ማህበራዊ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበራዊ
በውጭ ሀገር ተደብቀው በኢትዮጵያዊያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተያዙ
Jul 17, 2026 446
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/ 2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዱባይ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በውጭ ሀገር ተደብቀው በኢትዮጵያውያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ዳውድ ተፈሪ ለገሰ እና ደስታ ተገኝ አበጋዝ የተባሉ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። ሁለቱ ዋና ተጠርጣሪዎች የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም 105 ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዱባይ በመውሰድና ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ ከተጎጂዎች በመሰብሰብ፣ በበርካታ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ የቆዩ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከዱባይ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ሥር ውለው ለሀገራችን ተላልፈው እንዲሰጡ አድርጓል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በደረሰው ጥቆማ፣ ተጠርጣሪዎቹ ዱባይ ተቀምጠው ሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ወጣቶችን በመመልመል ወደ ዱባይ በመላክ፣ በተዘጋጀ የማገቻ ቦታ በማቆየት፣ በተለይ በሴቶች ላይ ጥቃት በማድረስና በማሰቃየት ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጽሙ የቆዩ መሆናቸው ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቶ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው በተቀናጀ መንገድ ወንጀሉን ሲፈፅሙ በቆዩ ዳውድ ተፈሪ ለገሰ ፣ ደስታ ተገኝ አበጋዝ እና በግብረአበሮቻቸው ላይ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማውጣት፣ ውጭ ሀገር ያሉትን ከዱባይ ፖሊስ ጋር በትብብር በመስራት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ለሀገራችን ተላልፈው እንዲሰጡ አድርጓል። ተጠርጣሪዎቹ ምንም ዓይነት ሰውን ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው፣ በሀገር ውስጥ ያለው ቡድን ከውጪ ካለው ቡድን ጋር ትስስር በመፍጠርና በተቀናጀ መልኩ "በተለያዩ ካምፓኒዎች ስራ እናስቀጥራችኋለን’’ በማለት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ዜጎችን ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመመልመል፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና ያልተገባ ተስፋ በመስጠት ከአንድ ሰው ከ320 ሺህ እስከ 600 ሺህ ብር በመቀበል ማታለያ የቱሪስት ቪዛ አዘጋጅተው በመላክ፣ በሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው በተከፈተ የባንክ አካውንት ገንዘቡን በኢትዮጵያ ብር፣ በድርሃም እና በሪያል ገቢ የሚያስደርጉ መሆናቸውን ፖሊስ ደርሶበታል። ገንዘቡን የከፈሉ ተጎጂዎች ዱባይ እንደገቡ በጉልበት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ከተጎጂዎች "ኮሚሽን" በሚል ተጨማሪ ገንዘብ በማስከፈል እንዲሁም የሁለት ወር የቱሪስት ቪዛ ሲያልቅ "የሁለት ዓመት የመኖሪያ ፍቃድ እናሰጣችኋለን፤ ካልከፈላችሁ ግን ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳላችሁ" በማለት በአንድ ሰው 1 ሺህ 200 ድርሃም እንዲከፍሉ በማድረግ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ግፍና ስቃይ ሲያደርሱ ቆይተዋል ብሏል ፖሊስ። ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን ከዱባይ ኤርፖርት ከተቀበሉ በኋላ ሰዎችን የሚያከማቹበት ቦታ በመውሰድ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ በርካታ ወንዶችንና ሴቶችን በማገት፣ ምግብ በስምንት ቀን አንድ ጊዜ ደረቅ ሩዝ በመስጠት ለከፍተኛ ርሃብ እና እንግልት እንዲሁም ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ሲያደርሱባቸው መቆየታቸው ተደርሶበታል። በተጨማሪ ባደረገው ክትትል፣ በሀገር ውስጥ ሆነው ዱባይ ካሉት ግብረ-አበሮቻቸው በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ሰዎችን መልምሎ በመላክና የባንክ አካውንት ከፍተው ገንዘብ እያሰባሰቡ የነበሩ 1ኛ ብዙአየሁ አውግቸው በሀይሉ እና 2ኛ ራህመት አበበ እሸቴ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን በስፋት በማከናወን ላይ መሆኑንም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገልጿል። ፖሊስ ምርመራውን ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ ይህንን ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ለማጣራት እንዲሁም በእነዚህ ተጠርጣሪዎች አማካኝነት ከሀገር ወጥተው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸው ከነበሩ ግለሰቦችና ተጎጂዎች ካሉበት ዱባይ የቀጥታ ቨርቹዋል የምስክርነት ቃላቸውን በመቀበል ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። ፖሊስ ሕጋዊ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ከሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር በመመሳጠር ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙና በዜጎች ከፍተኛ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ኤጀንሲዎችም መኖራቸውን ማረጋገጡን ጠቅሶ በቀጣይ ምርመራውን በእነዚህ አካላት ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዚህ ውስብስብ ወንጀል ውስጥ በህጋዊ ሽፋን ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለመያዝ ከዱባይ ፖሊስና በዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅንጅት በመስራት ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናውን እያቀረበ፤ ኅብረተሰቡ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ 991 ነፃ የስልክ መስመር እና ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ (SPS)ን በመጠቀም መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል።
የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ ፍትህ ለመስጠት እያስቻለ ነው
Jul 17, 2026 295
ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ):- የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ ፍትህ በመስጠት ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር እያስቻለ መሆኑ ተገለጸ። በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ድሬዳዋ ምድብ ችሎት የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአትን ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል። መግባቢያ የሰነዱን የፈረሙት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው። የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት አንዳንድ ቤተሰባዊ ጉዳዮችን በማስማማት በፍጥነትና በውጤታማነት ለመጨረስ የሚያስችል የዳኝነት ሥርአት ነው። የጋራ መግባቢያ ሰነዱም በድሬዳዋ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማዕከልን በማቋቋም ከባህል ሽማግሌዎች እና ከኃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር በመቀናጀት ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር በስምምነቱ ወቅቱ እንደገለጹት፤ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች አዳዲስ ሪፎርሞች እና በቴክኖሊጂ የታገዙ አሰራሮችን በመተግበር ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ ፍትህ መስጠት ተችሏል። ማህበረሰብ ተኮር ፍትህ እያሰፈኑ ካሉት መካከል በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በመተግበር ላይ የሚገኘው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ስርአት አንዱ መሆኑን አንስተዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ሥርአቱ አንዳንድ ቤተሰባዊ ጉዳዮችን በማስማማት በፍጥነትና በውጤታማነት በመጨረስ የህዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ሥርአት ለመገንባት እያገዘ ነው። ለዚህም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በ13 ምድብ ችሎቶች ከውርስ፣ ከቤተሰብ እና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ 1ሺህ 690 መዝገቦችን በስምምነት በመጨረስ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ ፍትህ መስጠት ተችሏል ብለዋል። በዚህም የማስማማት ጥበብ እና ተቀባይነት ያላቸው የባህልና የኃይማኖት አባቶች የፍርድ ቤት ሥርአትና ነፃነትን ተከትለው የድርሻቸውን እንዲወጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። ዛሬ በድሬዳዋ የተፈረመው የሥራ መግባቢያ ሰነድ ተቀባይነትና ዕውቀት ላላቸው የአገር ሽማግሌዎች፣ የኡጋዝ፣ የአባገዳና የእምነት አባቶች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ሥርአቱን ወደ ተግባር የሚያሸጋገር መሆኑን ገልጸዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት በቤተሰብ፣ በዘመድ አዝማድ እና በነዋሪዎች መካከል የሚነሱ ክርክሮችን በማስማማት ማህበረሰባዊ ትስስርና ግንኙነት በዘላቂነት ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል። ይህም የፍርድ ቤቶችን ጊዜ በመቆጠብ የመዛግብት ፍሰት ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ሥራ የሚሳተፉት ተቀባይነት ያላቸው የባህል አባቶች የህግ ሥርአትን ተከትለው እንደሚሰሩ አመልክተዋል። የስምምነት ፊርማው ሲፈጸም የአገር ሽማግሌዎች፣ የአባገዳ እና የኡጋዝ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ለስምምነቱ ውጤታማነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ድሬዳዋ ምድብ ችሎት በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማዕከል የሚከናወኑ ሥራዎች በየሦስት ወራት በተቋቋመ ቴክኒክ ኮሚቴ የሚገመገም መሆኑም ታውቋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀጣይነት ያለው አጀንዳችን ነው- ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ
Jul 17, 2026 325
አዳማ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ )፡-የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀጣይነት ያለው አጀንዳችን ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ። 3ኛው የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ጠቅላላ ጉባኤ በአዳማ ገልመ አባገዳ አዳራሽ ዛሬ ተካሄዷል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል። ይህም ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ድርሻው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። ለተግባራዊነቱም ከኦሮሞ ሕዝብ የመረዳዳት ባህል የተቀዳውን ቡሳ ጎኖፋ ሥራ ላይ በማዋል ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል። ቡሳ ጎኖፋ የማኅበረሰቡን የመረዳዳት ባህል ይበልጥ ለማጎልበትና በምግብ ራስን ለመቻል ተደማሪ አቅም መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም በክልሉ ዝናብ አጠር በሆኑ 59 ወረዳዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ማህበራዊ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ ማገዙን ተናግረዋል። ተግባሩ ለሰዎች የሚሆን የምግብ ክምችትን ከማሳደግ ባለፈ ውሃን በማቆር የእንስሳት መኖ ለማልማት ማስቻሉን ጠቅሰዋል። የቡሳ ጎኖፋ የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው ቡሳ ጎኖፋ በክልሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም እያገዘ ነው ብለዋል። ለዚህም በእርሻ ሥራና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተሰማራ ይገኛል ያሉት አምባሳደር አለማየሁ፣ ለዚህም በቡልቡላና በነቀምቴ ከተሞች የተቀናጀ የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እየገነባ ነው ብለዋል። በአዲሱ በጀት ዓመት ይህንን በቅንጅት ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ሃላፊ አቶ ሙሐመድ ጁንዳ እንደገለፁት በክልሉ እስካሁን ድረስ 29 ነጥብ 4 ሚሊዮን አባላት ማፍራት መቻሉን አንስተዋል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል። በአይነት ከተሰበሰበው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህልም ለተማሪዎች ምገባና ለመጠባበቂያነት መዋሉን ገልጸዋል። ተግባሩን ለማሳካትም በእርሻ፣ በእንስሳት እርባታና በመጋዘን ግንባታዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል
Jul 17, 2026 333
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ገለጹ። የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በቋሚ የጤና ሥርዓት ውስጥ በማካተት፣ ተደራሽነቱንና ጥራቱን ለማሻሻል የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። የ2018 ዓ.ም የጤና ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በሸገር ከተማ ዳለቲ ማረሚያ ቤት በይፋ ተጀምሯል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ማረሚያ ቤቶች የሕግ የበላይነት የሚከበርባቸው ስፍራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሰብዓዊነት የሚነግስባቸውና ታራሚዎች በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ልቦና ታንጸው ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉባቸው የለውጥ ማዕከላት ናቸው ብለዋል። ታራሚዎች እንደማንኛውም ዜጋ ማግኘት ያለባቸውን ሰብዓዊና የጤና ክብካቤ ሁሉ የማግኘት መብት አላቸው ያሉ ሲሆን የሚያገኙትን የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎትም ለህክምና ተደራሽነት የራሱ አጋዥ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፥ በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ይበልጥ ማስፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የመንግሥትና የግል የጤና ባለሙያዎችን በማስተባበር በየወቅቱ ሰፋ ያለ የሕክምናና የምርመራ ተግባርን ማከናወን እንደሚገባ አመላክተዋል። የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረ ሀገራዊ ንቅናቄ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም ይህንን ተሞክሮ በጤናው ዘርፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በጤና ዘርፉ በየዓመቱ የሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ፣ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራ የጤና ባለሙያዎችንና ሌሎች በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ይህም ለበርካታ ዜጎች ተደራሽ የጤና አገልግሎትን ለማስፋት ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል። በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎችም ነጻ፣ ጥራት ያለውና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል። በማረሚያ ቤቶቹ ያሉ የጤና ተቋማት አቅም እንዲጠናከርና የአገልግሎት ደረጃቸው እንዲሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል። መርሐ ግብሩ የአንድ ቀን ወይም የአንድ ጊዜ እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ተቋማትና ማረሚያ ቤቶች በቀጣይነት የሚተገበር ዘላቂ ፕሮግራም መሆኑንም አብራርተዋል። በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
በሲዳማ ክልል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው
Jul 17, 2026 147
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ምክትልና በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዘርፍ ሃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፍ ሥራ እየተሰራ ነው። በዚህም የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የግልና የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ ላይ በትኩረት መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡ በዋናነትም ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን የማዳፈን፣ የማፋሰስና ቆሻሻ ቦታዎችን የማጽዳት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በክልሉ የወባ ስርጭት ባለባቸው አራት ወረዳዎች ቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መደረጉንና ከ850 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱንም ተናግረዋል፡፡ ከወባ መከላከል ስራው በተጨማሪ በበሽታው የተያዙ ሕሙማን አፋጠኝ ሕክምና እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት የወባ መከላከልና መቆጣጠር ኦፊሰር አቶ ዮናስ ለማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በሚከናወኑ ስራዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡ በዚህም ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማዳፈንና በማፋሰስ ወባን የመከላከል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። ህብረተሰቡ የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ በመጠቀም ወባን እንዲከላከል መደረጉን ገልጸው፣ በቱላ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 12 ቀበሌዎች የቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ተጀምሯል ብለዋል። በሀዋሳ ከተማ ቱላ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን ከወባ በሽታ ተጋላጭነት ለመከላከል የሚያስችል ሙያዊ ድጋፍ ከጤና ባለሙያዎች ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል። በተፈጠረላቸው ግንዛቤም በአካባቢያቸው ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራ ከማከናወን ባለፈ በመኖሪያ ቤታቸው የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት እንዲሁም የቤተሰባቸው የአልጋ አጎበር አጠቃቀምን ማስተካከላቸውንም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የመረጃ ነፃነት አዋጅ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ለማስጠበቅ እና ግልጽነትን ለማስፈን ትልቅ ፋይዳ አለው
Jul 17, 2026 172
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ አዲሱ የመረጃ ነፃነት አዋጅ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ለማስጠበቅ እና ግልጽነትን ለማስፈን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ያፀደቀውን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 1427/2018 አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም አዲሱ አዋጅ የዜጎችን መረጃ የመጠየቅና የማግኘት መብት በአግባቡ እንዲከበር ከማስቻሉ በላይ፣ ቀደም ሲል በነበሩ የሕግና የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለዋል። ከ17 ዓመታት በላይ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የቀድሞው አዋጅ ሀሳብን የመግለጽ እና የመረጃ የማግኘት ነጻነቶችን በአንድ ላይ አጣምሮ በመያዙ በአፈጻጸም በኩል በርካታ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ተናግረዋል፡፡ አዲሱ አዋጅ በ7 ክፍሎች፣ በ60 አንቀጾች እና በ197 ንዑስ አንቀጾች የተደራጀ ሲሆን፣ ዘመናዊ የሰብአዊ መብት ጽንሰ-ሐሳብንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የተከተለ መሆኑን አስረድተዋል። አዋጁ የመረጃ ነፃነት አፈጻጸምን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ድንጋጌዎች መያዙን ጠቅሰው የሕጉ ተፈጻሚነት ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ፣ ከመንግስት ጋር የገንዘብ ትስስር ያላቸውን፣ መንግስታዊ ሥራ የሚያከናውኑትንና የመንግስት ድርሻ ያላቸውን የግል ተቋማትም ያካትታል ብለዋል። በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥ ግልጽ የአሰራር ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት የተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው መረጃ በሰነድ ባይደራጅም እንኳ በቃል እንዲሰጥ ከተጠየቀ የመስጠት ግዴታ እንደተጣለበትም ጠቅሰዋል፡፡ ተቋማት መረጃዎችን በፍጥነት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊና በኮምፒውተር የታገዘ የሰነድ አያያዝ ሥርዓት የመዘርጋት ግዴታ እንዳለባቸው መደንገጉንም ጠቁመዋል፡፡ የዜጎችን መብት ለማስከበር የመረጃ ጥያቄ ምላሽ መስጫ ጊዜያት በአዋጁ እንዲያጥሩ መደረጉን ጠቅሰው መደበኛ የመረጃ ጥያቄ ከ30 ቀናት ወደ 21 የሥራ ቀናት ዝቅ ተደርጓል፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ ለ14 ቀናት ሊራዘም ይችላል ብለዋል። የአስቸኳይ መረጃ ጥያቄዎችም ከ10 ቀናት ወደ 48 ሰዓታት ዝቅ እንዲል መደረጉንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ አዋጁ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ልዩ የሕግ ከለላ መስጠቱን ዋና ዕንባ ጠባቂዋ ስመኝ ውቤ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ይህንን አዋጅ በአግባቡ ለማስፈጸም ሰፊ የክትትል፣ የማስፈጸም፣ አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድና ስልታዊ ምርመራዎችን የማካሄድ ሥልጣን እንደተሰጠው ገልጸዋል።
በክልሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው
Jul 17, 2026 120
ቦንጋ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰትም በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። ከተረጂነት በመላቀቅ ለሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል። የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለማ መሠለ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው:: በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተከሰተ የዝናብ እጥረት እና እርጥበት በበልግ ወቅት በ30 ሺህ ሄክታር ማሳ የለማ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል። በዚህም በቀጣይ በእነዚህ አካባቢዎች ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ እጥረት ችግር ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የሰብል እና የተለያዩ ሥራስሮችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ ቀድሞ እንደሚጀምርና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ከአየር ትንበያ የተገኘ መረጃ ያሳያል ያሉት ኮሚሽነር ለማ (ዶ/ር)፤ ይህም ጎርፍ፣ የመሬት ናዳና ሌሎች አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል አመልክተዋል። በዚህ ሊከሰት የሚችልን ድንገተኛ አደጋ ቀድሞ ለመከላከል በስጋት በተለዩ 573 ቦታዎች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ የቅደመ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም በዝናብ እጥረትም ሆነ ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ለሚከሰት አደጋ በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ጠንካራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል ። ለዚህም ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የእህል ክምችት፣ የመጠባበቂያ ፈንድ፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ የማሰባሰብና ሌሎች ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው ያነሱት። እስካሁንም 800 ኩንታል የሕፃናት አልሚ ምግብ፣ ከ7ሺህ 200 በላይ ኩንታል የእህል ክምችት፣ 1ሺህ 474 ቁሳቁስ እና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። ዝግጅቱ በየደረጃው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፣ የከፋ ችግር ካጋጠመም ከተረጂነት ወጥቶ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ መጠባበቂያ ፈንድ ተይዟል ብለዋል። ህብረተሰቡ የተፈጠረለትን ግንዛቤ በአግባቡ በመተግበር ራሱን ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች መከላከል እንዳለበትና ባለድርሻ አካላትም ጠንካራ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በገጠር ሞዴል መንደሮች ምቹና ዘመናዊ አኗኗር እውን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር እያረጋገጥን ነው - ነዋሪዎች
Jul 17, 2026 232
አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦በገጠር ሞዴል መንደሮች ምቹና ዘመናዊ አኗኗር እውን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር እያረጋገጥን ነው ሲሉ በጋሞ ዞን ሐመሳ ቀበሌ የኢሊሎ ሞዴል የገጠር መንደር ነዋሪዎች ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን የሀማሳ ሞዴል መንደር መመርቃቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት መንደሩ የአርሶ አደሩን ኑሮና ምርታማነት ለማሻሻል የሚያግዙ ዘመናዊ የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የእንስሳት ማደሪያ፣ የአትክልት ስፍራ፣ የባዮ ጋዝ እና የንብ ቀፎዎችን ያሟሉ በመሆኑ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል። ይህ ሞዴል መንደር የገጠሩን ማህበረሰብ ክብር፣ ምቾት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑንም ማንሳታቸው የሚታወስ ነው። ኢዜአ ካነጋገራቸው የመንደሩ ነዋሪዎች መካከል አቶ አስፋው አያኖ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በግንዛቤ እጥረት ገንዘባቸውን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ኑሯቸው ያልዘመነ እንደበር አስታውሰዋል። አሁን በአካባቢያቸው የተገነባው ሞዴል የገጠር መንደር መኖሪያ ቤታቸውን ከማዘመን ባለፈ አኗኗራቸውን ለመቀየር ማስቻሉን ተናግረዋል። በግቢያቸው ውስጥ የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከማልማት ባለፈ በዶሮ እና ፍየል እርባታም ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ባለቤታቸው ወይዘሮ ወይንሸት ሀድጉም በገጠር ሞዴል መንደሩ የፀሐይ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። ለብቻው የተዘጋጀ የእንስሳት ማደሪያ ያለውና ለዘመናዊ ኑሮ የሚያስፈልጉ ቁሶች የተሟሉለት በመሆኑ ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። አቶ ደስታ ኡሊሶ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ደግነሽ ደምሴ፤ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለኑሮ አስፈላጊ ግብአቶች በሌለው መኖሪያ ቤት ውስጥ በችግር ይኖሩ እንደነበር አንስተዋል። በሐመሳ ቀበሌ ኢሊሎ መንደር የገነቡት ሞዴል መኖሪያ ቤት ኤሌክትሪክ ሃይልን ጨምሮ ሌሎች ግብአቶች የተሟላላት በመሆኑ ምቹና ዘመናዊ ኑሮ ለመምራት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። ሞዴል የገጠር መንደሩ ዘመናዊነትን ለተላበሰ የኑሮ ዜይቤ መነሻ ሆኖናል ያሉት ደግሞ አቶ ከበደ ገቢሳ ናቸው። አርሶ አደሩ ሀብት እያለው በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ኑሮው ሳይዘምን መቆየቱን አስታውሰው፣ ሞዴል መንደሩ ንጹህና ሁሉም መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል። የመንደሩ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በገጠር ኮሪደር እሳቤ የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻልና አኗኗራቸው እንዲዘምን በቁርጠኝነት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ለሃገራዊ ምክክር ጉባዔ በመጣችበት ለተገላገለችው ልጅ "ምክክር" ብላ ስም ያወጣችው እናት
Jul 16, 2026 1003
ምክክር ጉባዔ ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየመከሩ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከልም "ምንም እንኳን የመውለጃዬ ቀን ቢቃረብም “ሀገሬ ጠርታኝ አልቀርም” በማለት ከጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመጣችው ወጣት ክርኑዶ ኡጁሉ፣ በጉባኤው ሂደት ላይ እያለች በዘውዲቱ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች። ወጣት ክርኑዶ ኡጁሉ በጉባዔው ሒደት ላይ እያለች በዘውዲቱ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባረፈችበት ቤት በመገኘት እንኳን በሰላም ተገላገልሽ ብለዋታል። ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ፥ የሀገር ፍቅር እና የእኔነት ስሜት ሲኖር የማይቻል ነገር አለመኖሩን ማሳያ የሆነችውን ይህችን ጀግና እናት፤ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡመድ ጋር በመሆን ባረፈችበት ቤት በመገኘት እንኳን ደስ አለሽ ብለናታል ብለዋል ። ይህች ጀግና እናት፤ የተለመደውን ስም የማውጣት ባሕል በመተው፣ የልጇን ስም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዲያወጣላት በጠየቀችው መሰረት የሕፃኑን ስም "ምክክር" ብላዋለች ሲሉም አመልክተዋል። ዛሬም በሄድንበት ወቅት፣ ወጣቷ የመጣችበትን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ከጥቂት ቀናት እረፍት በኋላ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው በልበ ሙሉነት እንደምትመለስ አረጋግጣልናለች ነው ያሉት። ከንቲባዋ ጉባዔውን አጠናቅቃ ወደ መጣችበት እስክትመለስ ድረስ ለእሷና ለልጇ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡ ከንቲባ አዳነች ፥ እህታችን ወንድ ልጇን በሰላም ተገላግላ በደስታ እንደተሞላች ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ሀገራችንም ከገጠማት አንዳንድ ችግሮች በምክክር እና በንግግር ተገላግላ፣ ትልቅ እና ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ እንደሚሆንላት ፅኑ እምነታችን ነው ብለዋል፡፡ ሕጻን ምክክር እና መሰል የኢትዮጵያ ሕፃናት ሁሉ ቦርቀው እና ተደስተው የሚያድጉባት እንዲሁም የሚረከቧት ሀገር ሰላሟ ሙሉ የሆነች፣ የሕዝቦች ፍቅር ያበበበት እና የበለፀገች ኢትዮጵያ እንድትሆንም ተመኝተዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ ነው
Jul 16, 2026 460
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፤ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም ተቋሙ ዘመኑን የሚመጥን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋት፣ የአሰራር ሥርዓቱን በማዘመን እና ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታ የሚያሳድጉ ተጨባጭ ለውጦች ማምጣቱን ገልጸዋል። የፓስፖርት እና የቪዛ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የይለፍ ሰነዶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፈው በጥራት እና በደህንነት እንዲመረት መደረጉን ጠቅሰው በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርቶች ታትመው ለዜጎች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት መስጫ ማዕከላትን ከነበሩበት 12 ወደ 23 በማሳደግ ተደራሽነቱን ማስፋፋት መቻሉን ጠቅሰው በአየር እና በየብስ የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ከ7 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ መንገደኞች ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች 42 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡንም ጠቁመዋል። በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዥ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ በተደረገው ቁጥጥር ከ55 ሺህ በላይ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል። እንዲሁም ተገቢነት ያለው ምዝገባ ያላደረጉ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ መደረጋቸውን አመላክተዋል። የተቋሙን የሰው ኃይል አደረጃጀት እና ልማት በማሻሻል አገልግሎቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ለውጡን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደነበሩም ገልጸዋል። የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት ለሚፈልጉ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚሲዮኖች አማካይነት ከፊታችን ሐምሌ 15 ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል። የተቋሙን አገልግሎት የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ከሚመለከታቸው ህጋዊ ተቋማት ብቻ ማስረጃዎችን ይዞ መቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በዳኝነት ስርዓቱ የተካሄዱ የአሰራር ማሻሻያዎች ፈጣን፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው ፍትህ ለመስጠት አስችለዋል
Jul 16, 2026 437
ባህር ዳር፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ በዳኝነት ስርዓቱ የተካሄዱ የአሰራር ማሻሻያዎች ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ግልጽ እና ተአማኒነት ያለው ፍትህ መስጠት ያስቻሉ መሆናቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ገለጹ። የክልሉ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመትና የሶስት ዓመቱን የስትራቴጂክ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል። ፕሬዝዳንቱ አቶ አለምአንተ አግደው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፣ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ለክልሉ ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መሰረት ነው። በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩትን እንደገና አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት ዳኞችንና ሰራተኞችን በአመለካከት የማነጽ፣ በእወቀትና ክህሎት የመገንባት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ እንግልትን በመቀነስ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል። ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው ንግድና ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በባህር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል። በክልሉ ከወረዳ እስከ ክልል ባሉ ፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላስመዘገቡት ከፍተኛ ስኬት ምስጋና አቅርበው የተመዘገቡ ስኬቶችን የማስቀጠል ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ በበኩላቸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዲጂታል ፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ በአራት ምድብ ችሎቶች ፣ በ14 ከፍተኛና በ27 የፓይለት ወረዳ ፍርድ ቤቶች "የስማርት ፍርድ ቤት" በማዘጋጀት የዳኝነት አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል። በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 16 ሺህ 606 መዛግብት በኢ-ፋይሊንግ ስርአት በመክፈት ሁለት ሺህ 564 ደንበኞችን በስማርት ችሎትና በቪዲዮ ኮንፈረንስ የፍትህ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል። የዲጂታል አገልግሎቱም ተገልጋዮች ወደ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመመላለስ ከሚደርስባቸው እንግልት ከመታደግ በተጨማሪ ያወጡት የነበረውን ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን አስገንዝበዋል። ዛሬ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይም የሃይማኖት አባቶች፣ የተቋማት ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛና ጠንካራ ለማድረግ የተተገበሩ የህግ ማዕቀፎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት አስችለዋል
Jul 16, 2026 407
ሀዋሳ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛና ጠንካራ ለማድረግ የተተገበሩ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት ማድረጋቸውን በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማህበራት ገለጹ፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የዴሞክራሲ ተቋማት ጠንካራ መሠረት ይዘው በገለልተኛነት እንዲሰሩ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታዎች ውጤት እያመጡ ናቸው፡፡ በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማህበራት እንደገለጹት፤ የሕግና የተቋማት ማሻሻያ አዳዲስ አዋጆች መጽደቃቸው ተቋማቱ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል። ይህም የዴሞክራሲ ባህል እየተጠናከረ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል። የተቋማቱ መጠናከር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻላል የሕዝብ አመኔታ እያደገ እንዲመጣ ማድረጉን ተናግረዋል። ከማህበራቱ መካከል የኢየሩሳሌም የሕፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ሀዋሳና አካባቢው ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅና የሲዳማ ክልል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተባባሪ አቶ ማስረሻ ክብረት፤ ተቋማቱ ገለልተኛ እንዲሆኑ መደረጉ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ የሲቪክ ማህበራት በነፃነት እንዲሰሩ የተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ዜጎች በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በምርጫ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሲቪክ ማህበራት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ገለልተኛ ሆነው መታዘብ እንዲችል ያገኘውን ፈቃድ ተጠቅሞ ሃላፊነቱን መወጣቱን ተናግረዋል፡፡ ምርጫው ነጻ፣ አሳታፊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የመራጮችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ አበክሮ መስራቱንም አስታውሰዋል። የሪሰረክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ብስራት ቦርሳሞ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ለውጡን ተከትሎ የዴሞክራሲ ተቋማት በተሻለ መንገድ እየተገነቡና አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ተቋማቸውም ገለልተኛ ሆኖ በምርጫው ሂደትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ ያገኘውን ዕድል በመጠቀም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ ከሲቪክ ማህበራት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ተግባር በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮችን ግንዛቤ ማጎልበት ላይ በመስራት የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለበት አስተዋጽኦ ማድርጋቸውንም ገልጸዋል። ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደት የጠንካራ ተቋማት መኖር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ብስራት፣ የተጀመረው ተግባር መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል፡
በጅማ ዞን አዲሱ መናኸሪያ ለማሕበረሰቡ ምቹ አገልግሎት እየሰጠ ነው
Jul 16, 2026 180
ጅማ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ በጅማ ዞን ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመናዊ መናኸሪያ ለማሕበረሰቡ ምቹ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተገልጋዮች እና አሽከርካሪዎች ገለጹ። አሽከርካሪዎች እና ተገልጋዮቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አዲሱ መናኸሪያ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የትራንስፖርት መስተንግዶ ፣ ክፍተቶችንና መጨናነቅን ያቃለለ ነው። ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ አብዱለዚዝ አላካ እና ሰሚራ አብዱልቃድር፤ አዲሱ መናኸሪያ ግልጽ፣ ምቹ እና ቁጥጥር የሚደረግበት አገልግሎት እንድናገኝ አድርጎናል ብለዋል። የተሻሻለው አገልግሎት ምቹ የሆነ እና የተሻለ ጉዞ እንዲኖር በማድረግ ትልቅ እፎይታን የሰጣቸው እንደሆነም ነው ያመለከቱት። አቶ ነጋ ጀማል በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በአዲሱ መናኸሪያ ምቹ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ከጅማ ወደ አዲስ አበባ የሚመላለሱት አሽከርካሪ ሙስሊም በድሩ እና አብዱላሂ አባፊራ ፤ቀደም ሲል በነበረው የተጨናነቀ እና አመቺ ያልሆነ መናኸሪያ በተደጋጋሚ ለአደጋ ይጋለጡ እንደነበር ገልፀዋል። መናኸሪያው በአዲስ መልክ ተገንብቶ መጠናቀቁ ያለምንም ስጋትና እንግልት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ምቹ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። በጅማ ዞን ትራንስፖርት ኤጀንሲ የስምሪት ኃላፊ የሺ ካሳ እንደገለጹት፤ በዞኑ ደረጃውን የጠበቀ የመናኸሪያ ማስፋፋያ በማካሄድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ተችሏል። ከዚህ ውስጥም ለተጓዦች በቴክኖሎጂ የታገዙ ምቹ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መቻሉ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ማድረጉን ገልጸዋል። የትራንስፖርት አገልግሎትን ምቹ ለማድረግ መቻሉም በአካባቢው ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ በእጅጉ ለማነቃቃት እንዳስቻለም ነው የተናገሩት። አዲሱ መነኸሪያ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ1 ሺህ 100 በላይ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገዱን አመልክተው አፈፃፀሙ መናኸሪያው የነበረውን የአገልግሎት አቅም እስከ አራት እጥፍ እንዳሳደገው ገልፀዋል። ይኸም ማሕበረሰቡን ከተጨማሪ ወጪና እንግልት ከማዳኑም በላይ፣ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ህገ-ወጥ የትራንስፖርት ስምሪት እንቅስቃሴዎችን ለመታደግ ማስቻሉን ጠቁመዋል። አዲሱ መናኸሪያ የጅማ ዞን ወረዳዎችን ጨምሮ እንደ ቦንጋ፣ ተርጫ፣ አመያ፣ ወልቂጤ፣ ቡኖ በደሌ እና ለሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች ምቹና የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተቋም ነው
Jul 16, 2026 180
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተቋም መሆኑን የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል፡፡ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ በዚሁ ጊዜ፣ ተቋሙ በአህጉር ደረጃ ሞዴል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሰፊ የለውጥ ጉዞ በማድረግ በአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ከሚታመኑባቸው የልህቀት ማዕከላት አንዱ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኞችን አስቀድሞ በመከላከል እንዲሁም ሲከሰቱ በፍጥነት በመቆጣጠር ረገድ የገነባው አቅም ለሌሎች አፍሪካውያን አገራት ትልቅ አርአያ መሆኑን አድንቀዋል። በአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የነበራቸው አገራት በቁጥር 12 ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 40 ማደጋቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህ ዕድገት የኢትዮጵያ ተሞክሮ ትልቅ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል። አህጉሪቱ በቀጣይ የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት ያላቸውን አገራት ቁጥር ወደ 50 ለማድረስ ግብ የጣለች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ ዋና ሞዴል እንደምታገለግል አስረድተዋል። በአፍሪካ ጠንካራ የላቦራቶሪ ትስስር መኖር የሕብረተሰብ ጤና ሥራዎችን ለመከወን ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ማዕከሉ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የላቦራቶሪ ትስስር መረብ ለመገንባት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያም የዚህ የሙከራ ትግበራ መነሻ ከሆኑት ቀዳሚ አገራት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል። የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበትና በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያውያንም በኢንስቲትዩቱ ባስመዘገበው ውጤትና በደረሰበት የልህቀት ደረጃ ሊኮሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓትና የላብራቶሪ አቅም ገንብታለች- ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ
Jul 16, 2026 227
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓትና የላብራቶሪ አቅም የገነባች ሀገር መሆኗን በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ ገለፁ። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል። በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ በዚሁ ወቅት፥ ኢንስቲትዩቱ ባለፈው አንድ ክፍለ ዘመን በሕብረተሰብ ጤና ዘርፍ ላስመዘገባቸው ታላላቅ ስኬቶች አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች አስተዳደር ረገድ የዓለም ጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል አድርጎ ለመሰየም የሚያስችል የድጋፍ ደብዳቤ በቅርቡ ለጤና ሚኒስቴር እንደሚላክም ይፋ አድርገዋል። በተጨማሪም የኢንስቲትዩቱ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ቡድን ዓለም አቀፍ የእውቅና ማረጋገጫ የማግኘት ሂደት የጀመረ ሲሆን ይህ ሂደት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ቡድን ያላት ሁለተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ትሆናለች ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ የቅኝት፣የላብራቶሪ፣ ምርምር፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትና ምላሽ እንዲሁም በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ቀረጻን በማቀናጀት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም እና ጠንካራ ከሆኑ የሕብረተሰብ ጤና ላብራቶሪ ሥርዓቶች አንዱን መገንባት ችላለች ብለዋል። በቅርቡ የተከሰተውን የማርበርግ ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ በመስጠት ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ችላለች ሲሉ ጠቅስዋል። የኢንስቲትዩቱ የዳበረ ልምድና የባለሙያዎች ብቃት አሁን ላይ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ጎረቤት ሀገራት በቴክኒክ ትብብር፣ በላብራቶሪ አገልግሎትና በሕብረተሰብ ጤና አመራር ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 11 ቀን 1947 የዓለም ጤና ድርጅት መስራች አባል በመሆን በይፋ የተቀላቀለች ሲሆን ባለፉት 79 ዓመታት ከድርጅቱ ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ሥርዓትን በመቅረጽ ረገድ ጉልህ ሚና ስትጫወት መቆየቷን አስታውሰዋል። ከሁሉም ስኬቶች ጀርባ ያለው የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ሕዝቧና በኤፒዲሚዮሎጂ፣ በላብራቶሪ ሳይንስና በአደጋ ጊዜ አስተዳደር ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ነው ሲሉ ተናግረዋል። የአየር ንብረት ለውጥ፣ አዳዲስና ዳግም የሚቀሰቀሱ በሽታዎች፣ የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ እና ሰብአዊ ቀውሶች የወደፊቱን የጤና ገጽታ እየቀየሩት መሆኑን ጠቅሰዋል። እነዚህን ለመቋቋም እንደ ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትን ማጠናከር፣ ጠንካራ አጋርነት መፍጠርና የማይበገሩ የጤና ሥርዓቶችን መገንባት የግድ ይላል ብለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ኢንስቲትዩቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ የዲጂታል ጤና ሥርዓትን ለማስፋፋትና ዓለም አቀፍ የጤና ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሀገር ልማት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሰረት መሆኑን በጽኑ ያምናል-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
Jul 16, 2026 240
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሀገር ልማት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሰረት መሆኑን በጽኑ ያምናል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል። ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለዜጎች ጤንነትና ለሀገር ደህንነት ያለው ሚና ወሳኝ ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ የመቶ ዓመት ጉዞ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ጤና የምታደርገው ጥረትና የጤና ሥርዓት ግንባታ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። የሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት ከህብረተሰብ ጤና ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ጥንካሬ የወደፊት እርምጃዋ በዜጎቿ ጤና መጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት የሕክምና ምርምር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ፈታኝ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ የጤና ቀውሶችን፣ ወረርሽኞችንና የተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ያሳየው አፈጻጸም የሚደነቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም እንደ ኮቪድ-19፣ ኤምፖክስ እና ማርበርግ ባሉ ወረርሽኞች ወቅት ኢንስቲትዩቱ ያሳየው ፈጣን ምላሽና ሳይንሳዊ አመራር ለሀገሪቱ ክብርን ያጎናጸፈ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሀገር ልማት፣የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን በጽኑ ያምናል ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ። መንግሥት ጠንካራ ተቋማትን የሀገር ግንባታ መሠረት አድርጎ እንደሚመለከት በማስታወስ፣ ለኢንስቲትዩቱ የመሠረተ ልማትና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ኢንስቲትዩቱ ለወደፊቱ ይበልጥ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆን መንግሥት አመቺ የፖሊሲ መደላድልን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። ባለፉት ስኬቶች ላይ በመመሥረት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ማዘመን እንደሚገባ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበሽታዎችን ስርጭት አስቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ፈጣንና ዘመናዊ መረጃ አያያዝና ትንተና ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ጠቅሰዋል። የኢንስቲትዩቱ መቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ያለፈውን የሚዘክርበት፣ የአሁኑን የሚያመሰግኑበትና ለወደፊቱ የላቀ ዕቅድ የሚያቅዱበት መሆኑንም ገልጸዋል። የኢንስቲትዩቱ የፅናት፣ የእድሜና የህልውና ሚስጥር የሚቀዳው ከሰራተኞቹና ከተመራማሪዎቹ ጥንካሬ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግሥት ለኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ መሳካት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ100 ዓመታት ለዜጎች የጤና ጥበቃ ውጤታማ ዘመን የማይሽረው አሻራ አሳርፏል
Jul 16, 2026 208
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 100 አመታት ለዜጎች ጤና ጥበቃ ውጤታማነት ዘመን የማይሽረው የጥናትና ምርምር አሻራ ማሳረፉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ገለጹ። ኢንስቲትዩት የ100ኛ በዓሉን ከዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያከብራል። የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል። በክብረ በዓሉ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 100 ዓመታት ለኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ጥበቃና ደኅንነት ዘርፎች ውጤታማ ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ተግባራትን በማከናወን፣ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ አሻራ አሳርፏል። ኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ቀድሞ በመለየትና ምርምር በማካሄድ፣ የተለያዩ ክትባቶችን በማምረት እንዲሁም ለጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ውጤታማ ሲሆን መቆየቱን ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረጻ ላይ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶችን እንደ ግብዓት በማቅረብ፣ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ቀድሞ በማወቅ፣ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው የላብራቶሪ ምርመራ ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም የሙያተኞችን አቅም በመገንባት ውጤታማ ተግባራትን እንዳከናወነ አንስተዋል። በአሁኑ ወቅትም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ወረርሽኞችን አስቀድሞ የመተንበይና የመረጃ ፍሰትን የማዘመንና የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ኢንስቲትዩቱን በምሥራቅ አፍሪካ የሕዝብ ጤና ምርምርና ስልጠና ግንባር ቀደም ተቋም ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ የ100ኛ ዓመት በዓሉን ከዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያከብራል።
ትምህርት ቤቶችን በግብአት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው
Jul 16, 2026 100
ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፡-ትምህርት ቤቶችን በግብአት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመጪውን የትምህርት ዘመን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በቅድመ ዝግጅት ስራዎችም የአዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች በማስገንባት፣ የማስፋፊያና የጥገና ተግባራትን በማከናወን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። እስካሁንም ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአምስት ትምህርት ቤቶች 18 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና የጥገና ስራዎች ተካሂዷል ብለዋል። ከዚህ ውስጥም በመድሃኔ አለም የ1ኛና መለስተኛ ትምህርት ቤት ውሰጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ መከናወኑን በማሳያነት አቅርበዋል። በተጨማሪም የተማሪዎች መቀመጫ ፣ ወንበር ፣ጠረጴዛና የጥቁር ሰሌዳን የማሟላትና የጥገና ስራን ጨምሮ የትምህርት ቤቶችን ግቢ ጽዱ፣ ውብና ማራኪ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል። በዚህም መጪው አዲሱን የትምህርት አጀመማር ስኬታማ በማድረግ ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ጠቁመው መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑድርጅቶች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። የባሶ 1ኛ ደረጃና መለስተኛ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር መምህር ጎበዜ ንጉሴ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤታቸው የመማሪያ ክፍሎች እድሳትና የግቢ ማስዋብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ምቹና የተሟላ የመማር መስተማር ስራ እንዲኖር የሚያደረግ ነው ሲሉ አመልክተዋል። በከተማ አስተዳደሩ 57 የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሀገር አልፎ የአህጉራችን ኩራት ነው- ዶክተር መቅደስ ዳባ
Jul 16, 2026 200
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሀገር አልፎ የአህጉራችን ኩራት ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እየተከበረ ይገኛል። በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ የጤና ዘርፍ ተወካዮችና አጋር አካላት ተገኝተዋል፡፡ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፥ ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በሀገሪቱ የጤና ታሪክ ውስጥ ጉልህና ታሪካዊ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል። በኢንስቲትዩቱ ውስጥ የሚገኙ ተመራማሪዎች፣ የቅኝት ባለሙያዎች፣ የመረጃ ተንታኞች፣ የአደጋ ምላሽ ሰጪዎች እና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የሚጫወቱትን የላቀ ሚና አድንቀዋል። ተቋሙ ሀገሪቱ አስቸጋሪ የጤና ፈተናዎችን ባለፈችባቸው ወቅቶች ያሳየው ተጋድሎ ትልቅና የሚደነቅ እንደነበር አስታውቀዋል። በተለይ በኮቪድ-19 እና በተለያዩ አስጊ ወረርሽኞች ወቅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመተባበር የሰራውን ውጤታማ ስራ አንስተዋል። የላብራቶሪ ምርመራና የቅኝት ስራዎችን በበላይነት መምራቱን፣ እንዲሁም በሳይንሳዊ ትንተናዎች የታገዘ ፈጣን የድንገተኛ አደጋ ምላሽ በመስጠት ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አቅም በአሁኑ ወቅት ከሀገር ወሰን ማለፉን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ተቋሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ አህጉራዊ ኩራት መሆኑን አስገንዝበዋል። መንግሥት የጤናውን ዘርፍ ፍትሐዊነት ለማረጋገጥና ጥራትን ለማሻሻል በዋናነት በርካታ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ከገጠር እስከ ከተማ የጤና አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣የእናቶችንና ህጻናትን ጤና ማሻሻል እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። የሕዝቡን ተሳትፎ ማሳደግና ዜጎች በጤና ወጪ ምክንያት ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንዳይጋለጡ ለማድረግ የባለቤትነት ስሜት በመፍጠር የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድንን የማስፋፋት ሰፊ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ዓለም አዲስና ውስብስብ የጤና ሥጋቶች እንዳሉባት እያየን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ እነዚህን ውስብስብ ሥጋቶች ለመመከት አደጋን አስቀድሞ የሚለይ፣ በፍጥነት የሚያስጠነቅቅ፣ በሳይንስ የሚተነትንና በተቀናጀ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መገንባት መሆኑን በአጽንኦት ተስጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎቹን በታማኝነትና በብቃት መወጣት እንዲችል ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን የፖሊሲ፣ የአመራርና የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በሀረሪ ክልል በበጎ ፈቃድ ተግባራት 246 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ተደርገዋል - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
Jul 16, 2026 83
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል በ2018 የበጀት ዓመት በበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ246 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ተጠቃሚ መደረጋቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ። የሀረሪ ክልል ምክር ቤት 6ተኛ ዙር 5ተኛ አመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል። ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለፁት በበጎ ፈቃድ እና የህብረተሰብ አገልግሎት ስራዎች 66 ሺ 594 በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ197 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ግምት ያለው አገልግሎት እንደተሰጠም ተናግረዋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 246 ሺ 367 ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስና በመገንባት፣በደም ልገሳ፣ ለተማሪዎች ድጋፍ በማድረግና በመሳሰሉት ተሳትፎዎች ውጤተማ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።