ ከተማ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 30 ከፍ አድርጓል። ከተከታዩ ነገሌ አርሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የማስፋት እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አዳማ ከተማ በ23 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዟል። ጨዋታውን ተከትሎ የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል። የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄዱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
በፕሪሚየር ሊጉ ቼልሲ ድል ሲቀናው ሊቨርፑል ነጥብ ጥሏል
Jan 17, 2026 78
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማምሻውን አምስት ጨዋታዎች ተደርገዋል። በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቼልሲ ብሬንትፎርድን 2 ለ 0 አሸንፏል። ጆአኦ ፔድሮ በጨዋታ እና ኮል ፓልመር በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ውጤቱን ተከትሎ ቼልሲ በ34 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ብሬንትፎርድ በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሊቨርፑል ከበርንሌይ አንድ አቻ ተለያይቷል። በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፍሎሪያን ዊትዝ ለሊቨርፑል፣ ማርከስ ኤድዋርድስ ለበርንሌይ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሊቨርፑል በጨዋታው ላይ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አማካዩ ዶምኒክ ስቦዝላይ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሊቨርፑል በ36 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ሲይዝ በርንሌይ በ14 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። በሌሎች መርሃ ግብሮች ሰንደርላንድ ክሪስታል ፓላስን ፣ ዌስትሃም ዩናይትድ ቶተንሃም ሆትስፐርስን በተመሳሳይ 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ሊድስ ዩናይትድ ፉልሃምን 1 ለ 0 ረቷል። በአሁኑ ሰዓት የሊጉ መሪ አርሰናል ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል።
በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው
Jan 17, 2026 123
ዲላ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታዳጊዎች ምዘናና የባህል ስፖርት ውድድር ፌስቲቫል ዛሬ በዲላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ወደ ስፖርት መምጣት እንዲችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ከነዚህ ተግባራት መካከል ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ስራ ዋናው መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ከከተሞች ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ ልማት እየተከናወነ መሆኑን አንስተው ይህም ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ የተጀመረው ታዳጊዎች ምዘናና የባህል ስፖርት ውድድር ተሳታፊዎችም ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ውድድሩ የታዳጊ ወጣቶችን አቅም በማጎልበት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ዓላማ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ ናቸው። ፌስቲቫሉ ከውድድርና ምዘና ባለፈ የክልሉ ህብረ ብሔራዊነትና ቱባ ባህሎች በአደባባይ የሚንጸባረቅበትና አንድነት የሚጎላበት መድረክ ነው ብለዋል። በውድድሩ ላይ በክልሉ ከሚገኙ 12 የዞንና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ታዳጊ ስፖርተኞች የሚሳተፉ ሲሆን በተለይ በእግር ኳስ ረገድ ክልሉን ወክለው በሃገር ደረጃ የሚሳተፉ 33 ታዳጊዎች ምልመላ እንደሚከናወን አንስተዋል። ውድድሩ ከ11 በላይ ባህላዊና ዘመናዊ ስፖርቶችን በሁለቱም ጾታዎች ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው ከ1 ሺህ 600 በላይ የስፖርት ልዑካን እንደሚሳተፉም ተናግረዋል። የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፌስቲቨሉ በከተማው መካሄዱ የስፖርት እንቅስቃሴን ከማነቃቃት ባለፈ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል። በተለይ በከተማው የሚገኙ ታዳጊ ስፖርተኞች በውድድሩ ከመሳተፍ ባለፈ ልምድ በመቅሰም ተወዳዳሪነታቸውን የሚያጠናክሩበት መልካም አጋጠሚ መሆኑን አንስተዋል። በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሁሉም መዋቅሮች የስፖርት ልዑካንና የስፖርቱ ቤተሰብ ተሳተፊ ሆነዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመለሰ
Jan 17, 2026 68
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አምበሉ አቤል ያለው በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ሀብታሙ ጉልላት እና ፍጹም ጥላሁን ደግሞ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። የድሬዳዋ ከተማው አማካይ ሄኖክ ሀሰን በ22ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህም በጨዋታው ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። ከስድስት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ በ22 ነጥብ ደረጃውን ከ10ኛ ወደ 7ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱም ስድስተኛ ድሉን አሳክቷል። በአንጻሩ በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ በ18 ነጥብ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ዝቅ ብሏል።
በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲን አሸነፈ
Jan 17, 2026 112
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲን 2 ለ 0 አሸንፏል። በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብራያን ምቡዌሞ በ65ኛውና ፓትሪክ ዶርጉ በ76ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ምቡዌሞ በዩናይትድ ማልያ ሰባተኛ የሊግ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል። በጨዋታው ላይ ማንችስተር ዩናይትድ ብልጫ ወስዶ የተጫወተ ሲሆን፤ ተጨማሪ ግቦችን የማስቆጠር እድሎችን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የዓለም አይኖች ያረፉበት ተጠባቂው የማንችስተር ደርቢ ማንችስተር ሲቲ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርጓል። ይህን ተከትሎም 198ኛው የማንችስተር ደርቢ በማንችስተር ዩናይትድ አሸናፊነት ተጠናቅቋል። በሊጉ 10ኛ ድሉን ያስመዘገበው ዩናይትድ በ35 ነጥብ ደረጃውን ከሰባተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ማንችስተር ሲቲ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድል አምክኗል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አላሻነፈም። የሊጉ መሪ አርሰናል ዛሬ ማምሻውን ኖቲንግሃም ፎረስት ካሸነፈ ከሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ቡና እና ሐዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋሩ
Jan 17, 2026 67
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ሐዋሳ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ናይጄሪያዊው ዲቫይን ዋቹኩዋ በ38ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ኢትዮጵያ ቡና መሪ ሆኗል። ጌታነህ ከበደ በ93ኛው ደቂቃ ለሐዋሳ ከተማ የአቻነቷን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና በ19 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ሐዋሳ ከተማ በ25 ነጥብ ደረጃውን ከአምስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል።
ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው
Jan 17, 2026 162
አሶሳ፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ። በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት የሚካሄድ ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ፕሮጀክት የምዘና ውድድር በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል። በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሀጂ መንሱር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታዳጊዎች ላይ መሠረት ያደረገ የስፖርት ፖሊሲ በመተግበር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ ለስፖርቱ እድገትና ማንሰራራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በማንሳት በዛሬው እለት የተጀመረው ውድድርም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል። የውድድሩ ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመመልመል እና ታዳጊዎች የወሰዱትን ስልጠና ለመመዘን እንደሆነ ገልጸዋል። ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የአሶሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ፍቃዱ በየነ፤ በክልሉ እየተነቃቃ ላለው የስፖርት ዘርፍ ውጤታማነት የተለያዩ የስፖርት መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ፕሮጀክት የምዘና ውድድር በእግርኳስ፣ አትሌቲክስ፤ ቮሊ ቦል፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶን ጨምር በ9 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።