የትግራይ ክልል ተወላጅ ምሁራን የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መቀሌ ከተማ ሊካሄድ ነው

53
መቀሌ ሀምሌ 6/2010 የትግራይ ክልል ተወላጅ ምሁራን የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ ነው። በትግራይ ክልል በሚገኙ አምስት ዩኒቨርስቲዎችና በክልሉ መንግስት የጋራ ትብብር በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ በኢትዮጰያና በተለያዩ የውጭ ሃገራት የሚገኙ ከአንድ ሺህ በላይ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ይሳተፋሉ። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትና የዩኒቨርስቲዎች አስተባባሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ህይወት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ የሚካሄደው ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ነው። የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በበለጠ ለማሳደግ የሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦችን በማመንጨት ወደ ትግባር የሚቀየርበት አሰራር ለመንደፍ ነው ። በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ምሁራን እውቀታቸውን ለክልሉ ጠቀሜታ የሚያውሉበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል መድረክ እንደሆነም ፕሮፌሰር ክንደያ አስታውቀዋል፡፡ በኮንፈረንሱ  ላይ ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት የሚዳስሱ ጥናታዊ ፅህፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም አመልክተዋል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የኮንፈረንሱ አስተባባሪ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ በበኩላቸው ክልሉን ማልማት የሚያስችሉ ሃብቶችን በመዳሰስ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚሆንበትን አቅጣጫ ማስቀመጥ የውይይት መድረኩ ዋና የትኩረት አጀንዳዎች እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ ''የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዘርፎችን በመለየት በጥናትና ምርምር እንዲደገፉ የክልሉ ምሁራኑ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ይሰራሉ'' ነው ያሉት አስተባባሪው። የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች እውቀታቸውና ክህሎታቸውን  ለህብረተሰቡ ጥቅም ለማዋል ከምሁራን ጋር መሰረታዊ የሆነ ትስስር ይፈጠራል ብለዋል። በኮንፈረንሱ ላይ በአገርቱ ከሚገኙ  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የውጭ ሃገራት ምሁራን፣ የኢዱስትሪ ባለሙያዎች፣ ሲቪክ ማህበረሰብ፣ የመንግስት ኃላፊዎችና  ሚዲያዎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። ማንኛውም  ምሁር በኮንፈረንሱ ላይ እንዲሳተፍና የውይይት መድረኩ ላይ ሃሳቡን እንዲገልጽ መድረኩ ክፍት መሆኑን አስተባባሪዎች ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም