በአማራ ክልል ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ጥራት መጓደል ዋነኛ ተግዳሮት እየሆኑ ነው

64
ባህርዳር ሐምሌ 6/2010 በአማራ ክልል ከገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ጥራት መጓደል ዋነኛ ተግዳሮት እየሆኑ መምጣታቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ የመስሪያ ቤታቸውን የ2010 በጀት ዓመት የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ለክልሉ ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በሚቀርቡ የሀሰት ማስረጃዎች ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች በገጠር መሬት ክርክር በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶችን እያጨናነቁ ይገኛሉ። ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ዳግም ተሻሽሎ ቢተገበርም እስካሁን በሚፈለገው ልክ ችግሩን መቀነስ አለመቻሉን ጠቅሰዋል። ለዚህ እንደአንድ መፍትሄ ያስቀመጡት በወረዳ ደረጃ የተቋቋሙ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤቶችን ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ በሚያስችል መልኩ አደራጅቶ ወደሥራ ማስገባትን ነው። "በክልሉ የተቋቋመው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲም የወንጀል ምርመራን በፎረንሲክና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዞ የፍትህ ስርዓቱን ከሰው ምስክርነትና ጥገኝነት በሂደት ለማላቀቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል" ብለዋል አቶ የኔነህ። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ባለፉት 11 ወራት በየደረጃው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች 663 ሺህ 381 የፍትሃ ብሄርና የወንጀል ጉዳዮች ቀርበው 91 ነጥብ 1 በመቶ ለሚሆኑት ዕልባት ተሰጥቷል። በክልሉ ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ በበኩላቸው "ሴቶችን ጨምሮ በሁሉም እርከኖች ያሉ ዳኞችን አቅም በስልጠና ማጎልበት መቻሉ በውሳኔ አሰጣጥና በፍርድ ጥራት ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል" ብለዋል። በዚህም በፍትሃ ብሄርና በወንጀል ከቀረቡ ጉዳዮች ውስጥ አብዛኞቹ ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ከ18 ሺህ የሚበልጡ ጉዳዮች በዕርቅ እንዲፈቱ የተከናወነው ስራም በመልካምነት እንደሚጠቀስ አመልክተዋል። አቶ አማረ እንደገለጹት በሚቀርቡ ሀሰተኛ ማስረጃዎች አርሶ አደሮች መሬታቸውን እየተነጠቁ ለከፋ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ባደረጋቸው የመስክ ምልከታዎች አረጋግጧል። ከገጠር መሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የይዞታ ማረጋገጫ መረጃን የማጥራት ሥራ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። "ከፍትህ ጋር ተያይዞ በሕብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍም በቀጣይ ሁሉም አጋር አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል። ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ የኔነህ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም