የልህቀት ማእከላቱ የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ በፈጠራ ማገዝ አለባቸው

85

አዳማ ነሐሴ 24/2012 (ኢዜአ)በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተደራጁ የልህቀት ማእከላት የሀገሪቱን ልማትና የብልፅግና ጉዞ በፈጠራ ስራዎች ማገዝ እንደሚገባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተደራጁ የልህቀት ማእከላት ያሉበትን ሁኔታ ትላንት ጎብኝተዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በወቅቱ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የተደራጁ የልህቀት ማእከላት የሀገሪቱን ልማትና የብልፅግና ጉዞ ለውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆን አለባቸው ።

"ማዕከለቱ የቴክኖሎጅ ማለማጃና ማስፋፊያ ስራዎች በስፋት የሚከናወኑበት ከመሆናቸው ባለፈ የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ገፅታዎች ከመሰረቱ የሚቀይሩ ናቸው" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተደራጁ ስምንት የልህቀት ማእከላት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሰው ኃይል ልማትና  ጥናትና ምርምር ስራዎች ጥራት መጠበቅ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን አመላክተዋል ።

ልማት፣እድገትና ብልፅግናን በማረጋገጥ ሽግግሩን እውን ማድረግ ከማዕከላቱ የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

"በቀጣይ አስር ዓመት ትልቁ ትኩረታችን የሰው ሃይል ልማት ላይ ነው" ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው ማእከላቱ የልማትና ብልፅግና ጉዞን ከውጤት በማብቃት ከኢንዱስትሪዎች ጋር የተጠናከረ ስራ በማከናወን የሴክተሩን ልማት ለማፋጠን የሚያግዙ መሆናቸውን አመላክተዋል ።

ማእከላቱ የመማር ማስተማር ተልዕኮ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያን ልማትና እድገት በሁለት እግሩ እንዲቆም የሚያስችል ዓላማና ተግባር የሚያራምዱ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከተደራጁ ስምንቱ ማዕከላት ውስጥ የህዋ ሳይንስ ፣ፋርማቲካል፣ ማቴሪያል ኢንጅነሪንግ፣ የሲሚንቶና አውቶሞቲቭ የልህቀት ማእከላት በተሻላ ደረጃ ወደ ተግባር መግባታቸውን በጉብኝቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ያደራጃቸው የልህቀት ማእከላት የሀገሪቱን ልማትና የብልፅግና ጉዞ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ስራዎች እንዲያግዙ በ100 ሚሊዮን ዶላር የጥናትና ምርምር ላቦራቶሪ ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተሻለ ደረጃ ወደ ተግባር መግባታቸው የተረጋገጠ የልህቀት ማዕከላት  ውጤታማ እንዲሆኑ  የምርምር ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂዎችና ማሽነሪዎች ከደቡብ ኮሪያ ግዥ እየተፈፀመ መሆኑን አመልክተዋል።

የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂዎችና ማሽነሪዎች ተገጥመው ስራ የሚጀምሩበት የምርምር ፓርክ ግንባታ በ500 ሚሊዮን ብር እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ለሚ የፕሮጄክቱ ግንባታ 92 በመቶ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ቀሪውን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርትና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ  መሆኑን አመልክተዋል።

"የልህቀት ማእከላቱ የሀገሪቷን ልማትና የብልፅግና ጉዞ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ስራዎች ማገዝ እንዲችሉ ብቁ የሰው ሃይል የማዘጋጀት ስራ እየሰራን ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ 161 ዶክተሮች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በውጭ ሀገር እየሰለጠኑ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ዩኒቨርሲቲውን የሳይንስቲስቶችና የቴክኖሎጂ ማፍለቅያ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተመልክቷል ።

ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ብቻ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የመግቢያ ፈተና በመስጠት ያለፉትን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ለሚ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም