ፖለቲካ - ኢዜአ አማርኛ
ፖለቲካ
ጨፌው በክልሉ በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በጥልቀት በመምከር የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል
Jul 18, 2026 708
አዳማ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ጨፌው በኦሮሚያ ክልል በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በጥልቀት በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ። የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ በአዳማ ገልመ ጨፌ ይጀመራል። የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ጉባኤውን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ጨፌው በቆይታው የክልሉ መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም፣ የ2019 ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት ይመክራል ብለዋል። በተጨማሪም የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ኦዲት ሪፖርቶችን መርምሮ፣ የ2019 በጀት ዓመት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስፈጸሚያ እንዲሁም ተጨማሪ በጀትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። ጨፌው የዳኞች ሹመትንም ያጸድቃል ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ ጉባኤው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እና በሀገራዊ ምክክር ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ጨፌው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ በተከናወኑ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ላይ በጥልቀት እንደሚመክርም አስታውቀዋል። የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በጠቅላይ ኦዲት የተሠሩ ሥራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች በጥልቀት ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። የ2019 በጀት ዓመት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስፈጸሚያ የሚውል በጀት ለጨፌው ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ዘርፉን በብቁ የሰው ኃይል ለማደራጀት፤ ተመልምለው ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ ዳኞች ሹመት በጨፌው እንደሚጸድቅም አክለዋል። በአዳማ ገልመ ጨፌ የሚካሄደው ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም አፈ ጉባኤዋ ጨምረው አመልክተዋል።
ሃገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በመፍታት ሰላምና ልማትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው
Jul 18, 2026 658
ደሴ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፡-እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ልዩነቶችን በመፍታት ሰላምና ልማትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ የደሴ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ገለጹ። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች ባሰባሰባቸው ስምንት አንኳር አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ የምክክር ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የጉባኤው መክፈቻ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በችግሮች ውስጥ እድሎች ያሉ በመሆኑ የምክክሩን ታሪካዊ እድል በመጠቀም የፀናች፣የለማችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል። ምክክሩን አስመልከቶ ኢዜአ በደሴ ከተማ ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌ አቶ መሀመድ ሰይድ እንዳሉት ፤ እየተካሄደ ያለው ምክክር ልዩነቶችን በመፍታት በሀገሪቱ ሰላምና ልማትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል። የተጀመረው ጉባኤ ምክክሮችን በማድረግ ቅድሚያ ለሀገር አንድነት፣ ሰላምና እድገት ለመስጠት ምቹ መደላድል እንዲኖር ከማድረግ አንፃር ተስፋ የሚጣልበት መሆኑንም ነው የገለጹት። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ መሀመድ አሊ በበኩላቸው፣ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ ሉዓላዊነቷን የጠበቀች እና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የገነባች ኢትዮጵያን ለማስረከብ የሚያስችል ነው ብለዋል ። በተጨማሪም ሀገራዊ ምክክሩ አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ጉባኤው ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ቅድሚያ ትከረት በመስጠት ሰላምን ለማጽናት የተሻለ አማራጭ እንደሆነም ተናግረዋል። የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ያለፈባቸውን ሂደትና እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ያደነቁት አቶ መሀመድ፣ ይህም ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የሚያመላክት መሆኑንም አስገንዝበዋል። ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ህብረ ብሄራዊ እንደነታችንና ሰላማችን ለማጽናት መሰረት የሚጥል ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እረህመት አየለ ናቸው። ምክክሩ በሀገሪቱ ለቆዩ እና ሲንከባለሉ ለመጡ ውስብስብ ችግሮቻችን መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን የደረሰበት ደረጃም የሚደነቅና ውጤታማ መሆን የሚያስችል ነው ብለዋል። ምክክሩ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግና ሀገራችንን የሚያጸና ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
በዞኑ ሰላምን ይበልጥ በማፅናት፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የበኩላችንን እንወጣለን
Jul 18, 2026 637
ጭሮ፤ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሰላምን ይበልጥ በማፅናት፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የበኩላችንን እየተወጣን ነው ሲሉ የዞኑ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ። ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በባለቤትነት እንዲጠብቅ በተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሥራ መሠራቱን የዞኑ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የጭሮ ከተማ አባገዳ ሐሺም አብደላ በሰጡት አስተያየት፤ በዞኑ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ዘላቂ በማድረግ ረገድ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የበኩላቸውን እየተወጡ ነው። ዞኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በግብርናው መስክ እያስመዘገበ ያለው ስኬት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ውጤት ለማስቀጠል በተለይ ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። የሸነን ዱጎ ወረዳ አባገዳ አህመድ አሚን በበኩላቸው፣ በአካባቢው ለሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ዋነኛው ምንጭ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የአካባቢውን ፀጥታ በትጋት በመጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም የልማት እንቅስቃሴው በየዓመቱ እያደገ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው፣ ኅብረተሰቡ የሰላምን ጠቀሜታ በመረዳት የሚጠበቅበትን እንዲወጣ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል። የሰላም ባለቤት ሕዝብ መሆኑን በመገንዘብ የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የመሰላ ከተማ የአገር ሽማግሌ ሼህ ሲራጅ መሐመድ ናቸው። እንደ አገር ሽማግሌና የሃይማኖት አባትነታቸውም ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ግንዛቤ በመስጠት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና አጠናክረው እንደሚወጡ ተናግረዋል። የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ዋቆ በበኩላቸው፣ በዞኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተሠራው የተቀናጀ ሥራ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል። በተለይ ወጣቱ የሰላምን ዋጋ ተረድቶ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ በዚህም በዞኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች እየተስፋፉና የግብርና ልማት ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አስገንዝበዋል።
ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ ከልማት ወደ ኋላ እያስቀረ ነው - አቶ ጌታቸው ረዳ
Jul 18, 2026 273
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ ከልማት ወደ ኋላ እያስቀረ ነው ሲሉ የስምረት ፓርቲ ሊቀ መንበር ጌታቸው ረዳ ገለጹ። ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ህዘብ ላይ የሚፈፅመውን አፈናና ጭቆና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል። አቶ ጌታቸው ረዳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርግ በተደራጀ መልኩ ልንታገለውና ድምፃችንን ልናሰማ ይገባል። ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ወጣቶችን ወደ ሱዳን መሸጥ ያቁም ያሉ ሲሆን ህገ ወጥ ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ከልማት ወደ ኋላ እያስቀረ ነው ሲሉም ገልጸዋል። አሁን ላይ የፕሪቶርያው ስምምነት ለትግራይ ህዝብ ያመጣው እፎይታ መገታቱን አስታውሰው የተገኘውን ለውጥ በመቀልበስ የጊዜያዊ አስተዳደሩን በመንፈቅለ መንግስት ማውረዱና ራሱ መሾሙን አንስተዋል። ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በዚህ ሳያበቃ ወጣቶችን በግዳጅ ለውትድርና እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን እናቶች ልጆቻቸው ከእቅፋቸው በመንጠቅ ወደ ጦር ካምፕ በማስገባትና እናቶች በማሰር ኢሰብአዊ ድርጊት እየፈፀመ ይገኛል ነው ያሉት። ሕገ ወጡ ህወሃት ለስልጣንና ለሀብት ብቻ ትኩረት በማድረግ ወጣቶችን ለስቃይ እየዳረገ እንደሚገኝ ገልፀው ቡድኑ እያስከተለ ያለውን ጥፋት በቃህ ሊባል እንደሚገባውም አመልክተዋል። ቡድኑ ወጣቶችን ያለፈቃዳቸው እያፈሰ ወደ ጦር ካምፕ ከማስገባት በተጨማሪ ለሱዳንና ለኤርትራ እየሸጠ እንደሚገኝ ገልፀው ይህም ለሰብዓዊ መብት የማይጨነቅ አምባገነን መሆኑን የሚሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት የዳረገ የጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርቷል
Jul 17, 2026 432
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ) ፦ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ሻዕቢያን ጨምሮ ከተለያዩ ሕገ-ወጥ ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ የጥፋት ተግባር ላይ በመሰማራት ጠላትነቱን አረጋግጧል ሲሉ የትግራይ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድርና የዓረና ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ አስራት ገለጹ። የትግራይ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር እና የዓረና ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ አስራት በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ላይ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸውም ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ፖለቲካዊና ወታደራዊ መሪዎች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደ ጎን በመተው፣ በስምምነቱ መሰረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳይሠራ በማድረግና በማፍረስ የክልሉን ሥልጣን በኃይል ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ለሥልጣን ሲል ከትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ከሻዕቢያና ከሌሎች የውጭና የሀገር ውስጥ ቡድኖች ጋር በመተባበር ለሌላ ግጭት እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ሻዕቢያ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት ይጥራል ያሉት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ፤ ለዚህ ደግሞ ቀደም ብሎ በክልሉ የፈጸመው ጭፍጨፋ እና ያስከተለው ውድመት ማረጋገጫ ነው ብለዋል። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሻዕቢያ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት የነበረውን ሕልም እንዳከሸፈበት ተናግረው፤ ስምምነቱ ሲፈረምም 'ተሰናክለናል' ሲል በአደባባይ መግለጹን አስታውሰዋል። ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን አሁንም ትግራይን የግጭት ማዕከል ለማድረግ ከተለያዩ ሕገ-ወጥ ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይን ሕዝብ ለመጉዳት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል። ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከውጭ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመስረት ሥልጣን ለፌዴራል መንግሥት ብቻ መሆኑን እንደሚደነግግ ያስታወሱት አቶ ገብሩ፤ ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ከኤርትራ፣ ከሱዳን እና ከሌሎች ሀገራት ጋር እያደረገ ያለው ግንኙነት ሕጋዊ መሠረትና አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል። ይህ ሕገ-ወጥ ቡድን ካለፈው ስህተቱ መማር ያልቻለና የማይማር መሆኑን ጠቁመው፤ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ከሻዕቢያ ጋር በመተባበርና ጥምረት በመፍጠር እኩይ ድርጊቶችን እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል። በተግባር ተፈትነው ለውድቀት የተዳረጉት እነዚህ ኃይሎች፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካም ሆነ የርዕዮተ-ዓለም ለውጥ ሳያደርጉ ባረጀ አስተሳሰባቸው መጓዛቸው ለትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ ሊያስገኝ እንደማይችል አስረድተዋል። ሕገ-ወጡ ቡድን ባወጣው ሕገ-ወጥ አዋጅ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ በከባድ ቀውስና በደል ውስጥ እንደሚገኝና የትግራይ ወጣትም ሀገሩን ትቶ እየተሰደደ መሆኑን ተናግረዋል። ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ካለፈው የአፋኝነቱ፣ የጭቆና እና የአምባገነንነት ተግባሩ ባደረሰው በደል ያልተጸጸተ መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ደግሞ ዝርፊያን እና ቅሚያን መሠረት ያደረገ አስተዳደር በመዘርጋት የክልሉን ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ መሆኑን አስረድተዋል። ወጣቶችን በማፈን እና ታጣቂዎችን ወደ ሱዳን በመሸጥ ገቢ እየሰበሰበ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህም የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ መገለጫዎች በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል። መላው የትግራይ ሕዝብ እያደረገ ያለውን ሰላማዊ ትግል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለትግራይ ችግር ዋና መፍትሔው ወደ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መመለስ መሆኑን ጠቁመዋል። ነገር ግን ቡድኑ በብዙ መንገድ ተጠያቂ የሚያደርጉት በርካታ በደሎችን ማድረሱና በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ በመዘፈቁ ምክንያት ሰላምን ቀዳሚ ምርጫው ያደርጋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። ሕገ-ወጡ ቡድን በፈጸማቸው ተደጋጋሚ ድርጊቶች ምክንያት ለሕግ ተጠያቂ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም አስረድተዋል።
በነገው እለት በአዲስ አበባ ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ
Jul 17, 2026 397
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 10/ 2018 (ኢዜአ)፦ሰልፉ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል። በትግራይ ክልል እየተባባሰ የመጣውን ቀውስ ለመቃወምና ለማስቆም እንዲሁም ለፌደራል መንግሥትና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ''አፈሳ ይቁም ሰላም ይስፈን'' በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከጥዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፉ ይደረጋል። ሰልፉ ተጀምሮ እስከ ሚጠናቀቅበት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ። በዚህም መሰረት:- ከመገናኛ በ22 አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ ቅ/ዑራኤል አደባባይ በቦሌ መንገድ ወደ መስቀል አደባባ ኦሎምፒያ አደባባይ ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ መስቀለኛ ለቀላል ተሽከርካሪ ጥላሁን አደባባይ ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ መስቀል ለገሀር መብራት ከለገሀር ቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታዲዮም ለገሀር ቴሌ ማቋረጫ ከአራት ኪሎ ወደ መሰቀል አደባባይ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ከካሳንቺስ በመቅረዝ ሆስፒታል ወደ መስቀል አደባባይ መቅረዝ ሆስፒታል አጠገብ ከአምባሳደር ቴአትር ወደ መስቀል አደባባይ ሐራምቤ መብራት የሚወስዱ መንገዶች ከንጋቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ መንገዶቹ ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ። ከዛሬ ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመስቀል አደባባይና በዙሪያው ባሉ መንገዶች ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ተሽከርካሪ ለአጭርም ሆነ ረዥም ሠዓት ማቆም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በመጠገን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል ነው
Jul 17, 2026 305
ሀዋሳ፤ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በመጠገን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል መሆኑን ምሁራን ገለጹ። በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክር ታሪካዊ ዕድል ሆኖ መጥቷል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተቋቁሞ ከዝግጅት እስከ ምክክር ምዕራፍ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ በአሁኑ ወቅት አካታች የሆነ የምክክር ሂደት እያከናወነ ይገኛል። በኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎች ላይ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የማጠቃለያ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። አጠቃላይ የምክክር ሂደቱንና ጉባኤውን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በመጠገን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን አንስተዋል። በዩኒቨርሲቲው የስነዜጋና ስነምግባር መምህር ብሩክ ደስታ፤ ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ የሰነቅንበት የጋራ እጣ ፋንታችን ነው ብለዋል። በመሆኑም ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት ለዓመታት የዘለቀው የምክክር ሂደት በውጤታማነት እንዲደመደም የሁላችንም ቅንንት፣መሻትና ለዘላቂ ሰላም መትጋት የግድ ነው ሲሉ አንስተዋል። ለምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎችን በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው የኢትዮጵያን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ አንኳር ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል። ምክክሩ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር ካለው ፋይዳ በተጨማሪ፣ የቆዩ ቁርሾዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት መፍትሄ ይሆናል ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር)፤ በምክክር ችግሮችን የመፍታት ባህልን ማዳበር ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይና የስልጣኔ መገለጫም ጭምር መሆኑን አንስተዋል። የሀገር ግንባታ ሂደት የሚሳካው በሰለጠነ ውይይትና ህብረ ብሔራዊ ሀገራዊ አንድነትን በማፅናት መሆኑን ገልጸው፥ታሪካዊ እድል የሆነውን ምክክር ስኬታማ ለማድረግ በሃላፊነት ስሜት መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መሰረት ጥሏል
Jul 17, 2026 430
ሆሳዕና፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላምና በልማት ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው የመስራት ባህል እንዲያዳብሩ ማድረጉን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዳሉት፤ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው አሳታፊ ስርአት በህዝብ ይሁንታ የተመሰረተ መንግስት በማዋቀር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ይረዳል። ሂደቱም የበለጸገችና የተረጋጋች ሀገርን ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንካራ መሰረት እንደሚሆን አስገንዝበዋል። በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዳንኤል ሀንዲኖ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠረው አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለሀገር ሰላምና ልማት ተቀራርቦ መስራታቸው እንዲጠናከር አድርጓል። ይህም ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ዕድገት ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከመፈራረጅና ከቂም በቀል ዕሳቤ ወጥተው ለትብብርና ለሰለጠነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የዴሞክራሲ ተቋማት አሰራር እና የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል ተአማኒ፣ ጠንካራና የማስፈጸም እቅማቸው እንዲጨምር መደረጉ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ግጭት ጥናት መምህር ጌታሁን አበራ በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግስት የመድበለ ፓርቲ ስርአትን በማስፋት ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ተቀራርብው የሚሰሩበትን አውድ መፍጠሩን ተናግረዋል። ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ከፍተኛ የሀላፊነት ቦታ ላይ ጭምር በቅንጅት በመስራት እያከናወኑት ያለው ተግባር በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል። በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ መንግስት ምቹ ምህዳር ከመፍጠር ባለፈ የተቋማትን የመፈጸም አቅም በማጠናከር የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ መሰራቱን አንስተዋል። በተለይ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት መጠናከራቸው ዴሞክራሲን በማጠናከር የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል።
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ረቂቅ አዋጆችን እና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ
Jul 17, 2026 384
ሀረር፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት አስረኛ መደበኛ ጉባዔ ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ። ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የሀረሪ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲን የሀረሪ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ በሚል ስያሜ እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል። ማሻሻያ አዋጁ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ይጠራበት የነበረውን የሀረሪ ብዙሃን መገናኝ ኤጀንሲ ስያሜ ከመቀየር ጀምሮ ለውጥ የተደረገበት ነው። የተቋሙን ሥልጣንና ተግባራት የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ተቋማት በአሁኑ ወቅት ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በብቃት፣ በጥራትና ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል በብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ደረጃ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ ማድረጉ እንዳስፈለገ ተገልጿል። አዋጁ ከጸደቀበት ከዛሬ ጀምሮ የሀረሪ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንደሚሆን በአዋጁ ተቀምጧል። ምክር ቤቱ የቀረበለትን የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅም አጽድቋል፡፡ አዋጁም ዜጎች መብትና ግዴታቸውን ተረድተው የሚያጋጥሟቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። እንዲሁም ምክር ቤቱ የሶስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመትም አጽድቋል። ምክር ቤቱም ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስድስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት አስረኛ መደበኛ ጉባዔ አጠናቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀመረ
Jul 17, 2026 418
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምሯል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የከተማ አስተዳደራችንን የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምረናል ብለዋል። ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ በበጀት ዓመቱ ለመፈፀም ያስቀመጥናቸውን ግቦች፣ እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዳችን ማጠቃለያ ዓመትም በመሆኑ ከባለፉት 5 ዓመታት አፈፃፀም ጋር አያይዘን የምንገመግም ይሆናል ነው ያሉት። እንደሚታወቀው ባለፉት 5 ዓመታት ያቀድናቸውን ስትራቴጂክ ግቦች በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር በታማኝነትና በቅንነት ያለ እረፍት 24/7 ሰርተን በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል ሲሉም ገልጸዋል። በተለይም መዲናችንን አዲስ አበባን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች አውጥተን የልማት እና የሰላም ማዕከል እንድትሆን አድርገናታል ብለዋል። እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ፅዱ፣ አረንጓዴና ውብ እየሆነች በመምጣቷ የዓለምን ትኩረትን ስባለች ሲሉ ጠቁመዋል። በእርግጥ ከስኬቶቻችን ባሻገር ዛሬም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች አሉብን። በተለይ የአመራራችን የውጤታማነት ልዩነቶች፣ በከተማችን የሚታዩ የኑሮ ውድነት እና ፍልሰት ችግሮችን በጥልቀት የምንገመግም ይሆናል ነው ያሉት። በርካታ ስኬቶችን ብናስመዘግብም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት እና ከብልፅግና ግባችን አንፃር ብዙ ስለሚቀረን ስኬቶቻችንን ማስፋት፤ ተግዳሮቶች ደግሞ ለይተን መፍታት በቀጣይ በጀት ዓመት የላቀ ስኬት ማስመዝገብ የግምገማችን ማዕከል ይሆናል ብለዋል። በቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችም ላይ እንወያያለን ሲሉም በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ እሳቤዎችን በተግባር በመተርጎም ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
Jul 17, 2026 451
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ አመራሩ የብልፅግና ፓርቲ እሳቤዎችን በተግባር በመተርጎም ውጤታማ የመንግሥትና የፓርቲ ተግባራት ማከናወኑን በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ። አቶ ጌቱ ወዬሳ በተጠናቀቀው በጀት አመት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በሰጡት መግለጫ በ2018 በጀት ዓመት ፓርቲውን በአሰራር፣ በሰው ሀይል እና በአደረጃጀት የማጠናከር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። አባልና አመራሩ በፓርቲው እሳቤዎችና አቋሞች ላይ የጠራ ግንዛቤና አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ በኩል አበረታች ስራዎች መሰራታቸውንም አክለዋል። ገዥ ትርክትን ለማስረጽ በተሰራ ስራ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው የአመራሩና የአባላት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በጉልህ የታየበት በመሆኑም ተደራራቢ ተልዕኮዎች ስኬታማ መሆናቸውን አብራርተዋል። አባላት የተግባር ተልዕኮዎችን ውጤታማ በማድረጋቸው ለክልሉ ፈጣን ዕድገት ጉልህ አሻራ ማሳረፍ መቻሉን ገልፀዋል። የፓርቲውን እሳቤዎች በተግባር በመተርጎም በየዘርፉ የተመዘገቡ ድሎች በቁርጠኛ አመራር የተመሩ፣ የሁሉም አሻራ ያረፈባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ጨምሮ በርካታ ግቦች ማሳካት መቻሉን ጠቁመው የሴቶችንና የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራ ስራም ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት። በቀጣይም በአገልግሎት አሰጣጥ የህዝብን እርካታ ማሳደግ እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን ከማስወገድ አንፃር በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል። አመራሩም የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የብልጽግና ግቦች እንዲሳኩ በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች
Jul 16, 2026 1268
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች በሀገሪቱ በነበራቸው የሥራ ቆይታ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ። አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ቆይታ፣ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ጊዜ ያጠናቀቁት የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በቆዩባቸው አራት ዓመታት የሀገሪቱን ውብና የተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች መጎብኘት በመቻላቸው እጅግ አስደሳች ጊዜ አሳልፈዋል። ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ ለረጅም ዓመታት ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በኢኮኖሚና በንግድ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ሰፋፊ ዕድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በቆይታቸውም በርካታ የኦስትሪያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲገነዘቡ የጋራ አጋርነትና የንግድ ትስስር እንዲመሰርቱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል። ይህ ግንኙነት ወደፊት ይበልጥ እንደሚጠናከር ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ጊዜ ያጠናቀቁት የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው፤ ላለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ያደረጉት ቆይታ እጅግ ፍሬያማና ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል። በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የባህል ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳና ምልመላ በሕዝቡ ላይ ሰብዓዊ ጉዳትና ጉስቁልና እያደረሰ ነው
Jul 16, 2026 750
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳና ምልመላ በሕዝቡ ላይ ሰብዓዊ ጉዳትና ጉስቁልና እያደረሰ መሆኑን የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አስታወቀ። ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ህዘብ ላይ የሚፈፅመውን አፈናና ጭቆና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደሚያካሂድ ምክር ቤቱ ገልጿል። የምክር ቤቱ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ከበደ አሰፋ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ''አፈሳ ይቁም፥ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ሃሳብ ሰላማዊ ሰልፉ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል። ይህንን ሰልፍ የጠራው የትግራይ የሰላምና የለውጥ ምክር ቤት ሲሆን፣ የሰልፉ አስተባባሪዎች ለዝግጅቱ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሕጋዊ ዕውቅና እና ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ሰላማዊ ሰልፉም በክልሉ በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሚፈጸመውን እኩይ ተግባር ለማጋለጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። ሕገ-ወጥ ቡድኑ በትግራይ ክልል ወጣቶች ላይ በሚፈፅመው አስገዳጅ ወታደራዊ ምልምላ እና እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ጉስቁልና እንዲሁም እያደረሰ ያለውን ሥነ-ልቦናዊ ጫና በፅኑ የሚቃወም መሆኑን አንስተዋል። በክልሉ ያለአግባብ ታስረው ለሚገኙ ንጹሀን ዜጎች በተለይም ለእናቶች ድምፅ በመሆን የሚደርስባቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብም የሰልፉ ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል። ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ወጣቶችን በግዳጅ ለውትድርና በመመልመል ሕዝብን ለዳግም እልቂት ለመዳረግ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል። በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ሕግ እንዲያስከብር እንዲሁም ቡድኑ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲያደርግ መልዕክት እንደሚተላለፍም ተናግረዋል። በዕለቱ በሚካሄደው ሰልፍ ላይ በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ሁሉም ሰላም ወዳድ የኢትዮጵያ ዜጎች በነቂስ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። የትግራይ ክልል ሕዝብም በዕለቱ ከቤቱ ባለመውጣት የተቃውሞው ተካፋይ እንዲሆንና ድጋፉን በተግባር እንዲገልጽ አስተባባሪዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ነው
Jul 16, 2026 728
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባኤ ከትናንት ረቡዕ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ ጀመረ ሲሆን፤ ከወረዳ እስከ ክልል፣ ከፌዴራል እስከ ውጭ ሀገራት የተውጣጡ የህዝብ ወኪሎችም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየመከሩ ነው። በጉባኤው አራት ሺህ የህዝብ ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ በሀገር ግንባታ፣ በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በምርጫ ሥርዓትና ውክልና፣ በፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) አስተዳደር፣ በሃይማኖት ጉዳዮች፣ በተቋማት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በአርሶ አደርና አርብቶ አደር ጥያቄዎች እንዲሁም በሙስና፣ በመልካም አስተዳደርና በሰላም ግንባታ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጉባኤው ዐበይት አጀንዳዎች የኢትዮጵያን የዘመናት አለመግባባቶች በመፍታት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ናቸው። በዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት በዜጎች መካከል የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል። የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን፤ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ዜጎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ስልጡን ምክክር ለማድረግ ከወሰኑበት ጊዜ ጀምሮ ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። የሀገራዊ ምክክሩ ዐበይት አጀንዳዎች የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተቀረጹ በመሆናቸው ውስብስብ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል። የዩቡንቱ ወጣቶች ለሰላም ጥምረት ሰብሳቢና የጣምራ ማህበራዊ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ይርጋለም፤ የጉባኤው አጀንዳዎች የወጣቶችን የተሻለ ሀገር የመገንባት ፍላጎት ያገናዘቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ወጣቶች በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊ ልየታ ሂደት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና ያቀረቧቸው ሃሳቦች በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ስር በንዑስ አጀንዳነት መካተታቸውን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርቢርሳ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የወጣቶችን ተሳትፎ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል። በጉባኤው የተካተቱት ዐበይት አጀንዳዎች ለዘመናት የቆዩ የተዛቡ ትርክቶችን በማረም፣ የወጣቶችን ዘላቂ ሰላምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም፤ ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊ ልየታ ወቅት ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና በዋናው ጉባኤም በወኪሎቻቸው አማካኝነት ገንቢ ሚና መጫወት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እናትዓለም እንዳለ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ለዘመናት በዘለቁ ግጭቶች ሴቶች ቀዳሚ ሰለባ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በመሆኑም በዋናው ጉባኤ የሕግና ፍትሕ፣ የሰብዓዊ መብትና የፖለቲካ ተሳትፎን የተመለከቱ የሴቶች አጀንዳዎች መለየታቸው ለችግሮቻቸው መፍትሔ እንደሚያመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለዘመናት የቆዩና የማያግባቡ ጉዳዮችን በጥልቀት በመምከር ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደሆነ ገልጸዋል። አቶ ያሬድ ደምሌ እንደገለጹት፤ በምክክር ጉባኤው ሀገርን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈሉ የጦርነትና የግጭት ምንጮችን በሃሳብ የበላይነት መፍታትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ይቻላል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ኃይሌ ባህረ በበኩላቸው፤ ምክክሩ የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚያስቀጥልና ጠንካራ መግባባትን የሚፈጥር ቁልፍ ዕድል መሆኑን አስረድተዋል። የኢትጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትና ዕድገትን በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ልማትን የሚያፋጥን ድልድይ መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች አሰናበቱ
Jul 16, 2026 821
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕን (ዶ/ር) እና የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክን አሰናብተዋል። አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ቆይታ፣ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸዋል። የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቆይታቸው የኢትዮጵያና ኦስትሪያን ታሪካዊና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል። ዲፕሎማሲያዊ ቆይታቸው ፍሬያማ እንደነበር ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ ለተደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በተመሳሳይ፣ ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ፤ የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ስኬታማ ቆይታ እንደነበራቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የተከናወኑ የትብብር ስራዎች፣ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ
Jul 16, 2026 827
ሀረር፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፡- የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ምክር ቤቱ እያካሄደ ያለው 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን ነው። ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የምክር ቤቱ ጉባኤ የ2018 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ አካላት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል። ለጉባዔው በቀረበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ የምክር ቤቱ አባላት ከተወያዩበት በኋላ ያፀድቁታል ተብሎ ይጠበቃል። የክልሉ ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል። በተጨማሪም የክልሉ መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል። ምክር ቤቱ የሚቀርቡለትን የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶንች ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂክ ትብብር ለማስፋት ቁርጠኛ ነው
Jul 15, 2026 1901
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂክ ትብብር ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም በአውሮፓ ሕብረትና በአፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ላይ በመምከር፣ በጋራ ጥቅሞችና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል። በተጨማሪም በቀጣናዊ እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ተመስርተው ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ይበልጥ ለማሳደግና ለማስፋፋት በሚያስችሉ መንገዶች ላይ መክረዋል። በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን የዘመናት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር፣ እንዲሁም በጋራ ጥቅም እና በአጋርነት ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ካያ ካላስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ሕብረቱ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ስትራቴጂክ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ግብዓቶች የተገኙበት ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር የነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያንና የሕብረቱን አጋርነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሚያስችል ገልጸዋል። አያይዘውም፣ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የሚኖረውን የኢንቨስትመንት፣ የዲጂታል አስተዳደር፣ የታዳሽ ኃይል እና የሌሎች ዘርፎች ትብብር የበለጠ ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ፍላጎት እያደገ መምጣቱም የንግድ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግና ሥራዎቻቸውን ለማስፋፋት ትልቅ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ዕድልም ለሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚነት ለማዋል እንደሚሰራ ተገልጿል። የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያግዙ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት በዲጂታል አስተዳደር ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ አመላክተዋል። በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ በመስራት ለጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ አስረድተዋል። ሕብረቱ በአገሪቱ የጥሬ ዕቃዎች ላይ እሴት መጨመርን በመደገፍ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲስፋፋ እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል። ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራ መስፋፋት የሚኖረውን ወሳኝ ሚና ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ተምሳሌታዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው
Jul 15, 2026 1548
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ተምሳሌታዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኝ የፓርላማ መረጃ ደኅንነት ፎረም ተሳታፊ እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አካውንታቢሊቲ ላብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማክዶናልድ ሌዋኒካ ገለጹ። ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን ለመፍታት፣ እንዲሁም ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በይፋ ተጀምሯል። የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አካውንታቢሊቲ ላብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማክዶናልድ ሌዋኒካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን የሚገነባ የዴሞክራሲ መንገድ ነው። አክለውም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮች ላይ ለመመካከርና መፍትሔ ለመስጠት በጉባኤው መሰባሰቡ ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ወደ መካሄድ መሸጋገሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት፣ የበርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ማግኘታቸው የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
በሲዳማ ክልል የህዝብና የአመራር አቅምን በማቀናጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማሳካት ተችሏል
Jul 15, 2026 1421
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል የህዝብና የአመራር አቅምን በማቀናጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማሳካት መቻሉን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ገለጹ፡፡ ''ከምርጫ ድል ማግስት ጠንካራ መንግስት'' በሚል መሪ ቃል የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጻምን የሚገመግም መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በወቅቱ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የአመራርና የህዝብ አቅምን በማቀናጀት የግብርና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግና ኢንዱስትሪውን በተገቢው በመምራት የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ተችሏል። በተለይ የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግን ጨምሮ ገበያ ተኮር ምርቶችን የማምረት ግብ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፣ በየደረጃው ያለው አመራር ተገቢውን ድጋፍ በማድረጉ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡ ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በጉድጓድ ውሃ ማልማት መጀመሩና መሬት ጾም እንዳያድር መደረጉም ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አያይዘው ገልጸዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳካትም ለክህሎት መር ስልጠና እንዲሁም የከተማና የገጠር የልማት አቅምችን ወደ ውጤት መቀየር ላይ በቅንጅት መሰራቱን አስረድተዋል። የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማቶች ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፋይዳቸውን ለማጉላትም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ጠቅሰዋል።፡ መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ወደ ሥራ የገቡ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ቀደም ሲል ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስችሏል ብለዋል፡፡ በተከናወኑ ሥራዎች በሁሉም ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት አመራሩ ተናቦ በቁርጠኝነት ከሰራ ያቀዱትን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል። በግምገማ መድረኩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የበጀት ዓመቱ የፓርቲና የመንግስት ዕቅድ አፈጻፀም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ- እናት ሙዶ አኮ
Jul 15, 2026 1139
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ከደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የካራ ማህበረሰብ ተወካይ እና የሰላም እናት ሙዶ አኮ በሀገራዊ የምክክር የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል። በመክፈቻ ጉባኤው ከደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የመጡት የካራ ማህበረሰብ ተወካይ እና የሰላም እናት ሙዶ አኮ፣ በዚሁ ወቅት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። እናት ሙዶ የኢትዮጵያ ሴቶች እና እናቶች ለዘመናት በታሪክ ሂደት ውስጥ ተሳትፏቸው የነበረው በደልን በመቀበል እና ሀዘንን በመጋራት ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም እናቶች ለዘመናት በሰላም እጦት የደረሰባቸውን መከራ በንግግራቸው ጠቅሰዋል። ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጻቸውን ለመስማት በመጥራቷ የኢትዮጵያ ሴቶችን ድምጽ በመወከል፣ ታሪካዊውን የምክክር መድረክ በክብር መቀላቀላቸውንም በደስታ ተናግረዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ያላቸውን ተስፋ እና ሙሉ እምነት አንጸባርቀዋል። እናት ሙዶ አኮ፣ ሀገሪቱ ያሳለፈችው ፈታኝ ጊዜ የጋራ መግባባት በመጥፋቱ እንደሆነ በማሳየት ለነገ የምንተወው ተስፋ መሠረቱ የዛሬው መደማመጥ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ መኖሪያ እንደሆነች ያነሱት እናት ሙዶ፣ በልባችን የያዝነውን የቀድሞ ቁጣ እና የቂም ቋጠሮ በመፍታት፣ ተመካካሪዎች በሙሉ ለሀገራዊ ለውጥ በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። ማን ያሸንፋል ከሚል አስተሳሰብ በመውጣትም፣ ኢትዮጵያን አሸናፊ በሚያደርግ የጋራ ዓላማ ዙሪያ መሰለፍ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል። የምክክር መድረኩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ብልፅግና ቁልፍ ምዕራፍ እንደሚሆንም ተናግረዋል። በመድረኩ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ያሉት እናት ሙዶ፥ የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ የመገንባት ትልቅ አደራችንን እንወጣ ብለዋል።