ኅብረተሰቡ ለፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ አቀባበል አንዲያደርግ ተጠየቀ

74
አዲስ አበባ ሃምሌ 6/2010 የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ነገ አዲስ አበባ ሲገቡ ኅብረተሰቡ ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጠየቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አንድነት ለማጎልበት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለፕሬዚዳንቱ አቀባበል እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ኤርትራ አስመራ አውሮፕላን ጣቢያ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል "ለፕሬዚዳንት ኢሳያስም በአዲስ አበባ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ መደገም አለበት" ብለዋል። ኅብረተሰቡ አቀባበል ሲያደርግ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች አብሮነት በሚያጎለብትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን እንዳለበት ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ነገ ከሰዓት ሃዋሳን እንደሚጎበኙ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በሃዋሳም የአካባቢው ኅብረተሰብ ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች ወደ አንድነት እንዲመጡ ያቀረቡት ጥሪ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ በኤርትራ አስመራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህም በሁለቱ አገሮች መካከል ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነት የተጀመረ ሲሆን፤ በተጨማሪም የወደብ አገልግሎት እንዲጀምር ኤምባሲዎች በአዲስ አበባና አስመራ ላይ እንዲከፈቱና የሁለቱ አገሮች አየር መንገዶች ወደ አስመራና አዲስ አበባ በረራ እንዲጀምሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም