አስኩ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በግጭት ለተፈናቃሉ ዜጎች 16 ቤቶችን ገንብቶ አስረከበ

853

ቡራዩ አምሌ 5/2010 አስኩ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኦሮሚያና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ለተፈናቃሉ ዜጎች 16 ቤቶችን ገንብቶ አስረከበ።

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኘውና ንብረትነቱ የአስኩ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር  የሆነው አኳ አዲስ የመጠጥ ውሃ ፍብሪካ እና ሰራተኞቹ ከኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ በተፈጠረ ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች 16 መኖሪያ ቤቶችን ሰርቶ አስረክቧል።

በዚህ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉና በቡራዩ በሚገኘው መጠለያ ውስጥ ያሉት ተፈናቃዮች ለኢዜአ እንዳሉት ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ከመጡ ጊዜ አንስቶ በከተማ አስተዳደሩ የተሰጣቸው ትኩረትና ድጋፍ ከፍ ያለ  ነው ።

ይህም በእነርሱና በህፃናት ልጆቻቸው ሕይወት ላይ ከሚደርስ ከባድ አደጋ እንዳዳናቸው በመጠቆም ለረዱዋቸው ሁሉ ልባዊ ምስጋናቸው እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

የተቋሙ ኦፕሬሽን አስተባባሪ የሆኑት ባንታየሁ አላምረው እንዳሉት ድርጅታቸው ተፈናቃዮችን ለመርዳትና የማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ስራዎችን እንደ ሰሩ ገልጸዋል።

አኳ አዲስን ጨምሮ ሌሎች በቡረዩ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ ሌሎች ፋብሪካዎች ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል።

በቡራዩ ከተማ በባለሀብቶችና በህብረተሰቡ ተፈናቃይ ዜጎችን ለማቋቋም ሰፊ ርብርብ የተደረገ ሲሆን እስካሁን 629 ቤቶች ተሰርተው 429 አባወራዎች ቤቶቻቸውን ተረክበዋል።