ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

105
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2010 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ከፍተኛ የልዑክ ቡድን ይዘው ይመጣሉ ተብሏል። ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂም ዛሬ ማለዳ በተገኙበት የሳዋ 31ኛ የምረቃ መርሃ-ግብር ላይ ዛሬ አዲስ አበበ እንደሚገቡ አረጋግጠዋል። የኤርትራ ቴሌቪዥን እንደዘገበው “የኤርትራ ሕዝብና የእናንተን የሰላም መልዕክት ይዤ  አዲስ አበባ እሄዳለሁ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት በማደስ አዲስ ታሪክ ለመሥራትም የአገራቱ መንግሥታት ቆርጠው መነሳታቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። በሁለቱም አገራት የተጀመረው የሰላም ግንኙነት የቀደመውን ኪሳራ የሚያካክስና አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም እንዲሁ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ በቆይታቸው በዶክተር አብይ አህመድ ከተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ቡድን ጋር ውይይት ያደርጋሉ ብሏል። በዚህም የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ለማጠናከር በቅርብ የተጀመረው ጥረት በሚጠናክርበት ሁኔታ ላይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአስመራ ጉብኝታቸው የተፈረመውን  ስምምነት የሚያከብርና የሚያወድስ መርሃ-ግብር ይካሄዳልም ተብሏል። በፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ የተመራው የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ሲገባ የወዳጅነት መስተንግዶ ለማድረግ በመንግሥት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉም ተጠቅሷል። ሕዝቡም ወንድም ለሆነው የኤርትራ የልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግ መጋበዙ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገሮችና ህዝቦች መካከል የተጀመረውን ጠንካራ ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተወሰደ መልካም እርምጃ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን አዲስ የሠላም እርምጃ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚቀጥለው ሳምንት ከ20 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ በረራውን ያደርጋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም