ቀጥታ፡
ስፖርት
ፈረንሳይ ከሞሮኮ፦ ማን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያልፋል?
Jul 9, 2026 706
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከእንድ ቀን እረፍት በኋላ ዛሬ በሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ይመለሳል። ምሽት አምስት ላይ ፈረንሳይ ከሞሮኮ በቦስተን ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ፈረንሳይ በ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ፓራጓይን በመርታት በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ለ10ኛ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች። ተጋጣሚዋ ሞሮኮ ከዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን ካናዳን 3 ለ 0 አሸንፋለች። ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው ታሪክ ሁለት ጊዜ ሩብ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል። ኳታር እ.አ.አ በ2022 ባዘጋጀችው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ፈረንሳይ 2 ለ 0 አሸንፋለች። ቴዎ ሄርናንዴዝ እና ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ሞሮኮ በጨዋታው ሽንፈት ቢገጥማትም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ ሀገር በመሆን ታሪክ ሰርታለች። ሁለቱ ሀገራት በአጠቃላይ በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፈረንሳይ አራት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ሞሮኮ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሞሮኮ በታሪኳ ፈረንሳይን ማሸነፍ የቻለችው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን እሱም እ.ኤ.አ. በ1998 በንጉሥ ሀሰን ሁለተኛ ዋንጫ ላይ ሁለት እኩል ተለያይተው በፍጹም ቅጣት ምት 6 ለ 5 ያሸነፈችበት ጨዋታ ነበር። በነዚህ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ፈረንሳይ 14 ጎሎችን ስታስቆጥር፣ ሞሮኮ 7 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች። የዓለም ዋንጫውን ታነሳለች ተብላ ሰፊ ግምት ያገኘችው ፈረንሳይ የማጥቃት ኃይሏ ለተጋጣሚዎቿ የራስ ምታት ሆኗል። የ27 ዓመቱ ኪሊያን እምባፔ በዘንድሮው ውድድር 7 ግቦችን በማስቆጠር እና ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ተመሳሳይ የግብ መጠን ያለውን አርጀንቲናዊውን ሊዮኔል ሜሲ በመብለጥ የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል። ምባፔ በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ 19 ግቦችን ከመረብ ላይ ያሳረፈ ሲሆን ከምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ሜሲ (20 ጎሎች) በአንድ ግብ ዝቅ ብሎ ይገኛል። ማይክል ኦሊሴ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። በሞሮኮ በኩል ሶስት ግቦችን በዓለም ዋንጫው ያስቆጠረው የ25 ዓመቱ አጥቂ ኢስማኤል ሳይባሪ ከካናዳ ጋር በነበረው ጨዋታ ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። የሳይባሪን ቦታ ሶፊያን ራሂሚ በዛሬው ጨዋታ እንደሚሸፍን ይጠበቃል። በዓለም ዋንጫው በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት አዜዲን ኡናሂ እና ሶፊያን ራሂሚ የማጥቃት እንቅስቃሴውን በዋነኛነት ይመሩታል። ምርጥ ጓደኛማቾች እየተባሉ የሚጠሩት አሽራፍ ሀኪሚና ኪሊያን እምባፔ በጨዋታው ላይ የሚኖራቸው ፉክክር ተጠባቂ ሆኗል። ፈረንሳንይ ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ብትወስድም ሞሮኮ ጠንካራ ተፋላሚነቷን ታሳያለች ተብሎ ይጠበቃል። የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከስፔን እና ቤልጂየም አሸናፊ ጋር ይገናኛል።
የኢትዮጵያ ዋንጫን ማን ያነሳል?  ሲዳማ ቡና ወይስ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ?
Jul 9, 2026 523
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መካከል ዛሬ ይደረጋል። ጨዋታው ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። በግማሽ ፍጻሜው ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ መድንን፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መቀሌ 70 እንደርታን በተመሳሳይ በመለያ ምት አሸንፈዋል። ሲዳማ ቡና ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ደርሷል። ቡድኑ ባለፈው ዓመት ውድድሩን አሸንፎ የነበረ ቢሆንም ቅጣት የተጣለባቸውን ተጫዋቾችን በፍጻሜው ላይ በመጠቀሙ ምክንያት ዋንጫው ለወላይታ ድቻ መሰጠቱ የሚታወስ ነው። ሲዳማ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማል። ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ሲያልፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። በሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው መርሐ ግብር አቻ ተለያይተዋል። ቡድኖቹ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 4 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም። በወቅቱ በነበረው ጨዋታ አበባው አጂሶ፣ አስቻለው ሙሴ፣ ተመስገን መንገሻ እና የወልዋሎው ጌታሁን ባፋ በራሱ ላይ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። ሰመረ ሀፍታይ ለወልዋሎ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል። በ20ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ቡና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ይህን ተከትሎም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ መሰታፉን አረጋግጧል። ቡድኑ የውድድር ዓመቱን በሁለት ዋንጫ ለመደምደም ዛሬ ወደ ሜዳ ይገባል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በ46 ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። ሲዳማ ቡና በአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎውን በማረጋገጡ ምክንያት፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ደንብ መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን ተከትሎ የጨዋታውን ውጤት ሳይጠብቅ በቀጥታ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ መሳተፉን አረጋግጧል። ሁለቱም ቡድኖች ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ለማንሳት ይፈለማሉ። በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የ80 ዓመት ታሪክ ያለው አንጋፋ ውድድር ነው።
ስዊዘርላንድ ከ72 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ አለፈች
Jul 8, 2026 950
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ የመጨረሻ ማለፍ መርሐ ግብር ስዊዘርላንድ ኮሎምቢያን በመለያ ምት አሸንፋለች። ማምሻውን በቢሲ ፔሌስ ቫንኩቨር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ 30 ደቂቃ የተጨመረ ሲሆን ግብ ባለመቆጠሩ ምክንያት ወደ መለያ ምት አምርቷል። በዚህም ስዊዘርላንድ 4 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች። ስዊዘርላንድ ከ72 ዓመታት በኋላ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች። በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ ስምንት ውስጥ ገብታለች። በሩብ ፍጻሜው ከአርጀንቲና ጋር ትጫወታለች። የደቡብ አሜሪካዋ ኮሎምቢያ በዓለም ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ ለሩብ ፍጻሜ የማለፍ ህልሟ አልተሳካም። አጠቃላይ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሳቢ ያልነበረ እና የግብ እድሎች በበቂ ሁኔታ ያልተፈጠሩበት ነበር። ጨዋታውን ተከትሎ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ተጠናቋል። የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ከሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ። ፈረንሳይ ከሞሮኮ፣ ኖርዌይ ከብራዚል፣ ስፔን ከቤልጂየም እና አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ በሩብ ፍጻሜው የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት አርጀንቲና ግብጽን በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች
Jul 7, 2026 868
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ አርጀንቲና ግብጽን ከ2 ለ 0 ከመመራት ተነስታ 3 ለ 2 አሸንፋለች። ማምሻውን በአትላንታ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ያስር ኢብራሂም በ15ኛው እና ሙስጠፋ ዚኮ በ67ኛው ደቂቃ ለግብጽ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሙስጠፋ ዚኮ በ58ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ጎል በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ታይቶ ጥፋት በመሰራቱ ተሽሯል። ክርስቲያን ሮሜሮ በ79ኛው፣ ሊዮኔል ሜሲ በ83ኛው እና ኤንዞ ፈርናንዴዝ በ93ኛው ደቂቃ የአርጀንቲናን ግቦች አስቆጥረዋል። በጨዋታው የግብጹ ግብ ጠባቂ ሙስጠፋ ሾቤር ያለቀላቸው ግቦችን በማዳን ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። አርጀንቲና ከውድድሩ ከመሰናበት ጫፍ ደርሳ ውጤቱን በመቀልበስ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች። ግብጽ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍጻሜ የመግባት ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል። የ2 ለ 0 ውጤቷንም ማስጠበቅ አልቻለችም። ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ስምንት በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናክሯል። በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ ያገባቸውን ጎሎች ብዛት 21 በማድረስ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን አጠናክሯል። ሜሲ በዘጠኝ ተከታታይ የዓለም ዋንጫዎች ላይ ግብ ያስቆጠረ እና በውድድሩ ዘጠኝ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ የመጀመሪያ ተጫዋች ሆኗል። ለሀገሩም 126ኛውን ግብ ከመረብ ላይ ያሳረፈ ሲሆን በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 918 አድርሷል። የ39 ዓመቱ አርጀንቲናዊ በ21ኛው ደቂቃ ፍጹም ቅጣት ስቷል። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የሳታቸውን ፍጹም ቅጣት ምቶች ብዛት ሁለት ደርሰዋል። ሜሲ በአንድ ዓለም ዋንጫ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምት የሳተ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። በአጠቃላይ በተሳተፋባቸው ዓለም ዋንጫዎች ላይ አራት ፍጹም ቅጣት ምቶችን ወደ ግብ መቀየር አልቻለም። አርጀንቲና በሩብ ፍጻሜው ከኮሎምቢያ እና ስዊዘርላንድ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች። ኮሎምቢያ እና ስዊዘርላንድ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በቢሲ ፕሌስ ቫንኩቨር ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመድረስ የሚደረጉ ተጠባቂ ፍልሚያዎች፦ አርጀንቲና ከግብፅ፤ ስዊዘርላንድ ከኮሎምቢያ
Jul 7, 2026 723
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30 /2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል። ምሽት አንድ ሰዓት ላይ አርጀንቲና ከግብጽ በአትላንታ ስታዲየም ይጫወታሉ። አርጀንቲና በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ኬፕቨርዴን 3 ለ 2 አሸንፋለች። የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ከተጋጣሚዋ የበረታ ፉክክር ቢገጥማትም፣ ድል ቀንቷት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግራለች። አርጀንቲና በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኳ ለ10ኛ ጊዜ ወደ 16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር አልፋለች። ከዚህ በነበራት የዘጠኝ ጊዜ ተሳትፎ ሰባቱን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ስታልፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፋለች። ተጋጣሚዋ ግብጽ ከአውስትራሊያ ጋር አንድ አቻ በመለያየት በመለያ ምት የ4 ለ 2 ድል በማስመዝገብ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 16 ውስጥ ገብታለች። የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር በጥሎ ማለፍ ስታሸንፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። አርጀንቲና እና ግብጽ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው ተገናኝተው አያውቁም። እ.አ.አ በ2008 በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ አርጀንቲና 2 ለ 0 አሸንፋለች። ሰርጂዮ አጉዌሮ እና ኒኮላስ ቡርዲሶ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረው እና በ20 ጎሎች የውድድሩ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪ ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታው የሚጠበቅ ተጫዋች ነው። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረውና በ20 ጎሎች የውድድሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሊዮኔል ሜሲ፣ በጨዋታው ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ተጫዋች ነው። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ኢማም አሹር እና አምበሉ መሐመድ ሳላህ በግብጽ በኩል የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው። የጨዋታው አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከስዊዘርላንድ እና ኮሎምቢያ አሸናፊ ጋር ይገናኛል። ስዊዘርላንድ ከኮሎምቢያ በቢሲ ፕሌስ ቫንኩቨር ስታዲየም ምሽት አምስት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ስዊዘርላንድ አልጄሪያን 2 ለ 0 አሸንፋለች። ይህም ከ88 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበችው የጥሎ ማለፍ ድል ነው። ተጋጣሚዋ ኮሎምቢያ ጋናን 1 ለ 0 በመርታት 16 ውስጥ ገብታለች። የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ በጥሎ ማለፉ ትጫወታለች። ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል። አሜሪካ እ.አ.አ በ1994 ባዘጋጀችው 15ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ኮሎምቢያ 2 ለ 0 አሸንፋለች። ሄርናን ጋቪሪያ እና ሃሮልድ ሎዛኖ ግቦቹን በወቅቱ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ሀገራቱ ከ32 ዓመታት በኋላ በጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተገናኝተዋል። ቡድኖቹ በአጠቃላይ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ኮሎምቢያ በሁለቱ ድል ሲቀናት በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። የስዊዘርላንድ እና ኮሎምቢያ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ። ሞሮኮ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስፔን እና ቤልጂየም እስከ አሁን ሩብ ፍጻሜ የገቡ ሀገራት ናቸው።
ቤልጂየም አሜሪካን በመርታት ሩብ ፍጻሜ ገብታለች
Jul 7, 2026 596
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ቤልጂየም አሜሪካን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች። ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሲያትል ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቻርልስ ደ ኬቴላሬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሃንስ ቫንከን እና ሮሜሎ ሉካኩ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። ማሊክ ቲልማን የአሜሪካን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል። አጥቂው ሮሜሎ ሉካኩ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሶስት አድርሷል። በአጠቃላይ ደግሞ በውድድሩ ላይ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ጎሎች ወደ ስምንት ከፍ አድርጓል። ለቤልጂየም ብሔራዊ ቡድንም 93ኛ ግቡን አስቆጥሯል። በጨዋታው ቤልጂየም ከፍተኛ ብልጫ ወስዳለች። የተመለከተው ቀይ ካርድ በአነጋጋሪ ሁኔታ የተነሳለት የአሜሪካው አጥቂ ፍሎሪያን ባሎጉን በጨዋታው ላይ ተሰልፏል። ውጤቱን ተከትሎ ቤልጂየም ወደ ሩብ ፍጻሜ የገባች ሲሆን ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ከስፔን ጋር ትፋለማለች። ከዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ የውድድሩ ጉዟዋ 16 ውስጥ ተገቷል። አሜሪካ ከ24 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው ሩብ ፍጻሜ የመግባት ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል። ጣምራ አዘጋጅ የሆኑት አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በ16ቱ ዙር የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከውድድሩ ተሰናብተዋል።
ስፔን ፖርቹጋልን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ አለፈች
Jul 7, 2026 490
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ 16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ተጠባቂ ግብር ስፔን ፖርቹጋልን 1 ለ 0 ረትታለች። ማምሻውን በዳላስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ሚኬል ሜሪኖ በ91ኛው ደቂቃ ግቧን አስቆጥሯል። ፌራን ቶሬስ ኳሱን አመቻችቶ አቀብሏል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ስፔን የግብ እድሎችን በመፍጠር ተሽላ ተገኝታለች። የ"አይቤሪያ ደርቢ" በስፔን አሸናፊነት ተጠናቋል። ስፔን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ግብ ያልተቆጠረባት ብቸኛ ሀገር ናት። ውጤቱን ተከትሎ ስፔን ወደ ሩብ ፍጻሜው የገባች አምስተኛ ሀገር ሆናለች። በሩብ ፍጻሜው ከአሜሪካ እና ቤልጂየም አሸናፊ ጋር ትጫወታለች። ስፔን የአንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ናት። የክርስቲያኖ ሮናልዶዋ ፖርቹጋል የዓለም ዋንጫ ጉዞዋ 16 ውስጥ ተገቷል። የ41 ዓመቱ ሮናልዶ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን የማንሳት ህልሙ ሳይሳካ ቀርቷል። ተጫዋቹ ዘንድሮ የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ መሆኑን ከጨዋታው በፊት ገልጾ ነበር። ሁለቱ ሀገራት ዓለም ዋንጫን ያሸንፋሉ ተብለው ግምት የተሰጣቸው ናቸው። አሜሪካ ከቤልጂየም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በሲያትል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ፖርቹጋል ከስፔን : ተጠባቂው የጥሎ ማለፍ ፍልሚያ
Jul 6, 2026 746
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፡- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የሚገቡ ሀገራት የሚለዩባቸው ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። ምሽት አራት ሰዓት ፖርቹጋል ከስፔን በዳላስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል። ፖርቹጋል በ32ቱ የጥሎ ማለፍ ዙር ክሮሺያን 2 ለ 1 ስታሸንፍ ስፔን በበኩሏ ኦስትሪያን በመርታት ቀጣዩን ዙር ተቀላቅላለች። የአውሮፓ እግር ኳስ ኃያላኑ በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ2010 ባዘጋጀችው 19ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በተመሳሳይ 16 ውስጥ ተገናኝተው ስፔን በዴቪድ ቪያ ጎል 1 ለ 0 ማሸነፏ ይታወሳል። በወቅቱ ስፔን የዓለም ዋንጫው ባለቤት መሆን የቻለች ሲሆን፣ ይህ ስኬትም እስካሁን ድረስ በታሪኳ ያስመዘገበችው ብቸኛ የዓለም ዋንጫ ድሏ ነው። በሩሲያ እ.አ.አ በ2018 በተካሄደው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ሶስት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለፖርቹጋል ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል። ብሔራዊ ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ባደረጓቸው 41 ጨዋታዎች ስፔን 17 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ፖርቹጋል ብስድስቱ ድል ሲቀናት በቀሪ 18 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በዛሬው ጨዋታ የ41 ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና የ18 ዓመቱ ላሚን ያማል የሚጠበቁ ሲሆን በጨዋታው ተመጣጣኝ እና አዝናኝ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከአሜሪካ እና ቤልጂየም አሸናፊ ጋር ይገናኛል።   አሜሪካ ከቤልጂየም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በሲያትል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ከዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ በ32ቱ ጥሎ ማለፍ ቦሲኒያ ሄርዞጎቪናን 2 ለ 0 ማሸነፏ እንዲሁም ተጋጣሚዋ ቤልጂየም በበኩሏ ሴኔጋልን ከ2 ለ 0 መመራት ተነስታ ውጤቱን ቀልብሳ 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር መቀላቀሏ ይታወቃል። ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል። ኡራጓይ እ.አ.አ በ1930 ባዘጋጀችው የመጀመሪያ የፊፋ የዓለም ዋንጫ በምድብ አራት ተገናኝተው አሜሪካ 3 ለ 0 አሸንፋለች። በርት ፓቴናውድ ሶስቱንን ግቦች ከመረብ በማሳረፍ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ሀትሪክ የሰራ ተጫዋች መሆንም ችሏል። ብራዚል እ.አ.አ በ2014 ባዘጋጀችው 20ኛው ፊፋ ዓለም ዋንጫ 16 ውስጥ ተገናኝተው ቤልጂየም 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፋለች። ኬቨን ደ ብሮይን እና ሮሜሎ ሉካኩ ግቦቹን ሲያስቆጥሩ ሁለቱም ተጫዋቾች በአሁኑ የዓለም ዋንጫ የቤልጂየም ስብስብ ውስጥ ይገኛሉ። ጁሊያን ግሪን በወቅቱ የአሜሪካን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። ሁለቱ ሀገራት ከ12 ዓመታት በኋላ በድጋሚ 16 ውስጥ ተገናኝተዋል። በአጠቃላይ ሀገራቱ እርስ በእርሳቸው ሰባት ጊዜ ተጫውተው ቤልጂየም ስድስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ በቀሪው አንድ ጨዋታ (በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ) አሜሪካ ድል ቀንቷታል። በአሜሪካ በኩል በውድድሩ ሶስት ግቦችን ያስቆጠረው የአሜሪካው ፍሎሪያን ባሎጉን ከቦሲኒያ ጋር በነበረው ጨዋታ የተመለከተው ቀይ ካርድ አግባብ ባለመሆኑ ምክንያት ተነስቶለት በጨዋታው ላይ እንዲጫወት መወሰኑን ፊፋ አስታውቋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋኒቲኖ የቀይ ካርድ ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይ ደውለው መጠየቃቸውን ተከትሎ ቀይ ካርዱ መነሳቱ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ላይ የተአማኒነት ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። ተጋጣሚዋ ቤልጂየም ውሳኔውን ፍጹም ተቀባይነት የለውም ስትል የተቃወመች ሲሆን የሁሉም ተሳታፊ ሀገራት መብት እንዲጠበቅና በእግር ኳሱ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን ሁሉንም አማራጮች እንደምትመለከት አስታውቃለች። ትራምፕ ውሳኔውን ተከትሎ ፊፋን ያመሰገኑ ሲሆን ፍትሃዊነትን ያሰፈነ ውሳኔ ሲሉ መግለጻቸውን ተከትሎ ውሳኔው ከጨዋታው በፊት ሰፊ መነጋገሪያ ሆኗል። ለቤልጂየም በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በዓለም ዋንጫው ያስቆጠሩት ሊአንድሮ ትሮሳርድ እና ሮሜሎ ሉካኩ በጨዋታው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው። ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጨዋታው አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።
ኖርዌይ እና እንግሊዝ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቀሉ
Jul 6, 2026 469
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር እንግሊዝ እና ኖርዌይ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቅለዋል። ቀደም ብሎ በተደረገው ጨዋታ ኖርዌይ ብራዚልን 2 ለ 1 አሸንፋለች። ማምሻውን በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አርሊንግ ሃላንድ በ79ኛው እና ደቂቃ 90ኛው ደቂቃ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል። የ25 ዓመቱ ሃላንድ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሰባት አድርሷል። ከአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ እና ከፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔ ጋር ተመሳሳይ የግብ መጠን ማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ መምራት ችሏል። ለሀገሩ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 62 ከፍ አድርጓል። ኔይማር በ100ኛው ደቂቃ የብራዚልን ብቸኛ ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።   በሌላ በኩል እንግሊዝ አዘጋጇን ሜክሲኮን 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቅላለች።በአስር ተጫዋች ሁለተኛውን አጋማሽ የተጫወቱት እንግሊዞች በሀሪ ኬን እና ቤሊንግሀም ሁለት ጎሎች አሸንፈዋል። ሀሪ ኬን በውድድሩ ስድስተኛ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል። ሀሪ ኬን በአለም ዋንጫው በድምሩ ያስቆጠራቸውን የጎሎች መጠን ወደ 14 ከፍ አድርጓል። ኖርዌይ በቀጣይ ዙር እንግሊዝን በሚያሚ ትገጥማለች።
ሲዳማ ቡና የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ተረከበ
Jul 5, 2026 874
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል። በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አቤል ሀብታሙ በ70ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ጎሉን አስቆጥሯል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ54 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና በ68 ነጥብ ዓመቱን ጨርሷል። ጨዋታውን ተከትሎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ የሆነው ሲዳማ ቡና ዋንጫውን ተረክቧል። የሊጉ ዋንጫ ሲዳማ ቡና በ1999 ዓ.ም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ያሳካው ትልቁ ድሉ ነው። ሻምፒዮንነቱን ተከትሎ በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል። ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ዋንጫውን ለማንሳት ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ይፋለማል። በዋንጫ ስነ ስርዓቱ ላይ በርካታ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ታድመዋል። በተጨማሪም ሲዳማ ቡና ዛሬ የተጠናቀቀውን ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በማጠቃለያ መርሐ ግብር ወላይታ ድቻን በመለያ ምት በመርታት ዋንጫውን አንስቷል። በዚህም ድርብ ድል አሳክቷል። በሊጉ የመዝጊያ ስነ ስርዓት የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የዘንድሮው የሊጉ ውድድር ዛሬ በ38ኛ ሳምንት ተቋጭቷል። ምድረ ገነት ሽሬ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ መቀሌ 70 እንደርታና አርባምንጭ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረዱ ክለቦች ናቸው። ከከፍተኛ ሊግ ያደጉት ሃላባ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በሊጉ ይሳተፋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ናትናኤል ዳንኤል እና የፋሲል ከነማው ታምራት እያሱ በተመሳሳይ 15 ጎሎች በጋራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቀዋል። የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው በ14 ግቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና የዋንጫ ሽልማቱን በሚረከብበት ዕለት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል
Jul 5, 2026 597
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጠናቀቃል። ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና በ68 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ51 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ሲዳማ ቡና የሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱን ያረጋገጠው በ36ኛ ሳምንት ከነገሌ አርሲ ጋር አንድ አቻ መለያይቱን ተከትሎ ነው። በ1999 ዓ.ም የተመሰረተው ሲዳማ ቡና የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ባለቤት መሆኑ በ19 ዓመት የክለቡ ጉዞ ውስጥ ትልቁ የሚባለው ስኬቱ ነው። ለረጅም ሳምንታት የሊጉ አናት ላይ የቆየው እና በአንጻራዊነት ወጥ አቋም ያሳየው ሲዳማ ቡና ከዛሬው ጨዋታ በኋላ ታሪካዊውን ዋንጫ የሚረከብ ይሆናል። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የዋንጫ አቀባበል ድባቡን ይበልጥ ለቡድኑ ያደምቀዋል። ቡድኑ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት ይሳተፋል። በተጨማሪም ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚፋለም ይሆናል። ዓመቱን በሁለት ዋንጫ የማጠናቀቅ እድል አለው። በ37ኛ ሳምንት ከሃዋሳ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዓመቱን በድል ለመደምደም ከሻምፒዮኑ ጋር ይፋለማል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቅቃል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው። ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል። በዝናብ ስጋት ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ የተዛወረው የሲዳማ ቡና እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ የ2018 ዓ.ም የሊጉ መዝጊያ ጨዋታ እሁድ ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በሳምንቱ አጋማሽ ማስታወቁ ይታወሳል።
ብራዚል ከኖርዌይ፣ ሜክሲኮ ከእንግሊዝ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ ተጠባቂ ፍልሚያዎች
Jul 5, 2026 623
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሁለት የ16 ውስጥ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ብራዚል ከኖርዌይ በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም ይጫወታሉ። የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል 32 ውስጥ ጃፓንን 2 ለ 1 በመርታት ቀጣዩን ዙር ተቀላቅላለች። ኖርዌይ ኮትዲቯርን 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ 16 ውስጥ ገብታለች። ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጀችው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ኖርዌይ 2 ለ 1 አሸንፋለች። ቶሬ አንድሬ ፍሎ እና ኬቲል ሬክዳል በወቅቱ ለኖርዌይ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ቤቤቶ የብራዚልን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ሀገራቱ ከ28 ዓመታት በኋላ በጥሎ ማለፍ መድረክ ተገናኝተዋል። በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድኖቹ እርስ በእርሳቸው ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ኖርዌይ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናት በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ብራዚል ኖርዌይን እስከ አሁን አሸንፋ አታውቅም። አምስት ግቦች በዓለም ዋንጫው ያስቆጠረው የኖርዌው አርሊን ሃላንድ እና አራት ግቦች ያለው ቪኒሸስ ጁኒየር በጨዋታው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው። የሁለቱ ቡድኖች የፊት መስመር አቅም የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል ተብሎ ይጠበቃል። የጨዋታው አሸናፊ ከሜክሲኮ እና እንግሊዝ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።   በሌላኛው መርሐ ግብር ሜክሲኮ ከእንግሊዝ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በሜክሲኮ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከዓለም ዋንጫው አስተናጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሜክሲኮ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ኢኳዶርን 2 ለ 0 በመርታት 16 ውስጥ ገብታለች። ተጋጣሚዋ እንግሊዝ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 2 ለ 1 በመርታት ወደ ሁለተኛው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግራለች። ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እንግሊዝ እ.አ.አ በ1966 ባዘጋጀችው ስምንተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 2 ለ 0 አሸንፋለች። ሰር ቦቢ ቻርልተን እና ሮጀር ሀንት ግቦቹን ለሶስቱ አናብስቶች በወቅቱ አስቆጥረዋል። እንግሊዝ እስከ መጨረሻው በመጓዝ ብቸኛውን የዓለም ዋንጫ ክብሯን ተቀዳጅታለች። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከስድስት እስርት ዓመታት በኋላ ዳግም በዓለም ዋንጫው ተገናኝተዋል። በዓለም ዋንጫው አምስት ጎሎች ያስቆጠረው የእንግሊዙ ሃሪ ኬን እና ሶስት ግቦች ያለው የሜክሲኮው ጁሊያን ኪኖኔስ በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው። የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ድል ማስመዝገብ ቀጥለዋል
Jul 5, 2026 391
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 የፕሪፎንቴይን ክላሲክ -ዩጂን ዳይመንድ ሊግ እና በአሜሪካው የፒችትሪ የጎዳና ሩጫ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል። በአሜሪካዋ ዩጂን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር፣ በሴቶች የሁለት ማይል ርቀት ብርቱ ፉክክር የተስተዋለበት ነበር። ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው አትሌት አለሺኝ ባወቀ ስትሆን፣ የወቅቱ ፈጣን የሆነ ሰዓት 9:20.02 በማስመዝገብ በአንደኝነት አጠናቃለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሒሩት መሸሻ በ9:20.20 በሆነ ሰዓት በቅርብ ልዩነት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በዚሁ የሁለት ማይል ውድድር ላይ የተሳተፉት ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል። አትሌት ማርታ አለማየሁ በ9:21.42 4ኛ ፣አትሌት የኔዋ ንብረት በ9:22.93 7ኛ እና አትሌት አሳየች አይቼው በ9:23.04 8ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በሴቶች የአንድ ማይል ውድድር ላይ የተሳተፉት አትሌት ሳሮን በርሀ በ4:22.50 11ኛ ደረጃን እንዲሁም አትሌት ወርቅነሽ መሰለ በ4:36.80 13ኛ ደረጃን ይዘው ፈፅመዋል። በሌላ በኩል 250ውን የአሜሪካ የነፃነት ቀን በዓል በማስመልከት በተካሄደው 57ኛው የፒችትሪ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ በአስደናቂ ሁኔታ ፍጥነት በመጨመር ውድድሩን በ31:02 በሆነ ሰዓት በአሸናፊነት አጠናቃለች። ሌላኛዋ አትሌት መልክናት ውዱ በ31:03 በአንድ ሴኮንድ ተቀድማ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ሞሮኮ ካናዳን 3ለ0 በመርታት በዓለም ዋንጫው ሩብ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች
Jul 4, 2026 1190
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ መርሐ ግብር ሞሮኮ ካናዳን 3 ለ 0 አሸንፋለች። ማምሻውን በሂውስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የ26 ዓመቱ የአማካይ ተጫዋች አዜዲን ኡናሂ በ50ኛው ፤ በ82ኛው እና ሶፊያን ራሒሚ በጭማሪ ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥሯል። የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድባትም በሁለተኛው 45 የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጋለች። የሞሮኮው ወሳኝ ተጫዋች ኢስማኤል ሳይባሪ (አጥቂ) ባጋጠመው የጡንቻ ጉዳት ምክንያት በ22ኛው ደቂቃ በሶፊያን ራሂሚ ተቀይሮ ወጥቷል። ውጤቱን ተከትሎ ሞሮኮ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪያ ሀገር ሆናለች። በሩብ ፍጻሜው ከፓራጓይ እና ፈረንሳይ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች። ኳታር እ.አ.አ በ2022 በተካሄደው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር በመሆን ታሪክ መስራቷ ይታወቃል። የአትላስ አንበሶች በዘንድሮውም የዓለም ዋንጫ በስኬታማ ጉዟቸው ቀጥለዋል። ከዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ካናዳ ጉዞዋ 16 ውስጥ ተገቷል። በሌላኛው የ16ቱ ጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ፓራጓይ ከፈረንሳይ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዛምቢያ አቻው ተሸነፈ
Jul 4, 2026 374
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 /2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛምቢያ ኢትዮጵያን 2 ለ 1 አሸንፋለች። በንዶላ ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፍሪዳ ንዳሼ እና ፒዳ ሙዙዋ የዛምቢያን ጎሎች አስቆጥረዋል። ምኅረት አየለ የኢትዮጵያን ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፋለች። ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ግብ ማስቆጠሯ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ለመቀልበስ ተስፋ የሚሰጥ ነው። የሁለቱ ሀገራት የመልስ ጨዋታ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል። ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረጋግጣለች። 10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከዛምቢያ ጋር ይጫወታል
Jul 4, 2026 442
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 /2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከዛምቢያ ጋር ታደርጋለች። ጨዋታው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በንዶላ ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም ይካሄዳል። በአሰልጣኝ ራውዳ አሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 8 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ብሩንዲን በአጠቃላይ ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። በካሮል ካኒዬምባ የሚሰለጥነው የዛምቢያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ሩዋንዳን በደርሶ መልስ ውጤት 4 ለ 1 አሸንፋለች። ዛምቢያ በሁለተኛው ዙር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን በድምር ውጤት 7 ለ 0 በመርታት ለወሳኙ ጨዋታ ደርሷል። አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ከዛምቢያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጓ ይታወቃል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ዛምቢያ አቅንቷል። ለዛሬው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በንዶላ ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም አከናውኗል። ተጫዋቾቹ በሙሉ ጤንነት እና በጥሩ ሞራል ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ካሮል ካኒዬምባ ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ላለባት ጨዋታ ለ35 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ያደረገች ሲሆን በመጨረሻ ስብስቡ የተቀነሰ ተጫዋች የለም። የሁለቱ ሀገራት የመልስ ጨዋታ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረጋግጣለች። 10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።
ሞሮኮ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ካናዳ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Jul 4, 2026 509
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል። ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ካናዳ ከሞሮኮ በሂውስተን ስታዲየም ይጫወታሉ። ካናዳ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ደቡብ አፍሪካን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች። የሰሜን አሜሪካዋ ሀገር በዓለም ዋንጫው 16 ውስጥ ስትገባ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሞሮኮ ኔዘርላንድስን በመርታት ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግራለች። በጨዋታው ሞሮኮ በ120 ደቂቃ አንድ አቻ የተለያየች ሲሆን በመለያ ምት ተጋጣሚዋን 3 ለ 2 ረትታለች። የአትላንስ አንበሶቹ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪካቸው 16 ውስጥ ሲገቡ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል። ኳታር ከአራት ዓመት በፊት ባዘጋጀችው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ መርሐ ግብር ተገናኝተው ሞሮኮ 2 ለ 1 ማሸነፏ አይዘነጋም። ሞሮኮ በወቅቱ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ድንቅ ግስጋሴ በማድረግ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጨረሻ አራት ውስጥ የገባች የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር ሆናለች። ብሔራዊ ቡድኖቹ እስከ አሁን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሞሮኮ ሶስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሞሮኮ የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት ወስዳለች። የሁለቱ ሀገራት አሸናፊ ከፓራጓይ እና ፈረንሳይ አሸናፊ ጋር በሩብ ፍጻሜው ይገናኛል። በሌላኛው መርሐ ግብር ፓራጓይ ከፈረንሳይ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ይጫወታሉ። ፓራጓይ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ሳትጠበቅ የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋን ጀርመንን በማሸነፍ 16 ወስጥ ገብታለች። የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በ120 ደቂቃ አንድ አቻ የወጣች ሲሆን በመለያ ምት 4 ለ 3 በማሸነፍ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ማንም ያልገመተውን ውጤት አስመዝግባለች። ፓራጓይ 16 ውስጥ ስትገባ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው። የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ ስዊድንን በበማሸነፍ 16ቱን ተቀላቅላለች። የዘንድሮውን ዓለም ዋንጫ የማንሳት ሰፊ ግምት ያገኘችው ፈረንሳይ ለሰባተኛ ጊዜ ወደ 16ት ውስጥ ገብታለች። ፈረንሳይ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ 16 ውስጥ ተሸንፋ አታውቅም። ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ፈረንሳይ ጨዋታዎቹን በድል ተወጥታለች። ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጀችው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 16 ውሰጥ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 1 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን እስከ መጨረሻው በመሄድ የመጀመሪያ ዋንጫዋን አንስታለች። ስዊድን እ.አ.አ በ1958 ባዘጋጀችው ስድስተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ፈረንሳይ 7 ለ 3 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነበት አሸንፋለች። በዛሬው የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ፈረንሳይ የማሸነፉን ሰፊ የቅድሚያ ግምት ወስዳለች።
ኮሎምቢያ 16ቱን ተቀላቀለች
Jul 4, 2026 263
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ የመጨረሻ ማለፍ መርሐ ግብር ኮሎምቢያ ጋናን 1 ለ 0 አሸንፋለች። ማለዳ ላይ ተጠናቀቀው እና በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጆን አሪያስ በ14ኛው ደቂቃ ጎሏን አስቆጥሯል። ኮሎምቢያ ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ነበራት። ጋና በጨዋታው አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ አላደረገችም። ውጤቱን ተከትሎ ኮሎምቢያ 16 ውስጥ የገባች የመጨረሻ ሀገር ሆናለች። የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በቀጣዩ ዙር ከስዊዘርላንድ ጋር ትጫወታለች። ጋና በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር የተሰናበተች ሰባተኛ ሀገር ሆናለች። የምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ከ18ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት ህልሟ አልተሳካም። ከአፍሪካ 16 ውስጥ መግባት የቻሉት ሞሮኮ እና ግብጽ ብቻ ናቸው። ጨዋታውን ተከትሎ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ተጠናቋል። የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
አምስት ጎሎች በተቆጠሩበት አስገራሚ ጨዋታ አርጀንቲና ኬፕቨርዴን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች
Jul 4, 2026 247
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር አርጀንቲና ኬፕቨርዴን 3 ለ 2 አሸንፋለች። ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሚያሚ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ በ29ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል አርጀንቲናን መሪ አድርጓል። ሌሮይ ዱአርቴ በ59ኛው ደቂቃ የኬፕቨርዴን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ 30 ደቂቃ ተጨምሯል። ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በ92ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል አርጀንቲናን በድጋሚ መሪ አድርጓል። ሲዲኒ ሎፔዝ ካብራል በ103ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ላይ ባሳረፈው ጎል ኬፕቨርዴ አቻ ሆናለች። የኬፕቨርዴው ተከላካይ ዲኔ ቦርጄስ በ111ኛው ደቂቃ ሜሲ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በራሱ ላይ አስቆጥሮ አርጀንቲና አሸናፊ ሆናለች። የ39 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ ሰባት በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መሪነቱን አጠናክሯል። በአጠቃላይ በውድድሩ 20 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን አስቀጥሏል። በዓለም ዋንጫ በስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ እና በውድድሩ ላይ 30ኛ ጨዋታውን ያደረገ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ለአርጀንቲና 123ኛ ጎሉን ያስቆጠረ ሲሆን በአጠቃላይ 918ኛ ፕሮፌሽናል ግቡን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አርጀንቲና 16 ውስጥ ገብታለች። አርጀንቲና በቀጣዩ ዙር ከግብጽ ጋር ትጫወታለች። የደሴቲቷ ሀገር ኬፕቨርዴ ያልተጠበቀ የዓለም ዋንጫ ጉዞዋ 32ቱ ላይ ተገቷል። ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ያላት ኬፕቨርዴ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ ያሳያቸው ብቃት አድናቆት አስችሯታል። የዘንድሮው ውድድር ክስተት ሆናለች። በሶስት ጨዋታዎች አቻ በመውጣት ጥሎ ማለፍ የገባችው ኬፕቨርዴ የመጀመሪያ ሽንፈቷን አስተናግዳለች። ኬፕቨርዴ በጨዋታው የዓለም ሻምፒዮናዋን አርጀንቲናን ፈትናለች። የ40 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ቮዚኒሃ ያለቀላቸውን ኳሶችን በማዳን ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።
ግብጽ 16ቱን ተቀላቀለች
Jul 4, 2026 233
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ግብጽን አውስትራሊያን በመለያ ምት አሸንፋለች። ትናንት ማምሻውን በዳላስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢማም አሹር በ13ኛው ደቂቃ ግብጽን መሪ ያደረገችውን ጎል አስቆጥሯል። የ28 ዓመቱ አሹር በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያገባቸውን ጎሎች ብዛት ሁለት አድርሷል። የግብጹ ተከላካይ መሐመድ ሃኒ በ55ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ ያስቆጠረው ጎል አውስትራሊያን አቻ አድርጓል። ሃኒ በአንድ የዓለም ዋንጫ ሁለት ጎሎች በራሱ ላይ ያስቆጠረ የመጀመሪያ ተጫዋች ሆኗል። ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ምክንያት 30 ደቂቃ የተጨመረ ሲሆን ጎል ሊቆጠር አልቻለም። ግብጽ በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ 16ቱን ተቀላቅላለች። የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ስታሸንፍ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሞሮኮን ተከትላ ወደ ቀጣዩ ዙር የገባች ሁለተኛ የአፍሪካ ሀገር ሆናለች። ግብጽ በቀጣዩ ዙር ከአርጀንቲና ጋር ትጫወታለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም