ዓለም አቀፍ ዜናዎች
የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት ለባህር በር መዳረሻና ለስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ ነው
Jan 12, 2024 598
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት ስምምነት ለባህር በር መዳረሻ እና ለቀጣናው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ መሆኑ ተመላከተ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር መገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያ ድርሻ የምታገኝ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነትን በተመለከተ ሰፊ ትንታኔን ያቀረበው አፍሪካን ኒውስ ስምምነቱ በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አውዶች ረገድ ግዙፍ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት አመልክቷል።   ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ከማስቻሉ ጎን ለጎን ምርቶች የሚከማቹበት ተጨማሪ ወደብ በማስገኘት የገበያ ተደራሽነቷን እንደሚያሰፋው ነው የተመለከተው። የሰፊ ህዝብ ባለቤትና ከፍተኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሆነችው ኢትዮጵያ ቁልፍ ስምምነት ማካሄዷን ያተተው ዘገባው ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ያለውን የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው አብራርቷል። በቀጣናው የኢኮኖሚና ተዛማጅ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አሊ ሆጂጅ በዘገባው ላይ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ የቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚና ህዝብ ባለቤት እንደመሆኗ የእድገት ጉዞዋን የሚመጥን ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋታል። ከሶማሌላንድ ጋር ያካሄደችው ስምምነትም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ በጅቡቲ ብቻ የነበረውን የወደብ ተጠቃሚነት በማስፋት የባህር በር እንድታገኝ ያስቻለ ቁልፍ ርምጃ መሆኑን አብራርተዋል። ስምምነቱ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ሆና በተቀላቀለችበት ወቅት የተካሄደ መሆኑም ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ባለሙያው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የሚኖራትን ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የሚኖራትን ሁለገብ ግንኙነት እንድታሰፋ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት። በቀጣናውና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄዱ የንግድ እንቅስቀሴዎች ላይም በባለቤትነት ለመሳተፍ ይህ ስምምነት ቁልፍ መሆኑን ያተቱት ባለሙያው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር እውቅና እንድታገኝና በአካባቢው የሚኖራትን ተሰሚነት የሚያሳደግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር  ለመስራት የወሰደችው እርምጃ  ብልህነት የተሞላበት ነው
Jan 11, 2024 413
አዲስ አበባ ፤ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፦ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት የወሰደችው እርምጃ ብልህነት የተሞላበት መሆኑን የአልአረብ ፐብሊሺንግ ኩባንያ ዋና አዘጋጅ (ዶ/ር )ሃይታም ኤል ዞባይድ ገለፁ። ሃይታም ዘአረብ ዊክሊ ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ የአለም ስርአት በእጅጉ መድልዎ የተሞላበት ነው። በማሳያነትም ሶማሊላንድ ነጻነቷን ማግኘት የነበረባት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1990ዎቹ መጀመሪያ አንደነበር በማንሳት ። በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ጥላ ስር የቆየችው ሶማሊላንድ በ1960ዎቹ ነጻ ስትወጣ ከጣሊያን ሶማሊ ጋር እንድትቀላቀል የተደረገበት መንገድ ተንኮሎች እንደነበሩት በምልሰት ያስታውሳሉ። እንደሌሎቹ የባህረሰላጤው ሃገራት የተትረፈረፈ የነዳጅ ሃብት ቢኖራት ኖሮ ልእለሃያላኑ ሀገራት ከሶማሊ ጋር እንድትቀላቀል አይፈርዱባትም ነበር ሲሉም ይሞግታሉ። ቀደም ሲል አሜሪካን ጨምሮ ከ35 ያላነሱ ሃገራት እውቅና የሰጧት ሶማሊላንድ በግዴታ ወደ ሶማሊያ መዋሃዷ ዜጎቿ ለተቃውሞ ዳርጎ ነበር ፤ በ1990ዎቹ የዚያድባሬ አገዛዝን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሶማሊያ የእርስበእርስ ጦርነት የሶማሊላንድን ዳግም ውልደት እስኪያመጣ ድረስ ። የዚያድባሬ አገዛዝ መገርሰስ የእርስበእርስ ጦርነት፣ የባህር ላይ ዝርፊያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ያለመረጋጋት ማንገሱን ያተተው የዶክተሩ ጽሁፍ ሶማሊላንድ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥም ሆና ዜጎቿን ማረጋጋት፣ የባህር ክልሏን መጠበቅ ብሎም ምርጫዎችን በማካሄድ የሉአላዊ ሃገር ተግባራትን ስትፈጽም እንደቆየች አትቷል። የትኛውም ሃገርም ሆነ ባለሃብት የረጅም ጊዜ ትርፉን አስቦ እንደሚንቀሳቀስ ነጋሪ እንደማይፈልግ የገለጹት ዶክተሩ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት፣ የገበያ አቅም፣ የመልማት እድል ብሎም የዲፕሎማሲ ትስስር አኳያ ለሶማሊላንድ ሊታለፍ የማይችል መልካም አጋጣሚ ነው። ዶክተሩ ሃሳባቸውን ሲቋጩ እስካሁን በነበረው ሁኔታ የሞቃዲሾ አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ አንዳንድ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሃገራት ታማኝ የልማት አጋር ሆነው ተባብረው የመስራት ብሎም የመለወጥ እድላቸውን በተከተሉት የአስተዳደር ዘይቤና ስግብግብነት ምክንያት ያባከኑ መሆናቸው ያስታውሳሉ። ከዚህ በተቃርኖ ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና በኤሽያ ሃገራት የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን በመረዳት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት መወሰኗ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ይሞግታሉ።
የመግባቢያ ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው
Jan 6, 2024 467
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ በሳህል ቀጠና የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛና የአትላንቲክ ካውንስል የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም ገለጹ። አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል። አምባሳደሩ ስምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛትና የመልማት አቅም እንዲሁም ከወደብ ኪራይ ዋጋ ውድነት አንጻር በጅቡቲ ወደቦች ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ከተገነዘበች ቆይታለች ብለዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ፣ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም አብራርተዋል። በተጨማሪም ስምምንቱ የቀጣናውን አካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ሊያሻሽል የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል። በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ በርካታ ሀገራት ሶማሌላንድን በነጻና ሉአላዊት ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋት የነበረ መሆኑን አስታውሰው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከሶማሊያ ግዛት ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል ነው ያሉት። ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መፈራረስ በኋላ ሶማሌላንድ የራሷ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች በማድረግ የራሷን አስተዳደር መስርታ ከሰላሳ አመታት በላይ መቆየቷንም አስታውሰዋል። ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች ሀገራትም በሶማሌላንድ መዋእለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆናቸውን በማውሳት የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትሱ ዱባይ ፖርትስ ኩባንያ ጋር በመሆን ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት በበርበራ ወደብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል። ቢዘገይም ቢፈጥንም፤ ቢፈለግም ባይፈለግም ሶማሊላንድ አለም አቀፍ እውቅና የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል አምባሳደሩ።
በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈረመው ስምምነት ለቀጣናው አዲስ ምእራፍ የሚያስተዋውቅ ነው
Jan 5, 2024 414
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የባህር በር አጠቃቀምን በሚመለከት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ለቀጣናው አገራት አዲስ ምእራፍ የሚያስተዋውቅ መሆኑን የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አንድሪው ኮሪብኮ ገለጹ። ሰርቫይቭ ዘ ኒውስ በተባለው ድረገጽ ላይ የሰፈረው የተንታኙ ዘለግ ያለ ጽሁፍ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን ለኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አገልግሎት ለመጠቀም የገባችው ስምምነት ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ትስስር ከማሳደግ ባለፈ ሌላ አላማ አለመያዙን አስረድተዋል። ብዝሃ ባህልና ሃይማኖት የሚተገበርባት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ አጠቃቀምን በሚመለከት የደረሰችበት የመግባቢያ ሰነድ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገባ ከሶማሊላንድ ባለፈ ወደ ሌሎች የአካባቢው አገራት የሚሻገር ትሩፋት እንዳለው ያተተው የተንታኙ ጽሁፍ ጥቂት የማይባሉ አካላት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስምምነቱን ጥላሸት እየቀቡት ይገኛሉ ብለዋል። ስምምነቱን ተከትሎ የተቃርኖ አስተሳሰቦችን የሙጥኝ ብለው የያዙ ሰዎች ከምንም በላይ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን ስምምነትና መልካም ምሳሌ ይጸየፋሉ ሲሉ ወቅሰዋል። ተንታኙ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗን ባረጋገጠችበት እለት የተፈረመው ይሄ የመግባቢያ ሰነድ ለሶማሊላንድ ህዝብና መንግስት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን በማንሳት ሁነቱ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ህዝቦች በተለይም ለሶማሊላንድ ዜጎች አዲስ የሚባል የታሪክ ክስተት ሆኖ ሊመዘገብ የሚገባው ነው ብለዋል። ስምምነቱ በትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር በሰጥቶ መቀበል መርህ በቀጣናው አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአለም ላይ በአንድ ቦታ እንደተቀመጠ የሚገኝ ነገር አለመኖሩን የሚያሳዩ ተጨባጭ ክስተቶች መኖራቸውን በማሳያዎች ያብራሩት ተንታኙ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በእጅጉ ኋላ ከቀሩበት የኢኮኖሚ ደረጃ ተመንጭቀው መውጣት ካለባቸው መሰል ስምምነቶችን አድርገው እድገታቸውን ማስቀጠል የግድ ይላቸዋል ብለዋል። ኢትዮጰያ ካላት ሁለንተናዊ አቅም አንጻር መሰል ስምምነቶችን አድርገው የጥቅም ተጋሪ መሆን የሚችሉ አገራት መሪዎች ይሄንን ሁነት ቀለል አድርገው ሊመለከቱት እንደማይችሉ በማተት በጉዳዩ ላይ የሶማሊያ ፌደራል መንግስትና የሽብር ቡድኑ አልሽባብ አብረው ለመስራት ያደረጉት ያልተቀደሰ ጋብቻ መጨረሻው መጠፋፋት መሆኑን አስምረውበታል።  
የስዕል ማራቶን ክብረ ወሰንን የሰበረው ናይጄሪያዊ የሥነ ጥበብ ተማሪ
Jan 4, 2024 321
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፡- ለተከታታይ 100 ሰዓታት የተለያዩ ስዕሎችን የሳለው ናይጄሪያዊው የሥነ ጥበብ ተማሪ የአለም የስዕል ማራቶን ክብረ ወሰንን ሰብሯል። በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት በሳቫና የስዕልና ዲዛይን ኮሌጅ ተማሪ የሆነው ቻንስለር አሀጎቱ ለረጅም ሰዓታት በመሳል የአለም ክብረ ወሰንን እንደጨበጠ ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ አስታውቋል። ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2013 በቤልጄየማዊው የስነ ጥበብ ተማሪ ሮናልድ ፓልሜርትስ የተያዘውን ለ60 ሰዓት የመሳል ክብረ ወሰን በመስበር ነው እውቅናውን የጨበጠው። ለአራት ቀናት ገደማ ቻንስለር ባካሄደው የስዕል ስራ የታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ፣ ምግቦች፣ ዕጽዋትና እንሰሳት እንዲሁም 106 ልዩ ልዩ ስዕሎች መሳሉን ዘገባው አመልክቷል። ለተከታተይ 88 ሰዓታት በስዕል ስራው ላይ ከቆየ በኋላ የድካም ስሜት ታይቶበት ነበረ ያለው ዘገባው ድካሙን በማሸነፍ ክብረ ወሰኑን መስበሩን አስነብቧል። ቻንስለር አሀጎቱ እውቅናውን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት “ወደ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የመጣሁት ሕልሜን እውን ለማድረግ ነው፣ ለ100 ሰዓታት ያለ እረፍት በመሳል ያሳካሁት ድል ነው ብሏል።
የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን አመት ስኬታማ ነበር
Jan 1, 2024 358
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016 (ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ አመት የኢትዮጵያና የቻይና ሁለንተናዊ ግንኙነት ስኬታማ ሆኖ ማለፉን ምሁራን ገለጹ። የሀገራቱ ግንኙነት በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ የማይለወጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የእውቀትና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በአውሮፓውያኑ 2023 ከተከወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል መሆናቸውን ዥንዋ አስነብቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና ቤጂንግ ባደረጉት ጉብኝት የሀገራቱ ግንኙነት በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ የማይለወጥበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይፋ እንደተደረገ ያስታወሰው ዘገባው ኢትዮጵያና ቻይና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ አብረው ሊሰሩባቸው የሚያስችሉ በርካታ እድሎች እንዳሉ አስነብቧል። ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ የስትራቴጂክ ግንኙነት ተቋም የአለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው መላኩ ሙሉአለም የአውሮፓውያኑ 2023 በኢትዮጵያና በቻይና ግንኙነት ሂደት ውስጥ “ታሪካዊ” ተብሎ ሊታወስ የሚችል መሆኑን ገልጸው አመቱ ከሚተባበሩባቸው የአለም ሰላምና ሁለንተናዊ ልማት ባሻገር የሃገራቱ ምጣኔሃብታዊ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ነው ብለዋል። “አመቱ ኢትዮጵያና ቻይና በልማትና ዘርፎች ለመርዳት የገባችውን ቃል ማክበሯን በተግባር ያሳየችበት ነው” ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፐብሊክ ፖሊሲ ፕሮፌሰር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ ናቸው። በተጠናቀቀው አመት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን የቻይና ድጋፍ ጉልህ እንደነበር ያስነበበው ዘገባው፤ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ በብሪክስ ቡድን የምታደርገው ተሳትፎ ከራሷ አልፎ ለአካባቢው ሃገራትም የሚተርፍ እንደሚሆን ተገልጿል። “በደቡብ-ደቡብ ትብር ውስጥ ኢትዮጵያ ወሳኝ የሚባል ድርሻ ስላላት አባል በሆነችበት የብሪክስ ቡድን ውስጥም ይሄንን ሚናዋን አጉልታ ታሳያለች” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው ቻይና ከቴክኒክና ሙያ በባቡር መሰረተልማት እንዲሁም በሳተላይት ዘርፎች ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የምትሰጠውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች አጠናክራ ትቀጥላለች ብሏል።  
በመጪው  ከጥር እስከ መጋቢት  ወራት የአፍሪካ ቀንድ   ከባድ ዝናብ  ያስተናግዳል
Dec 31, 2023 338
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21/2016 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከጥር እስከ መጋቢት ከባድ ዝናብ እንደሚጥል ኢጋድ አስጠነቀቀ። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከጥር እስከ መጋቢት 2024 ወራት አብዛኛው የአፍሪካ ቀንድ ከባድ ዝናብ እንደሚጥል ተንብይዋል። በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ የኤልኒኖ ተጽኖ ምክንያት መሆኑንም ማዕከሉ አስታውቋል። መቀመጫውን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ማዕከሉ በትንበያው እንዳስታወቀው፤በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የሁኑ እርጥበታማ የአየር ሁኔታዎች በደቡባዊ እና ኢኳቶሪያል አካባቢ በሚገኙ የቀጠናው ክፍሎች ላይ ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ እንደሚጠበቁ ማዕከሉ ገልጿል። ከጥር እስከ መጋቢት ከባድ ዝናብ ከሚያስተናጉዱት ሀገራት መካከልም ታንዛኒያ፣ብሩንዲ፣ኬንያ፣ደቡብ ኡጋንዳ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ እንደሚገኙበት ማዕከሉ አስታውቋል። ማዕከሉ ጨምሮ እንዳስታወቀው፤ በዚህ ወቅት ከመደበኛው ሁኔታ በላይ ደረቃማ ሁኔታ እንደሚኖር አመልክቷል። ደረቅ የሚሆኑት አካባቢዎችም በማዕከላዊ ኬንያ፣ በሰሜን እና በምዕራብ ታንዛኒያ በሚገኙ ጥቂት ቦታዎች ላይ ነው ብሏል። የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በአጠቃላይ ከጥቅምት እስከ ታህሣሥ ባለው ጊዜ በገጠማቸው የዝናብ እጥረት ድርቅ እንደነበረ ያስታወሰው ማዕከሉ፤ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ የአየር ሁኔታውን እየቀየረ መሆኑን ገልጿል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል በአካባቢው ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በተጨማሪ፣ የሙቀት መጠኑ ከመደበኛው በላይ እንደሚሆንም አመልክቷል። በዚህ ወቅት በመኪሰተው ሙቀት የከፋ ጉዳት የሚደርስባቸው ቦታዎች የሰሜን ኬንያ፣ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን የተለያዩ ክፍሎች እንደሚያጠቃልል ያስታወቀው ማዕከሉ፤ በዚህ ወቅት የሚከሰተው የሙቀት መጠን ከ32 እስከ 40 ዲግሪ ሴልስየስ ሊጨምር እንደሚችልም ተንብይዯል። የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሊጠናቀቅ ሰዓታት በቀሩት የፈረንጆቹ ዓመት ፈጣን የአየር ሁኔታ ለውጦች ማገጠሙን ያመለከተው ማዕከሉ፤ በጥቅምት ወር በአካባቢው የጣለው የኤልኒኖ ዝናብ በጎርጎርሲያኑ አቆጣጠር ከጥር 2024 እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ከፍተኛ ዝናብ አስከትሎ ይከሰታል ብሏል። በቀጠናው የተራዘመ ድርቅ አለያም የጎርፍ አደጋዎች በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ዥንዋ ዘግቧል።
ህንድ ለጂኦ ኢንተለጀንስ አገልግሎት የሚውሉ 50 ሳተላይቶችን ልታመጥቅ ነው
Dec 29, 2023 345
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፡- ህንድ ለጂኦ ኢንተለጀንስ አገልግሎት የሚሰጡ 50 ሳተላይቶችን ወደ ህዋ የማመንጠቅ ዕቅድ እንዳላት ተገለጸ። የአገሪቱን የጠፈር ምርምር ድርጅት ዋና ኃላፊ ኤስ ሶማታንን ጠቅሶ የዘሂንዱ ድረገጽ እንደዘገበው ሳተላይቶቹ በሚቀጥሉት አምስት አምታት ወደ ህዋ የሚመነጠቁ ናቸው። እስካሁን የአብዛኛዎቹ ሳተላይት ንድፍ እና ቀመር መጠናቀቃቸውን ኃላፊው ጠቁመው ሳተላይቶቹ በጠፈር ላይ በተለያዩ ምህዋሮች እየተሽከረከሩ ከሺህ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ እንቅስቃሴዎችን ከመከታተል ባለፈም የምስል መረጃ የመላክ አቅም ያላቸው እንደሆኑም አብራርተዋል። ህንድን ከአለም ጠንካራ አገሮች ተርታ ለማሰልፍ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል የመረጃ ሳተላይት ሰርቶ የማመንጠቅ ስራ አንዱና ዋነኛው መሆኑን የጠፈር ምርምር ተቋም ሊቀመንበር ኤስ ሶማታን ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት አገሪቱ የምትጠቀምባቸው የሳተላይት ቴክኖሎጂዎች አቅም ውስንነት ያለባቸው መሆኑን ጠቁመው ወደፊት አገሪቷ የምታምጥቃቸው የሳተላይት አይነቶች በብቃት ከአሁኖቹ በአስር እጥፍ የላቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። ህንድ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን አምርቶ ለማመንጠቅ መዘጋጀቷንም መረጃው አስታውሷል።  
የኡጋንዳ መከላከያ ኤዲኤፍ የተሰኘው የሽብር ቡድን መሪ መገደሉን ገለጸ
Dec 29, 2023 284
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የኡጋንዳ መከላከያ ሰራዊት በምዕራባዊ ኡጋንዳ የሽብር ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው ያለውንና የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሚል የሚጠራውን ቡድን መሪ መግደሉን አስታወቀ። የኡጋንዳ ህዝቦች መከላከያ ሠራዊት እንዳስታወቀው በዚህ ወር በሀገሪቱ ተከስቶ ለነበረውና 13 ሰዎች ለሞቱበት የሽብር ተግባር ተጠያቂ የነበረው የኤዲኤፍ መሪ መከላከያ ሠራዊቱ በወሰደው ወታደራዊ ዘመቻ ተገድሏል። የሰራዊቱ ምክትል ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዴዎ አኪኪ እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ መሪ ሙሳ ካሙሲ እርምጃ ተወስዶበታል። አሸባሪው ታህሳስ 8 እና 16 በኪባሌ ብሔራዊ ፓርክ በተፈጸመው ጥቃት ዋነኛ መሪ የነበረ ሲሆን በዚህም የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅትም የኡጋንዳ ህዝቦች መከላከያ ሠራዊት ቀጣናውን ከአሻባሪዎች ነጻ የማድረግና ወደ ቀደመ ሰላሙ የመመለስ ተግባር በተጠናከረ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። አሸባሪ ቡድን ከቅርብ አመታት ወዲህ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቱሪስቶችን ጨምሮ በንጹሃን ላይ የሽብር ተግባር በመፈጸም ተጠያቂ የተደረገ ቡድን መሆኑን አናዶሉ ዘግቧል።    
ቻይና ለአየር ንብረት  ትንበያ የሚያገለግሉ አራት ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ላከች
Dec 27, 2023 290
አዲስ አበባ ፤ ታህሣሥ 17/2016 (ኢዜአ)፦ ቻይና ለአየር ንብረት ትንበያ የሚረዱ አራት አዲስ ሳተላይቶችን በያዝነው ሳምንት ወደ ህዋ መላኳን አናዶሉ አስነብባል። ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ጂውኩዋን ከተባለው የጠፈር ማምጠቂያ ማእከል የተደረገው ሳተላይቶቹን የማምጠቅ ሂደት ስኬታማ እንደነበርና በእለቱም ሁዋይ ዡ 1ኤ የተሰኘችው ሮኬት እንደመጠቀች ይፋ ተደርጓል። ሁዋይ ዡ 1ኤ የተባለችው ሮኬት ለ24ኛ ጊዜ መምጠቋን ተከትሎ ቻይና ለንግድ፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚውሉ ተጨማሪ አራት ሳተላይቶችን ከቀናት በፊት እንዳመጠቀች ተገልጿል። ወደ ህዋ የተላኩት ሳተላይቶች ወደታቀደላቸው ምህዋር መድረሳቸውና የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን እንደሚልኩም በመረጃው ተመላክቷል። ቻይና ማክሰኞ ወደ ህዋ ከላከቻቸው አምስት ሳተላይቶች መካከል ሶስቱ ሺያን -24ሲ የሚባሉና የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ነክ ለሆኑ ምርምሮች የሚያገለግሉ እንደሆነም ተገልጿል።
በኮፕ28 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ላይ ተደረሰ
Dec 24, 2023 322
አዲስ አበባ ፤ ታኅሣስ 14/2016 (ኢዜአ) በኮፕ28 ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ተደረገ። የኮፕ28 ፕሬዚዳንት ሱልጣን አሕመድ አል ጃባር እንዳስታወቁት የተመድ የአየር ንበረት ለውጥ ጉባኤ ተሳታፊዎች “ታሪካዊ ስምምነት” ላይ ደረሰዋል። የተደረሰው ስምምነት ከዚህ ቀደሞቹ የተሻለ፣ ስህተቶችን ያረመና ለተግባራዊነቱ ሁሉም አጽንኦት የሰጡበት ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ። በዚህም ስምምነት የአየር ንበረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ የገንዘብ፣ የፖሊሲና ሰትራቴጂ ቅየሳዎች መካተታቸውንም ተናግረዋል። የታዳሽ ኃይል ተግባራትን ለማከናውን የሚያስችሉ ማዕቀፎች በስምምነቱ ከተካተቱ አንኳር ጉዳዮች አንዱ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል። ኢትዮጵያም በኮፕ 28 ጉበኤ የአየር ጠባይ ለውጥን ለመከላከል እየከወነች ያለችውን ተጨባጭ መፍትኄ በአረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ ያቀረበች ሲሆን መካነ ርዕዩን የሀገራት መሪዎችና የአለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የጃፓን ተመራማሪዎች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የእአምሮ እንቅስቃሴን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ምስል ማግኘታቸው ተነገረ
Dec 19, 2023 389
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፡- የጃፓን ተመራማሪዎች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሠው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሰው ልጅ አእምሮ የድርጊት እንቅስቃሴን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ምስል መፍጠራቸው ተነገረ። የጃፓን ብሔራዊ የኳንተም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንሰቲቲዩት እንዲሁም ሌሎች ተመራማሪዎች የሰው ልጅ አእምሮ ምስል ከሳች እንቅስቃሴ ላይ ባካሄዱት ጥናት አዲስ ውጤት ማግኘታቸው ተነግሯል። ተመራማሪዎቹ ሠው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ባካሄዱት ጥናት በአእምሮ ውስጥ እንዴት ሙሉ ምስል ሊከሰት አንደሚችል የሚያሳዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መገንዘባቸው የተመላከተ ሲሆን የአቦ ሸማኔ ሙሉ ገጽታን፣ የአውሮፕላንን ቅርጽንና የማብራት ምልክቶችን ግልጽ ምስል ማግኘታቸው ነው የተገለጸ። በበዚኅም የሠው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የአእምሮ ምስል ከሳች እንቅስቃሴን በጉልህ የሚያሳይ የመጀመሪያውን ምስል ተመራማሪዎቹ ማግኘታቸውን ዥንዋ ዘግቧል። "የአንጎል ዲኮዲንግ" የሚል ስያሜ በተሰጠው የቴክኖሎጂ ምርምር 1200 ምስሎች እና መሬት ላይ ያሉ ግዑዝ አካላት ከአእምሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተጠና ሲሆን ምርምሩ በአእምሮ እንቅስቃሴ ላይ በመመስረት የሰው ልጅን የማስተዋል ይዘቶች ለማለየት እንደሚያስችል ተነግሯል። የምርምሩ ግኝቶች በቅርቡ በሚታተመው ኢንተርናሽናል ሳይንቲፊክ ጆርናል ለእይታ እንደሚበቃም በመረጃው ተመልክቷል።
በጊኒ ነዳጅ ማጠራቀሚያ ስፍራ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ የሰዎች ሕይወት አለፈ
Dec 18, 2023 379
አዲስ አበባ ፤ ታህሳሥ 8/2016 (ኢዜአ)፦ በጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሬ በነዳጅ ማጠራቀሚያ ስፍራ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። ኮናክሬ በሚገኘው ግዙፍ የነዳጅ ማደያ ዛሬ ሌሊት ከፍተኛ ፍንዳታ መከሰቱንና እስካሁንም መቆጣጠር እንዳልተቻለ ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል። የአይን እማኞች ለሮይተርስ በሰጡት መረጃ ደግሞ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ሌሎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ ተቋማትም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተነገረ ሲሆን ብዙዎች ከአካባቢው በመሸሽ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል። የአደጋ መከላከል እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ የዘገበው ሮይተርስ ኢግናሴ ዲን እንዲሁም ዶንካ የተባሉት ሆስፒታሎች በቁስለኞች መጨናነቃቸውን አመልክቷል። በነዳጅ ማጠራቀሚያው ላይ የተከሰተውን ፍንዳታ ለመቆጣጠር የጊኒ ወታደራዊ ተቋማትና የእሳት አደጋ ሰራተኞች ርብርብ እያደረጉ ስለመሆኑም ዘገባው አስነብቧል። በመረጃው ስለ አደጋው መንስኤ ምንም የተባለ ነገር የለም። ዘግይተው በወጡ መረጃዎች ደግሞ አደጋው ማየሉን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተጠቁሟል።  
ከ60 በላይ ፍልሰተኞች የተሳፈሩበት ጀልባ በመሰበሩ በሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ መስጠማቸው ተገለጸ
Dec 17, 2023 364
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፡- ከሊቢያ ወደብ የተነሱ ከ60 በላይ ፍልሰተኞች የተሳፈሩበት ጀልባ በመሰበሩ ሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ መስጠማቸውን የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ። አይ ኦ ኤም አንዳስታወቀው ፍልሰተኞቹ መነሻቸውን ሊቢያ በማድረግ የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ በተነሳ ከፍተኛ ወጀብ ምክንያት ጀልባው በመሰበሩ እንደሰጠሙ አስታውቋል። ፍልሰተኞቹ ከናይጄሪ፣ ጋምቢያ እና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት የተነሱ ሲሆን ህጻናትና ሴቶች እንደሚገኙበትም ተመላክቷል። ጀልባዋ ከተነሳችበት የሊቢያዋ ዙዋራ ወደብ 86 ሰዎችን አሳፍራ አንደነበር ከምንጮች ማረጋገጡን ድርጅቱ ይፋ ማድረጉን የሬውተርስ ዘገባ ያመላክታል። ከጉዳቱ የተረፉ 25 ሰዎችም የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በዘገባው ተመላክቷል። የአይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ ፈላቪኦ ዲጋካሞ እንዳሉት በያዝነው አመት ብቻ አደገኛውን የሜድትራኒያን ባህርን አቋርጠው ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሞከሩ 2ሺህ 250 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን መግለጻቸውን ጠቁሟል።
በአቧራ ማጽጃ ማሽን ውስጥ የተገኘው የአልማዝ ቀለበት
Dec 13, 2023 394
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 03/2016(ኢዜአ)፦ ከ800 ሺህ ዶላር በላይ ግምት ያለው የአልማዝ ቀለበት ከ48 ሰዓት ፍለጋ በኋላ በአቧራ ማጽጃ ማሽን ውስጥ መገኘቱ ተሰምቷል። በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ የሚገኘው ዘ ሪትዝ ቅንጡ ሆቴል ደንበኛ የሆነችው ማሌዢያዊት ባለሃብት ለፓሪስ ፖሊስ የንብረት ጠፍቶኛል ሪፖርት ተቃርባለች። የተለያዩ እቃዎችን ለመግዛት ገበያ በወጣሁበት ወቅት የአልማዝ ቀለበቴ ጠፍቷል ለዚህም የሆቴሉ ሰራኞች ይመርመሩልኝ ስትል ነው ለፖሊስ ሪፖርት ያቀረበችው። ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በመለየት በሆቴሉ ሰራተኞችና የጥበቃ ክፍል አበላት የአልማዝ ቀለበቱ ፍለጋ የተከናወነ ሲሆን በክፍል አቧራ ማጽጃ ማሽን(ቫኪዉም) ውስጥ ቀለበቱ እንደተገኘ ዩፒአይ ዘግቧል። የሆቴሉ የጽዳት ሰራተኞች ክፍሉን በሚያጸዱበት ጊዜ ማሽኑ በሚያወጣው ነፋስ ቀለበቱ ሊሳብና ውስጡ ሊገባ እንደቻለ ነው የተገለጸው። ቅዳሜለት የጠፋውን ቀለበት በለንድን የምትገኘው ባለንብረት ወደ ፓሪስ መጥታ መውሰድ እንደምትችልም ፖሊስ ገልጿል። ዘ ሪትዝ ሆቴል በፓሪስ ከሚገኙ ቅንጡ ሆቴሎች መካከል አንዱ ሲሆን ለአንድ ምሽት ቆይታ ከ2 ሺህ እስከ 50 ሺህ ዶላር የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ በመረጃው ተመልክቷል።
በቴነሲ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጉዳት የስድስት ሰዎች ሕይወት አለፈ
Dec 10, 2023 332
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፡- በአሜሪካዋ ቴነሲ ግዛት ውሽንፍር የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጉዳት በትንሹ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ። በግዛቷ ከትላንት በስትያ ጀምሮ የተከሰተው ውሽንፍር የቀላቀለ አወሎ ነፋስ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል። አውሎ ነፋሱ መኖሪያ ቤቶችን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና ሌሎች ንብረቶችን ሲያወድም የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉና 23 ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል። ከሟቾቹ መካከል ህጻናትና አዛውንት እንደሚገኙበት ያመለከተው ዘገባው ገሚሶቹ የግዛቷ ዋና ከተማ ናሽቪል ነዋሪ መሆናቸውን አስነብቧል። የከተማዋ ከንቲባ ጆ ፒትስ አደጋውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን አውሎ ነፋሱ ያስከተለውን ጉዳት “እጅግ አደገኛ ክስተት” ሲሉ ገልጸውታል። ችግሩን ለመከላከል ተጨማሪ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን በማሰማራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በቴነስ የተከሰተው አውሎ ነፋስ በአሁኑ ወቅት ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች ከሃይል አቅርቦት ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉም በዘገባው ተመልክቷል።
መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሃገራት በሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ
Dec 7, 2023 356
አዲስ አበባ ፤ ህዳር27/2016(ኢዜአ)፡- መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሃገራት ፈጠራን ማእከል ያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያመጡ በሰው ሃብት ልማት ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ። በአፍሪካ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ በፖሊሲ አውጭዎች፣ በምሁራን እና የልማት አጋሮች እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ትብብር በተዘጋጀው የበይነመረብ የውይይት መርሃግብር ላይ እንደተገለጸው የሰለጠነ ሰው ሃብት አቅም በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘት እና የመንግስት እዳ መጨመር መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሃገራት ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው ተብሏል። በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር ዙዛና ብሪክሾቫ ሽዊድሮዊስኪ “ ሃገራት በሰው ሃብት ክህሎት ላይ በትኩረት መስራትና የትምህርት ስርአታቸውን ከጊዜው ጋር ማራመድ አለባቸው” ያሉ ሲሆን “ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተዋውቆ ምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ መስራት እንዳለበት የተገነዘበ ዜጋ የሚፈጥሩ ከሆነ ካሉበት ማነቆ ፈጥነው መውጣት ይችላሉ” ሲሉ መክረዋል። ወቅቱ የሚጠይቀውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ማቅረብ ያልቻሉት የአፍሪካ ባለ መካከለኛ ገቢ ሃገራት ፈጠራን ማእከል ያደረገ እድገት ለማምጣት እየተቸገሩ መሆኑን ይፋ ያደረገው የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሃገራቱ የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያስመዘግቡም የሰው ሃብታቸው ላይ ከወዲሁ መስራት አማራጭ የማይገኝለት መፍትሄ ነው ብሏል። አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ተቀላቅሎ ባለከፍተኛ ገቢ የመሆን ርእይ ያላቸው ሃገራት መዋቅራዊ ሽግግራቸውን በዘላቂነት ለማሳካት ያግዙናል የሚሏቸውን አዳዲስ ፈጠራዎችና ወቅቱ የሚሰጣቸውን እድሎች አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸውም ኮሚሽኑ መክሯል። ከሌሎች ሃገራት አንጻር እነዚህ ሃገራት መንግስታዊ የእዳ ጫናቸው እያደገ በመምጣቱ ዘላቂ እድገትና ልማት ማስመዝገብ ብሎም ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት የዜጎቻቸውን ህይወት በአስተማማኝ ሁኔታ የመቀየር ጥረታቸው እየተገደበ መሆኑን ያተተው ዘገባው ሃገራቱ አሁን ባለው የገንዘብ ስርአት እምነት እንዲያጡ እያደረጋቸው መሆኑንም አንስቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምሁራን ተመራማሪዎች ፖሊሲ አውጭዎች እና የልማት ባለድርሻዎችን በማካተት ሰፋ ያለ የምክክር ጉባኤ በሞሮኮዋ ማራካሽ ለማድረግ ለሚመጣው የካቲት ቀጠሮ መያዙንም የዥንዋ ዘገባ አመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ከሩሲያ ጋር ያላትን ትብብር ያጠናክራል - ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
Dec 5, 2023 436
አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከሩሲያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ የሚያጠናክረው መሆኑን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ። በሩሲያ ፌዴሬሽን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡሪያት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሩሲያው ፕሬዝዳንት አቀርበዋል ፡፡   አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ፕሬዝዳንት ፑቲን ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመሰረቱ 125 ዓመታትን ያስቆጠሩ ወዳጅ አገራት መሆናቸውን አንስተዋል።   ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በሩሲያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ የተለያዩ የትብብር ስምምነቶች መፈረማቸው ግንኙነቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳሻገረው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ደግሞ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል፡፡
በታንዛንያ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የ47 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ
Dec 4, 2023 317
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፦ በታንዛንያ ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት በትንሹ የ47 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል። የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ከፓስፊክ ውቅያኖስ የሚነሳው ዝናብ አዘሉ የአሌ ኒኖ ክስተት ታንዛንያን ጨምሮ በኬኒያና በሶማልያ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። በሰሜን ታንዛንያም ከቅዳሜ ጀምሮ እየጣለ የሚገኘው ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ዘጋርዲያን በዘገባው አስነብቧል።   በሰሜናዊ ታንዛንያ ካቴሽ ከተማ በተከሰተው አደጋ እስከ ትላንት ምሽት ድረስ በተንሹ የ47 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 85 ሰዎች መጎዳታቸውን ተጠቅሷል። በግዛቲቱ እየጣለ የሚገኘውን ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ተከትሎ የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ያመለከተው ዘገባው ለአካባቢው ነዋሪዎች የማስጠንቀቂያ መልዕክት ከግዛቲቱ የአደጋ መከላከል ኮሚሽን መተላለፉንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም