ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጥንቃቄ መመሪያዎችን የማይተገብሩ ሰዎችን ለማስተማር እየተሰራ ነው

65

አዲስ አበባ ነሐሴ 24/2012 (ኢዜአ) ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጥንቃቄ መመሪያዎችን የማይተገብሩ ሰዎችን ለማስተማር ከፀጥታ ኃይሎች ጋር  በጋራ  እየሰሩ መሆናቸውን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ወጣት በጎፈቃደኛ ማኅበር  ሰብሳቢ ወጣት ጌቱ በስር  እንዳለው የኮሮና ቫይረስ  ስርጭትን ለመግታት  የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው  የትራንስፖርትና የገበያ ስፍራዎች  ተገልጋዮች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ  እየሰሩ ናቸው፡፡

አብዛኛው ኅብረተሰብ ስለ ኮሮና መተላለፊያ ግንዛቤ ቢኖረውም ቸልተኛ እንደሆነ የሚያስረዳው  ወጣት ጌቱ ችግሩን ለመፍታት   ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ሕዝቡ ርቀቱን ጠብቆ እንዲገለገል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል ህዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች በሰዓት 1ሺ200 ሰዎች ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ ማስታጠቢያ ለአገልግሎት ማብቃቱን የሚነግረን በጎ ፈቃደኛው የፈጠራ ባለሙያው  ታምሩ ካሣ ነው፡፡

 አገልግሮቱን በምኒሊክ አደባባይ ለተጠቃሚ ማድረሱን የሚነግረን ወጣቱ ተደራሽነቱን ለማስፋት የገንዘብ ድጋፍ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት  ቢያቀርብም የትብብር ደብዳቤ ከመጻፍ በዘለለ ውጤታማ አለመሆኑን ይገልጻል ወጣት ታምሩ ፡፡

ቴክኖሎጂው ለትምህርት ቤቶች፣ ለሆስፒታሎች፣ ለመዝናኛ ቦታዎችና በርካታ የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጠቀሜታ እንዳለው በመጠቆም ።

የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክበሩ ዱላ በበኩላቸው በፈጠራ ባለሙያው ወጣት ታምሩ የቀረበው  ዲጂታል የእጅ ማስታጠቢያ ለሦስት ወራት ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

ይህን  የእጅ ማስታጠቢያ ቴክኖሎጂውን በሌሎች የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎችም ለማስፋፋት በክፍለከተማውና በወረዳው የባለሀብቶችን ድጋፍ ለማግኘት የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ በማከል። 

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ኅብረተሰቡን የእጅ መታጠብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው እንዲሆን ሲቀሰቅስ መቆየቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

በሥራ ቦታዎችና በንግድ ተቋሞች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት አልኮልና ሳኒታየዝር የማዘጋጀትና የእጅ ማስታጠብ እንዲኖር እየተከታተሉ መሆኑን አቶ ክብሩ አመልክተዋል።

በወረዳው 15 የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት የመለየት ሥራና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንቅስቃሴ መኖሩንም ገልጸዋል።

አንዳንድ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎችም በሚዲያና ቤት ለቤትም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ቢታይም በኅብረተሰቡ ዘንድ በትራንስፖርትና በአገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሲያደርግ አይታይም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም