ዓለም አቀፍ ዜናዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ዜናዎች
የአፍሪካ ህብረት እና ሳዑዲ አረቢያ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
Feb 23, 2026 435
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና ሳዑዲ አረቢያ በሰላም፣ ልማት እና ዲፕሎማሲ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታወቁ። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሌድ ቢን አብዱልከሪም ኤል- ከሀርጂ(ኢ/ር) ከተመራ ልዑክ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል። የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አፍሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ለረጅም ጊዜ የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ትብብሩ በጥልቅ የባህል፣ የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አውስተዋል። ሳዑዲ አረቢያ በአፍሪካ ያላትን ዘላቂ ትብብር እና በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን ኢንቨስትመንት አልፎም በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ያላትን ገንቢ ሚና አድንቀዋል። ሳዑዲ አረቢያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመቀናጀት በሊቢያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች እያሳየች ያለውን የዲፕሎማሲ ድጋፍ እና ተሳትፎ አዎንታዊ መሆኑን አመልክተዋል። የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሌድ ቢን አብዱልከሪም ኤል- ከሀርጂ በበኩላቸው የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ በልማት፣ በሰላም እና በባለብዙ ወገን ትብብር ያለውን የመሪነት ሚና አንስተዋል። ሳዑዲ አረቢያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ልማት፣ ሰላም፣ ደህንነት እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል። ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ህብረትና ሳዑዲ አረቢያ ያላቸውን ግንኙነት በጋራ መከባበር መንፈስ፣ በወዳጅነት እና በስትራቴጂካዊ አጋርነት ላይ በመመስረት የበለጠ ለማጠናከር የጋራ ፍላጎት ማሳየታቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና የፈጠረውን የንግድ ትስስር ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው
Feb 21, 2026 698
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የፈጠረውን የንግድ ትስስር ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም በመንግሥታትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለ አጋርነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ። የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የስምምነቱ ትግበራ የንግድ መሰናክሎችን በማስቀረት የሀገራትን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ነው። እስካሁን 50 ሀገራት ፈርመው ያጸደቁት ይህ የንግድ ቀጣና፤ በዲጂታል የኢኮኖሚ ዕድገት የፋይናንስ ቴክኖሎጂን በማስፋት የአኅጉሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ በማዘመንና የገንዘብ ዝውውርን በማቀላጠፍ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የአሰራር ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተዳራሽ ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዘርግቷል የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲሱ ገጽታ፤ ከአማራጭ ማጣት ወደ መዳረሻዎች ብዛት በኢትዮጵያ ለግል ዘርፉ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ኢኮኖሚው እየተነቃቃ ነው የአፍሪካን የተፈጥሮ ሃብትም በተሻለ የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት በማልማት የመሰረተ ልማት፣ የዋጋ ግሽበትና የንግድ መሰናክሎችን ለመቀነስ አይነተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስረድተዋል። በዚህም አባል ሀገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን በማፋጠን የእርስበርስ የንግድ ልውውጥን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የፈጠረውን ዕድል ለመጠቀም የግሉ ዘርፍና የአባል ሀገራት መንግሥታት የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት መሰረትም የአባል ሀገራት ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃ የኢንቨስትመንት ጥበቃ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል። የስምምነቱ የኢንቨስትመንት ጥበቃም የአፍሪካን በመተማመን ላይ የተመሰረተ የእርስበርስ ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።
ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ታሪካዊ አጋርነት
Feb 16, 2026 689
የኢትዮጵያ እና ቱርኪዬ ግንኙነት ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። የአፍሪካ ጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ኦቶማን ኢምፓየርን ጨምሮ በታሪክ ከመካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ነበራት። ኦቶማን ኢምፓየር ለዘመናዊቷ ቱርክዬ መሰረት ጥሎ አልፏል። በ20ኛ ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የተጀመረው የሀገራቱ ወዳጅነት በዲፕሎማሲ እና ንግድ ልውውጥ ላይ የተመረኮዘ ነው። ቱርክዬ አፍሪካን እንደ ስትራቴጂካዊ አጋር የምትቆጥር ሲሆን አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ቁልፍ አህጉራዊ ተቋማት የሚገኙባት እና የአፍሪካ መዲና ኢትዮጵያ የዚህ ትብብር አካል ናት። ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1896 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የመጀመሪያ የኦቶማን-ቱርክዬ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እ.አ.አ በ1912 በሐረር ከተማ ተከፍቷል። ቱርክዬ ከሰሃራ በታች የመጀመሪያውን ኤምባሲ የከፈተችው በኢትዮጵያ ሲሆን ወቅቱም እ.አ.አ በ1926 ነበር። ኢትዮጵያ በቱርክዬ ኤምባሲዋን የከፈተችው እ.አ.አ በ1933 ነው። ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ግንኙነት ከፍተኛ እድገት ያሳየበት ነው። ኢኮኖሚ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት ምሰሶ እንደሆነ ይጠቀሳል። የቱርክዬ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በግንባታ እና በግብርና ማቀነባበሪያ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ። ቱርክዬ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ሀገራት መካከል በዋናነት ትጠቀሳለች። የሀገራቱ የንግድ ግንኙነትም እየዳበረ መጥቷል። ከኢኮኖሚ ባሻገር ፖለቲካ፣ ደህንነት፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ እና ባህል ሌሎች የትብብር መስኮች ናቸው። ባለፉት 10 ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል የከፍተኛ ባለስልጣናት የጉብኝት ልውውጦች ተደርገዋል። የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን እ.አ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ጉብኝቱ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትስስር ማጠናከርን ያለመ ነው። እ.አ.አ በ2017 የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በቱርክዬ ጉብኝት በማድረግ ኢትዮጵያን በመወከል በቱርክዬ-አፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ በ2021 በቱርክዬ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በወቅቱ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች የትብብር ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወሳል። ውሃ፣ ወታደራዊ ትብብር እና ፋይናንስ ከስምምነቶቹ ትኩረቶች መካከልም ይገኙበታል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተደረገው ኢትዮጵያና ቱርክዬ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 125ኛ ዓመት ላይ መሆኑ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት የተፈረሙት ስምምነቶች የግንኙነቱን መጠናከር እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል። ለኢትዮጵያ የልማት እና መረጋጋት ጉዞ ቱርክዬ የምታደርገውን ድጋፍም አድንቀዋል። የቱርክዬ መንግስት እና ህዝብ ያደረገልንን የወሳኝ ጊዜ ትብብር ሀገራችን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በነበራቸው ቆይታ። የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እ.ኤ.አ በ2021 በቱርክዬ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በወቅቱ አዲስ የተገነባውን የኢትዮጵያ ኤምባሲም መርቀዋል። የቱርክዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እ.አ.አ በ2024 ኢትዮጵያን በመጎብኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። የከፍተኛ ባለስልጣናቱ ጉብኝት የሀገራቱን የግንኙነት መጠናከር የበለጠ የሚያጎለብቱም ናቸው። ኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ፣ መሰረተ ልማት፣ የንግድ ብዝሃነትን ማስፋት፣ መከላከያ እና ደህንነት፣ ቱሪዝም እና ባህል ሀገራቱ ትብብራቸውን ሊያሰፉባቸው እየሰሩባቸው ከሚገኙ መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ አጋርነት በጋራ ፍላጎቶች፣ ተራማጅ በሆኑ ሀሳቦች፣ በጋራ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና እየተለወጡ ያሉ የዓለም እውነታዎችን ባማከለ ሁኔታ የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል። በልማት ጎዳና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ከአፍሪካ ጋር ያላት ትስስር የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር የበለጠ ጥልቀት የሚሰጥ ነው። ሁለቱ ሀገራት በፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘው ቀጣናዊ እና የዓለም ምህዳር ውስጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩም ይገኛሉ።
የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ አጋርነታቸውን ለማደስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ
Feb 16, 2026 700
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ):- የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የአህጉሪቱን የፋይናንስ መዋቅር ማጠናከርን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን አጋርነት በአዲስ መልክ ለማደስ እንደሚሰሩ አስታወቁ። 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተካሂዷል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ(ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል። የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ባንኩ ለአፍሪካ ቁልፍ የትኩረት መስኮች እያደረገ ያለውን ጠንካራ ድጋፍ ያደነቁ ሲሆን ለአፍሪካ ልማት ፈንድ 11 ቢሊን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን መልካም የሚባል እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል። ሊቀመንበሩ እና የባንኩ ፕሬዝዳንት ከእዳ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የደህንነት ፈተናዎች ባለፈ የፋይናንስ አቅርቦት የአፍሪካ አበይት ፈተና መሆኑን በምክክራቸው ወቅት ገልጸዋል። ሁለቱ ወገኖች የፕሮጀክት ዝግጅት ትብብርን ለማጠናከር፣ የአንድ ትሪሊን የአሜሪካን ዶላር የአፍሪካ ካፒታል ማሰባሰብ፣ የአፍሪካ የብድር ምዘና ኤጀንሲን ማጎልበትና ጠንካራ የአፍሪካ የፋይናንስ ስርዓት መገንባት ጉዳዮች ላይ መክረዋል። በውይይቱ የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ አጋርነታቸውን በአዲስ መልክ ለማደስ ተሠማመተዋለ። በዓመት ሁለት ጊዜ ለመወያያት እና በአፍሪካ ፋይናንስ ላይ የከፍተኛ ደረጃ ምክክር ለማካሄድ እቅድ መያዛቸውንም ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል
Feb 16, 2026 487
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ):- ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሴኤ) ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁነቱን አዘጋጅተውታል። “የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ በፋይናንስ መደገፍ፤ ሥራ እና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ትራንስፎርሜሽን” የፎረሙ መሪ ሐሳብ ነው። የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ የልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄድ ከፍተኛ አኅጉራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። አኅጉራዊው መድረክ የአፍሪካ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያንና የልማት አጋሮችን በአንድ መድረክ ያገናኛል። ፎረሙ አጋርነትና የኢንቨስትመንት መጠንን ማሳደግ በተለይም የመንግሥት እና የግል የተቀናጀ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይወያያል። የሥራ ዕድል፣ ምቹ የኢኖቬሽን ሥነ-ምኅዳር እና የአፍሪካን የፈጠራ ዐቅም አሟጦ መጠቀም በፎረሙ ላይ ምክክር ከሚካሄድባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይም የዲጂታል ኢንዱስትሪዎች፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም እየሰፋ ያለው የአፍሪካ የፈጠራ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶታል። በፎረሙ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችና ማዕቀፎች ይተዋወቃሉ። የወጣቶችን የኢኖቬሽን ሥራ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የሚያስተሣሥር የአፍሪካ የወጣቶች አይበገሬነትና ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ይፋ ይሆናል። በኢሲኤ የበለጸገውና የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ቃል ኪዳኖችን ትግበራ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ሥርዓትም በፎረሙ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ ይገባል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሁነት ላይ የአፍሪካ ሀገራት የመሪዎች የምክክር መድረኮችና የባለሙያዎች ውይይቶች ይደረጋሉ። አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የፈጠራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች እና ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ ዐውደ-ርዕይም ይካሄዳል። ሁነቶቹ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨበጡ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ለመቀየር አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል። የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በዘላቂ ልማት ግቦችና በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ ስትራቴጂካዊ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝም በመረጃው ተመላክቷል። የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች https://linktr.ee/ENADigitalክቷል።
አፍሪካ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸመባት በደል የታሪክ ዕውቅና እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የምትጠይቅበት ነው - የጋና ፕሬዚዳንት
Feb 15, 2026 433
አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፦አፍሪካ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸመባት በደል የታሪክ ዕውቅና እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የምትጠይቅበት መሆኑን የጋና ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ሻምፒዮን ጆን ድራማኒ ማሃማ ገለጹ። ”ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል። ከሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የጋና ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ሻምፒዮን ጆን ድራማኒ ማሃማ "የቅድመ አያቶች ዕዳ፣ ዘመናዊ ፍትሕና የአፍሪካውያን ምክንያታዊ የአንድነት ውክልና" በሚል መሪ ሃሳብ መነሻ መግለጫ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው፤ በአፍሪካ ለተፈጸመው በደል ስርዓታዊ ማካካሻና በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ላይ ለምታቀርበው ፍትሀዊ የውክልና ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በትራንስ-አትላንቲክ የባሪያ ንግድ በአፍሪካውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ በሰው ልጅ ታሪክ የታየ ከፍተኛው ኢ-ፍትሀዊ በደል መሆኑን አስታውሰዋል። ይህ ኢ-ፍትሀዊ በደል ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ዕውቅና መስጠት መከፋፈል ሳይሆን የሞራል ድፍረትና ፍትሕን የማረጋገጥ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ብለዋል። የአክራ ዳግም ማስጀመር የተሰኘው አሕጉራዊ ንቅናቄ አፍሪካ በውጭ ያላትን የእርዳታ ጥገኝነት ለማስቆም ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በኮቪድ-19 ወቅት አፍሪካ ክትባት በማግኘት ረገድ የመጨረሻ ተሰላፊ የነበረችበትን አሳዛኝ ሁኔታ በማስታወስ፣ አህጉሪቱ የራሷን የጤና እና የፋይናንስ ተቋማት በራሷ አቅም መገንባት እንዳለባት ገልጸዋል። የማካካሻ ፍትህን ጥያቄን በተመለከተም ጥያቄው ከገንዘብ ክፍያ ባለፈ የታሪክ መዝገብን የማስተካከልና የተዘረፉ ቅርሶችን የመመለስ ጉዳይ እንደሚጨምር ጠቁመዋል። አፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ድምፅ ለመቆም መስማማታቸውን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል የባሪያ ንግድ በሰው ልጅ ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል እውቅና እንዲያገኝ ግፊት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ለአፍሪካ ብልጽግና እና መረጋጋት በውኃ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል
Feb 15, 2026 362
አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፡- ለአፍሪካ ብልጽግና እና መረጋጋት በውኃ ዘርፍ ላይ በቁርጠኝነት ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ በአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ አስገነዘቡ። 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሐሳብ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ውኃ እና የንጽህና አጠባበቅ ለአፍሪካ ልማት እና ለኢኮኖሚ ሽግግር መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። አፍሪካ በዘርፉ በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር የገንዘብ እጥረት እንዳለባት ጠቁመው፤ ይህም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል። ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአፍሪካ ኅብረት 39ኛው የመሪዎች ጉባዔ መሪ ሐሳብ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና አስተማማኝ የንጽህና ሥርዓቶችን በማረጋገጥ አጀንዳ 2063ን ማሳካት" ተብሎ የተመረጠውም ለዚህ ነው ብለዋል። በጉባዔው ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የሆኑ ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህም በዓመት በርካታ ቢሊየን ዶላር የሚደርስ የኢንቨስትመንት ቃል ኪዳን ተገኝቶላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የውኃ ፕሮግራሞችን እንዲያዘጋጁ የሚያግዙ መመሪያዎች እና የኢንቨስትመንት ሂደቱን ለመከታተል የሚያስችል የውጤት መመዝገቢያ ይፋ መደረጉንም ጠቅሰዋል። ለአፍሪካ ብልጽግና እና መረጋጋት በቁርጠኝነት በውኃ ዘርፍ ላይ በቆራጥነት ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ
Feb 15, 2026 431
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የጉባኤው መሪ ቃል ነው። ትናንት የተጀመረው ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መምከሩን ይቀጥላል። ከመሪ ቃሉ ጋር በተያያዘ ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓት፣ አካታች እድገት፣ ጤናማ ማህበረሰብና ጠንካራ ስነ ምህዳር መገንባት፣ የተፈጥሮ ሀብት ዘላቂ አጠቃቀምና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ጉዳዮች ውይይት ይደረግባቸዋል። ውሃ እና ንጽህና የአጀንዳ 2063 አጀንዳን ከማሳካት አንጻር ያላቸው ሚና ይቃኛል። ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ ተቋማዊ እና የፋይናንስ ሪፎርሞች፣ ቀጣናዊ አጋርነትና አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላት ሚና ጉባኤው ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ። የአፍሪካ ህብረት የ2026 መሪ ሀሳብ ይፋ ማድረጊያ መርሐ-ግብርም ዛሬ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይገኝበታል። በመርሐ-ግብሩ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ይገኛሉ። የሀገራት መሪዎች የሚገኙበት የአፍሪካ ሀገራት የውሃ ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ የተመለከተ ከፍተኛ መድረክም ይካሄዳል። የአፍሪካ ህብረት የደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ባለስልጠናት ኮሚቴ በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምክክር ያደርጋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሚገኙ የአፍሪካ አባል ሀገራት (A3) የሚኒስትሮች ስብሰባም ይከናወናል። ሱማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ላይቤሪያ የምክር ቤቱ የአፍሪካ አባል ናቸው። የዓለም የጤና ስርዓት ምህዳርን ማሻሻል ላይ የዓለም ትብብር ምን መምሰል እንዳለበት የሚመክር ጉባኤም ይካሄዳል። የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በአህጉሪቱ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ። በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የጎንዮሽ ሁነቶችም እንዲሁ ከዛሬ መርሃ ግብሮች መካከል ናቸው። የተለያዩ የአፍሪካ ህብረት ተቋማት እና አደረጃጀቶች በስራዎቻቸው ዙሪያ መግለጫዎች እንደሚሰጡና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ውይይቶች እንደሚካሄዱ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል። 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዙ ወገን አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ
Feb 13, 2026 328
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የፀጥታው ምክር ቤት ውክልናን ጨምሮ የባለብዙ ወገን አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ። 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከጉባኤው አስቀድሞ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ በቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት፣ ዘላቂ ልማትና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ላይ ያተኮረ ነው። በተለይም የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ እሴት መጨመርና መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ለእድገት፣ ለስራ ፈጠራ እና ለዘላቂ መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ተነስቷል። የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የህብረቱ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጋርነት ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ ሰላም፣ ደህንነትና ዘላቂ አጋርነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዙ ወገን ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኑን ገልጸው አፍሪካ በዓለም ሰላም፣ ደህንነትና የባለብዙ ወገን ስርዓት ሪፎርም ወሳኝ ሚና እንዳላት ተናግረዋል። በውይይቱ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ሪፎርም እንደሚያስፈልገውና አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ ውክልና ማግኘት እንደሚገባት ተነስቷል። ባለስልጣናቱ ህብረቱ እና ተመድ የዓለም የፋይናንስ ስርዓት እንዲሻሻልና አፍሪካ ፍትሃዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንድታገኝ የጀመሩትን የጋራ ስራ አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አጀንዳ 2063: የ50 ዓመቱ የአፍሪካ እቅድ
Feb 13, 2026 596
.አጀንዳ 2063 ‘የምንፈልጋትን አፍሪካ ‘ በሚል መሪ ሀሳብ አፍሪካ ለ50 ዓመት (ከእ.አ.አ 2013 እስከ 2063) የምትመራበትን እቅድ የያዘ ማዕቀፍ ነው። .አጀንዳው ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት የተደረገበት እ.አ.አ በ2013 በአዲስ አበባ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ(ጉባኤው የተካሄደበት ዓመት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የተከበረበት ነው)። .አጀንዳ 2063 እ.አ.አ በ2015 በአዲስ አበባ በተካሄደው 24ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ውይይት ተደርጎበት አባል አገራቱ አጽድቀውታል። .የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት(የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት) አፍሪካ ከአፓርታይድ ስርዓት ለማላቀቅና የፖለቲካ ነጻነት እንድታገኝ ሲያደርግ የነበረው ትግል ለአጀንዳ 2063 አጀንዳ መጠንሰስ ምክንያት እንደሆነ ይገለጻል። .አጀንዳ 2063 በአፍሪካ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የሆነ ልማት ማምጣት እንዲሁም በፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ሕዳሴ ራዕይ ስር አንድነቷን የጠበቀች፣ የራስን እድል በራስ የምትወስን፣ነጻ የሆነች፣የተለወጠችና የበለጸገች አፍሪካ የመፍጠር ግብ እንዳለው የአፍሪካ ሕብረት በድረ ገጹ ላይ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል። .አጀንዳ 2063 የአፍሪካን ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የልማት ግቦችን ያሳካል ተብሎ የታመነበት የአህጉሪቷ ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ ሲሆን፤አፍሪካን በዓለም መድረክ ተጽእኖ ፈጣሪ የማድረግ ራዕይ ያለው ነው። አጀንዳ 2063 ሰባት ግቦች ሳይሆን ሰባት አላማዎች፣20 ግቦችና 15 ፕሮጀክቶች ያሉት ነው የአጀንዳ 2063 ሰባት አላማዎችና ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫዎች አጀንዳ 2063 ‘የምንፈልጋትን አፍሪካ ‘ በሚል መሪ ሀሳብ አፍሪካ ለ50 ዓመት (ከእ.አ.አ 2013 እስከ 2063) የምትመራበትን እቅድ የያዘ ማዕቀፍ ነው። አጀንዳ 2063 ሰባት አላማዎችና ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫዎች አሉት። እነሱም፦ 1. ሁሉን አቀፍ በሆነ እድገትና ዘላቂ ልማት የበለጸገች አፍሪካን መፍጠር 2. በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤዎችና በአፍሪካ ሕዳሴ ራዕይ አማካኝነት የተሳሰረችና ፖለቲካዊ አንድነት ያላት አህጉርን እውን ማድረግ 3. አፍሪካን መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ የሰብአዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት፣ ፍትሕ የነገሰባትና ዴሞክራሲያዊ አህጉር ማድረግ 4 .ሰላሟንና አንድነቷን የጠበቀች አፍሪካን መፍጠር 5.ጠንካራ የባህል ማንነት፣ የጋራ ቅርስና እሴቶች ያሏት እንዲሁም ጠንካራ ማህበረሳባዊ የሞራል መሰረት የፈጠረች አፍሪካን ማየት 6. አፍሪካ ልማቷ ዜጎችን ማዕከል ያደረገ፣ የአፍሪካን ሕዝብ በተለይም የወጣቶችና ሴቶችን አቅም የሚጠቀምና ለሕጻናት ክብካቤ ትኩረትን የሰጠ እንዲሆን ማድረግ 7. ጠንካራ፣ አንድነቷን የጠበቀች፣ የማትበገርና በዓለም መድረክ ተጽእኖ ፈጣሪና አጋር የሆነች አፍሪካን መፍጠር ናቸው። የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአጀንዳ 2063 አፈጻጸም ትግበራ ላይ እንደሚመክር የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።
የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሶማኒ እና የሌሴቶው ንጉስ ሌትሴ ሳልሳዊ በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ
Feb 11, 2026 455
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሶማኒ እና የሌሴቶው ንጉስ ሌትሴ ሳልሳዊ በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል። ፕሬዚዳንቱ እና ንጉሱ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በተያያዘ ዜና የጋምቢያ ምክትል ፕሬዚዳንት መሐመድ ጃሎው በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ አቀባበል አድርገውላቸዋል። 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።
48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ጀመረ
Feb 11, 2026 373
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። ስብሰባው “ዘላቂ የውሃ ኑረትና ንጽህና ስርዓት ለአጀንዳ 2063 ስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ ይደረጋል። የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በስብሰባው የሚሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል። ምክር ቤቱ በጥር ወር 2018 ዓ.ም 51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር ያደርጋል። የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ እስከ ነገ ይቆያል።
የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው
Feb 11, 2026 365
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እና በ39ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ። ዛሬ ንጋት አዲስ አበባ ከገቡት መካከል የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩድዘቶ አብላካዋ፣ የሲሸልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባሪ ፏር፣ የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቸኪህ ናንግ እና የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሞንደየሰ ሳሚያ ኩምቢያ ይገኙበታል። በተጨማሪም የኢስዋትኒ የውጭ ጉዳይ እና የአለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ፎሊል ድላሚኒ ሻካንቱ፣ የቶጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሮበርት ዱሰይ፣ የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የምስራቅ አፍሪካ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ማህመድ ታቢት ካምቦ እና የላይበሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳራ በይሶሎው ኒያንቲ አዲስ አበባ ገብተዋል። እንዲሁም የኮንጎ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኖይላ ናክዊፓኔ አዬጋናጋቶ በ48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እና በ39ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡት መከካል ይገኙበታል። ሚኒስትሮቹ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል። የሚኒስትሮች የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። የጅቡቲ፣ የቻድ፣ የጊኒ ሪፐብሊክ፣ የሌሴቶ፣ የኬንያ፣ አልጄሪያ እና ሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትላንት ለሊት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።
የህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ነገ ይጀመራል
Feb 10, 2026 273
አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የሚሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ። የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
የኢጋድ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳትፎ እና ቀጣናዊ የትኩረት መስኮች
Feb 9, 2026 303
አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰላም እና የውሃ ሀብቶችን ጨምሮ ቀጣናዊ የትኩረት መስኮች ላይ ትኩረት ያደረገ ተሳትፎ እንደሚኖረው አስታወቀ። የህብረቱ ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በመል መሪ ሐሳብ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል። ቀደም ብሎ የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም 48ኛው የህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ይካሄዳል። በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ የተመራ ልዑክ በጉባኤው ላይ ይሳተፋል። ኢጋድ በቀጣናው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ይዞ እንደሚቀርብ አስታውቋል። ሰላም እና ደህንነት፣ የአየር ንብረት፣ የውሃ ሀብቶች እና ቀጣናዊ ትስስር ከአጀንዳዎቹ መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ኢጋድ በጉባኤው የሚኖረው ተሳትፎ ከቀጣናዊ አጀንዳዎች እና ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን አመልክቷል። በዋና ጸሀፊው የሚመራው ልዑክ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ ከህብረቱ አባል ሀገራት ጋር በተለያዩ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ተመላክቷል። ኢጋድ የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች የቅንጅት እና የትብብር ማዕቀፍ ሊቀ መንበርነት በጉባኤው ላይ ለደቡባዊ አፍሪካ ልማት ትብብር ኮንፈረንስ(ሳዴክ) ያስረክባል። ይህም ለአህጉራዊ ትብብር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጿል። በሚኖሩት ምክክሮች እና ውይይቶች ኢጋድ የአፍሪካ ቀንድ የትኩረት መስኮችን ወደ አህጉራዊው መድረክ በማምጣት የሰላም፣ አይበገሬነትና የጋራ ብልጽግና አጀንዳዎች ለማሳለጥ እንደሚሰራ መግለጹን ኢዜአ ከተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች
Feb 8, 2026 452
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ እና አሥተዳደራዊ ክንፍ ነው። ኮሚሽኑ የሕብረቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፤ ፖሊሲዎችን ይተገብራል። በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት፣ ከቀጣናዊ ተቋማት እና አደረጃጀቶች ጋር ያላቸው ትብብር እንዲጠናከር የማስተባበር ሚና ይወጣል። የሕብረቱን በጀት እና ሀብቶችም ያሥተዳድራል። የተለያዩ የአፍሪካ ሕብረት አደረጃጀቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡም ድጋፍ ያደርጋል። ኮሚሽኑ በሊቀ መንበር የሚመራ ሲሆን፤ ምክትል ሊቀ መንበር እና የተለያዩ ዘርፎች የሚመሩ ኮሚሽነሮችንም ይዟል። በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ሊቀ መንበርነት የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በሥሩ ሥድስት ኮሚሽኖች አሉት። እነሱም:- የግብርና፣ ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን - በኢስዋቲኒው ሞሰስ ቪላካቲ የሚመራ፤ የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን - በኢኳቶሪያል ጊኒዋ ፍራንቺስካ ቻቹፕ ቤሎቤ የሚመራ፤ የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽን - በብሩንዲያዊው ፕሮፌሰር ጋስፓርድ ባያንኪምቦና የሚመራ፤ የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን - በደቡብ አፍሪካዊቷ ሌራቶ ማታቦጅ የሚመራ፤ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽን - በናይጄሪያዊው አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ የሚመራ፤ የጤና፣ ሰብዓዊ ጉዳዮችና የማኅበራዊ ልማት ኮሚሽን - በጋናዊቷ አምባሳደር አማ ትውም አሞን የሚመራ፤ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች መካከል ሦስቱ ሴቶች ናቸው። አንድ ኮሚሽነር ለአራት ዓመት የሚያገለግል ሲሆን፤ ኮሚሽነር ለመሆን በሚደረግ ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ መወዳዳር ይችላል። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እ.አ.አ በ2025 በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተካሄደ ምርጫ፤ ለአራት ዓመት በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ መመረጣቸው ይታወሳል። እንዲሁም አልጄሪያዊቷ አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ እ.አ.አ በ2025 በተካሄደው ምርጫ የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል። አምባሳዳር ሰልማ ከሩዋንዳዊቷ ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ በኋላ፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡ ሁለተኛ ሴት ባለሥልጣን ናቸው። 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም፤ ከዚህ ቀደም ብሎ ደግሞ 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ የዘንድሮው ጉባዔ “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በመል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያም ጉባዔው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅቷን አጠናቅቃለች።
የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የምታስተናግዳቸው አህጉራዊ ሁነቶች
Feb 4, 2026 626
በሙሴ መለሰ የዓለም ስርዓት በፍጥነት እየተቀያየረ ይገኛል። አፍሪካ በዚህ ተለዋዋጭ ስርዓት ውስጥ የሚገባትን ቦታ የመያዝ ጉዳይ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል። አፍሪካ በርካታ ወጣት የያዘች እና ብዝሃ የተፈጥሮ ፀጋዎች ያሏት አህጉር ናት። በአፍሪካ ተግባራዊ የተደረገው አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በቀጣናው የንግድ ትስስርን በማሳለጥ እድገትን የማፋጠን ተስፋ ተጥሎበታል። አፍሪካ እድሎቿን በሚገባ ለመጠቀምና የሚስተዋሉ ፈተናዎቿን ለመሻገር ምላሽ የምትሰጥበት የልማት እና እድገት ጉዞዋን ከመበየን ባለፈ በዓለም መድረክ የሚኖራትን ሚናም ይወስናል። በአህጉር ደረጃ የተቀመጡ እንደ አጀንዳ 2063 እና የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ያሉ አህጉራዊ ማዕቀፎች እንዲሳኩ ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። መንግስታት፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች ትብብራቸው ማጠናከር ይኖርባቸዋል። የተገቡ ቃልኪዳኖችን ወደ ሚለካ ውጤት ለመቀየር ዘላቂነት ያለው አመራር ሰጪነት፣ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር እና ተከታታይነት ያለው ውይይቶችን ማድረግ ይገባል። ውሳኔ ሰጪዎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኙ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ መድረኮች በአጀንዳዎች ላይ የተቀናጀ የተግበባር ምላሽ ለመስጠት ቁልፍ ሚና አላቸው። አፍሪካ እድሎቿን በመጠቀም እና ፈተናዎቿን በማለፍ መንገድ ላይ በሆነችበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ አህጉራዊ ሁነቶችን ታስተናግዳለች። 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል። የዘንድሮው መሪ ሀሳብ በአፍሪካ የውሃ ደህንነትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የመሪዎች ጉባኤ መሪ ሀሳብ ነው። ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓት ዘላቂ ልማት፣ አካታች እድገት፣ ጤናማ ማህበረሰብና ጠንካራ ስነ ምህዳር መገንባት፣ የተፈጥሮ ሀብት ዘላቂ አጠቃቀምና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር የተሳሰረ መሆኑ ተገልጿል። የመሪዎች ጉባኤው በመሪ ሀሳቡ በጥልቀት በመምከር የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦች ያስተላልፋል ተብሎም ይጠበቃል። ከመሪዎቹ ጉባኤ አስቀድሞ 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። 51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ኮሚቴ ተወካዮች (PRC) ስብሰባ ከጥር 4 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በስብሰባው የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል። ስብሰባው የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲሁም የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚከናወነው 39ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ መክሯል። ኮሚቴው በ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ሀሳብ ላይ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል። የኮሚቴው መደበኛ ስብሰባ ለዋናው ጉባኤ እንደ ይፋዊ የዝግጅት ስብሰባ የሚያገለግል ነው። ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ማግስት ሌላኛው በኢትዮጵያ የሚካሄደው ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ነው። የቢዝነስ ፎረሙ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሴኤ) ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁነቱን አዘጋጅተውታል። “የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ በፋይናንስ መደገፍ፤ ስራ እና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ትራንስፎርሜሽን” የፎረሙ መሪ ሀሳብ ነው። የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ የልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄድ ከፍተኛ አህጉራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን የኢሲኤ መረጃ ያመለክታል። በፎረሙ ላይ አጋርነትና የኢንቨስትመንት መጠንን ማሳደግ በተለይም የመንግስት እና የግል የተቀናጀ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይወያያል። የወጣቶችን የኢኖቬሽን ስራ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የሚያስተሳስር የአፍሪካ የወጣቶች አይበገሬነትና ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ይፋ ይሆናል። በኢሲኤ የበለጸገውና የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ቃል ኪዳኖችን ትግበራ የሚከታታልና የሚቆጣጠር ስርዓትም በፎረሙ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ ይገባል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሁነት ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የምክክር መድረኮችና የባለሙያዎች ውይይቶች ይደረጋሉ። አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የፈጣራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች እና ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ አውደ ርዕይም ይካሄዳል። ሁነቶቹ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨበጡ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ለመቀየር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል። ከአህጉራዊ ሁነቶቹ ባሻገር የባለብዙ ወገን መድረክ የሆነው የአፍሪካ እና ጣልያን ጉባኤ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ካለፈው ታሪካዊ ግንኙነቶች ፣ እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ ትብብር እና የጋራ ፈተናዎችን የመፍታት ቁርጠኝነት አኳያ በአፍሪካ እና በጣልያን መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ታምኖበታል። ኢትዮጵያ አህጉራዊ ሁነቶቹን ማዘጋጀቷ በአፍሪካ ዲፕሎማሲ ውስጥ ጸንቶ የቆየውን የመሪነት ሚናዋን እንዲሁም የአህጉራዊ ምክክር፣ የባለብዙ ወገን ውይይቶችና ስትራቴጂካዊ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባት ማዕከልነቷንም አጉልቶ የሚያሳይ ነው። የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት እና በከተማ ማዘመን ስራ በፍጥነት እየተለወጠች ሲሆን የሁነቱ ተሳታፊዎች ከስብሰባው ባለፈ የመዲናዋን አዲስ መልክ የመመልከት እድል ያገኛሉ። የእነዚህ አህጉራዊ ስብሰባዎች ስኬት የሚለካው በአቋም መግለጫ ሳይሆን አጋርነትን በማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግና የሚጨበጥ ውጤት በአህጉሪቱ በማስመዝገብ ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ የምታዘጋጃቸው አህጉራዊ ሁነቶች አህጉራዊ ትስስርን በማጠናከርና በዓለም ጉዳዮች ላይ የአፍሪካን ድምጽ ከፍ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ኢትዮጵያ ሁነቶቹን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የፈጣራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች እና ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ አውደ ርዕይም ይካሄዳል። ሁነቶቹ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨበጡ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ለመቀየር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል። ከአህጉራዊ ሁነቶቹ ባሻገር የባለብዙ ወገን መድረክ የሆነው የአፍሪካ እና ጣልያን ጉባኤ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ካለፈው ታሪካዊ ግንኙነቶች ፣ እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ ትብብር እና የጋራ ፈተናዎችን የመፍታት ቁርጠኝነት አኳያ በአፍሪካ እና በጣልያን መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ታምኖበታል። ኢትዮጵያ አህጉራዊ ሁነቶቹን ማዘጋጀቷ በአፍሪካ ዲፕሎማሲ ውስጥ ጸንቶ የቆየውን የመሪነት ሚናዋን እንዲሁም የአህጉራዊ ምክክር፣ የባለብዙ ወገን ውይይቶችና ስትራቴጂካዊ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባት ማዕከልነቷንም አጉልቶ የሚያሳይ ነው። የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት እና በከተማ ማዘመን ስራ በፍጥነት እየተለወጠች ሲሆን የሁነቱ ተሳታፊዎች ከስብሰባው ባለፈ የመዲናዋን አዲስ መልክ የመመልከት እድል ያገኛሉ። የእነዚህ አህጉራዊ ስብሰባዎች ስኬት የሚለካው በአቋም መግለጫ ሳይሆን አጋርነትን በማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግና የሚጨበጥ ውጤት በአህጉሪቱ በማስመዝገብ ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ የምታዘጋጃቸው አህጉራዊ ሁነቶች አህጉራዊ ትስስርን በማጠናከርና በዓለም ጉዳዮች ላይ የአፍሪካን ድምጽ ከፍ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ኢትዮጵያ ሁነቶቹን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
በኒጀር በደረሰ ጥቃት መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው የአስካይ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ተጠግነው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ
Feb 3, 2026 433
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ በኒጀር ዋና ከተማ በደረሰ ጥቃት መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት የአስካይ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ተጠግነው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ ፡፡ አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ባለፈው ሐሙስ ጥር 21/ 2018 ዓ.ም ሌሊት በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው ጥቃት ሁለት የአስካይ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፡፡ አውሮፕላኖቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋር የሆነው የአስካይ አየር መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ከአውሮፕላን አከራዮች የተከራያቸው እና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተመዘገቡ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ በአውሮፕላኖቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም የተላከው የቴክኒክ ቡድን ጉዳቱ መጠነኛ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን አውሮፕላኖቹ ተጠግነው በቅርቡ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡም ተገልጿል ::
የአፍሪካ ህብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም አጋርነታቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
Feb 2, 2026 317
አዲስ አበባ፤ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም ሰላምና ልማትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አጋርነታቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ ኮመንዌልዝ እና የልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ጋር በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተወያይተዋል። ውይይቱ ለረጅም ጊዜ ጸንቶ በቆየው የአፍሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም አጋርነት ያተኮረ ነው። ሁለቱ ወገኖች የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እና ህግን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ስርዓት ለመጠበቅ የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል። የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ዩናይትድ ኪንግደም ከአፍሪካ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ትስስር ያደነቁ ሲሆን በዓለም ላይ ያላትን ገንቢ ሚና እና ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ጋር በጤና፣ ትምህርት፣ የአየር ንብረት ምላሽ እና ንግድ ያላትን ትብብር አንስተዋል። ሀገሪቷ ለአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) በአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና ምላሽ እንዲሁም በሶማሊያ ለአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝም አመልክተዋል። የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ኮመንዌልዝ እና የልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ይቬት ኩፐር የአፍሪካ ህብረት በዓለም ዲፕሎማሲ፣ ቀጣናዊ ሰላም እና ልማት ያለውን ሚና አድንቀዋል። ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ህብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም በሱዳን፣ በሳሄል ቀጣና እና በሶማሊያ ያለውን የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል። #Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ
የአፍሪካ ሀገራት ለውኃ አቅርቦት፣ ጥራት እና ለንጽህና መሰረተ ልማቶች ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል
Feb 1, 2026 471
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- በአፍሪካ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም ሀገራት ለውኃ አቅርቦት፣ ለጥራት እና ለንጽህና መሰረተ ልማቶች ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው የአፍሪካ ሕብረት አስገነዘበ። በሕብረቱ የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጥበቃ ኮሚሽነር ሙሴ ቪላካቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አህጉራዊው የግብርና ልማት ፕሮግራም ባለፉት 20 ዓመታት በአባል ሀገራት ዘንድ ጉልህ ለውጦች ማምጣቱን ገልጸዋል። ይህም አባል ሀገራት ጠንካራ የግብርና ዕቅድ ሥርዓት እንዲዘረጉ፣ ውጤታማ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም ቀረፃ እንዲኖራቸው እና በምርትና ምርታማነት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማገዙን አንስተዋል። ፕሮግራሙ ትኩረት የሚያደርገው በተለይም በምርት መጠንና በምርታማነት ዕድገት ላይ በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሀገራት ውስጥ የሚታየው የምርት መጠን መጨመር የዚሁ ጥረት ውጤት ነው ብለዋል። ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ከውኃ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስገንዝበው፤ ግብርናን፣ ኢነርጂን ወይም ጤናን ስናስብ ሁሉም ነገር ከውኃ ጋር የተያያዘ ነው፤ ስለዚህ ውኃ ለዘላቂ ልማት እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል። ለዚህም ነው “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የሚለው መሪ ሐሳብ ለ39ኛው የሕብረቱ መሪዎች ጉባዔ የተመረጠው ብለዋል። ኮሚሽነሩ ጉዳዩ በሕብረቱ አጀንዳነት የተያዘው በአህጉሪቱ ያለውን የውኃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል። በአህጉሪቱ ወደ 400 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች መሰረታዊ የውኃ አገልግሎት እንደማያገኙ ጠቁመው፤ ከ700 ሚሊየን የሚልቁትም ደኅንነቱ የተጠበቀ የጽዳት አገልግሎት የላቸውም ብለዋል። ይህ የአገልግሎት እጥረት በሰዎች የዕድገትና የአህጉሪቱ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ላይ ትልቅ እንቅፋት መሆኑንም አመላክተዋል። ውኃን እንደ ትምህርት፣ ጤና እና ግብርና ትልቅ ትኩረት ሰጥተን ብንሠራበት ኖሮ ይህንን ችግር በቀላሉ መፍታት እንችል ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁን ላይ ጉዳዩ ትኩረት በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ዋነኛ ግብ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረው፤ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም 45 በመቶ የሚሆነውን የግብርና ምርት በአፍሪካ ለማምረት ግብ ይዞ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪ የአፍሪካን የውኃ አካላት ሀብት ወይም ብሉ ኢኮኖሚን ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሆነ አንስተው፤ ይህ ዘርፍ ለአህጉሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል ነው ያሉት። የአፍሪካን የሰብል ዝርያዎች መጠበቅ መቻል የአህጉሪቱ ኅልውና ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸው፤ ለዚህም ጠንካራ የዘር ባንኮች ሊኖሩን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።