በአዲስ አበባ ምክር ቤት ከኃላፊነት የሚነሱ ኃላፊዎችና ዳኞች ጥቅማጥቅሞችን የሚወስን አዋጅ ፀደቀ

61
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2010 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኃላፊነት የሚነሱ የቢሮ ኃላፊዎችና ዳኞች ሊያገኙት የሚገባውን መብትና ጥቅማጥቅሞች ለመወሰን ተሻሽሎ የቀረበለትን አዋጅ አፀደቀ። አዋጁ የፀደቀው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ትናንት ባጠናቀቀው ጉባኤው ላይ ነው። ዳኞችን ጨምሮ ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከኃላፊነት ከተነሱ በኋላ የኑሮ ችግር አንዳይገጥማቸው ማድረግ የአዋጁ ዓላማ ነው። አዋጁ የከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና ምክትል አፈ-ጉባኤዎችን፣  የከተማ ምክር ቤት ፀሐፊዎችን፣ የከተማ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎችንም ያካትታል። በአዋጁ ላይ አንደተመለከተው ከሥራ የሚነሱ ኃላፊዎች አንደየኃላፈነት ደረጃቸውና የአገልግሎት ዘመን ቆይታ የመኖሪያ ቤት፣ ህክምናና ሌሎች አስፈላጊ መሰረታዊ አገልግሎቶችን አንዲያገኙ የሚያስችል ነው። በአሁኑ የሀገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት በአዋጁ የተደነገጉት አንዳንድ ጥቅማጥቅሞች አቅምን ያገናዘቡ አይደሉም ሲሉ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ተከራክረዋል። በሌላ በኩልም የተቀመጡት ጥቅማጥቅሞች ኃላፊዎችም ሆኑ ዳኞች በሥራ ዘመናቸው ህዝቡን በቅንነትና በኃላፊነት እንዲያገለግሉ የሚያበረታታቸው መሆኑን በመግለፅ የአዋጁን መጽደቅ ደግፈው ሞግተዋል። የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ የአዋጁ አንቀፆች ላይ ከተከራከሩ በኋላ አንዳንድ የቀረቡ ሀሳቦችን ለማካተት በመስማማት በ69 ድጋፍ እና በስድስት ድምጸ ተኣቅቦ አዋጁን አፅድቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም