ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የጀመረችው ግንኙነት የነበረውን ችግር በመፍታት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ተገለጸ

828

ሶዶ አምሌ 5/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የቆየውን ችግር ለመፍታት መንግስት  የጀመረው ግንኙነት  የነበረውን ችግር በመፍታት ሀገሪቱን  ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት በወላይታ ሶዶ ከተማ የታሪክና ስነ ዜጋ መምህራን ገለጹ፡፡

የሃገራቱን ግንኙነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ህዝቡ  ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፉን መቀጠል እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡

በሶዶ መሰናዶ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ ደሳለኝ ዳርጋሶ ለኢዜአ እንዳሉት በሁለቱ ሃገራት የነበረውን አለመግባባት ህዝቦቹን የነጠለና የስነ ልቦና ጫና ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

በሃገራቱ መካከል የቆየውን ችግር ለመፍታት መንግስት የጀመረው ግንኙነት  የነበረውን ችግር በመፍታት ሀገሪቱን  ተጠቃሚ የሚያደርጋት ነው፡፡

“የሰላም ሂደቱ ዘላቂ እንዲሆን በሁለቱም በኩል ያሉ ዜጎች የድርሻቸዉን ሊወጡ ይገባል “ያሉት መምህሩ ለዚሀም የፖሊቲካ አመራሩ ድርሻ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኦቶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት መምህርት ብርቅነሽ ብርሃኑ በበኩላቸው “በዕርቅና የሰላም ፍላጎት የሚፈታ አለመግባባት ዘላቂ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው” ብለዋል፡፡

መምህርቷ እንዳስረዱት በዓለም ላይ ያሉ ታላላቅ መንግስታት ከጠላትነት ይልቅ ወዳጅነትንና በመነጋገር ችግሮቻቸውን የመፍታት አሰራር እየተከተሉ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህንን  ዕድል መጠቀሟ መሰልጠኗን ጭምር ያሳያል፡፡

በሁለቱ ወንድማማች ህዝብ መካከል የነበረው አለመግባባት ችግር መፈታቱ ያልተገቡ ውጥረቶችን በማስወገድ የቀጠናውን ሰላም ለመመለስ እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው የታሪክ መምህር ጳውሎስ ባልቻ ” በኑሮ ዘይቤ፣ በኃይማኖት ፣ በቋንቋ በባህልና በተፈጥሮ የማይለያዩ ህዝቦች መገናኘታቸው እንደማይቀርና የህዝቡን ስሜት ለሚረዳ መንግስት ምላሹ ምን እንደሆነ የተገነዘብኩበት ነው” ብለዋል የሁለቱ ሀገራት የአሁኑ ግንኙነት፡፡

የፖለቲካ አለመረጋጋት በስፋት በሚስተዋልበት በምስራቅ አፍርካ መንግስት የወሰደው  ወዳጅነት የማፍራት እርምጃ የነበረውን ችግር በመፍታት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

“የምስራቅ አፍርቃ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ መሪ ሃገር እንደመሆናችን የቀጠናውን ችግር በሰከነ መልኩ መፍታት እንደሚቻልና ሰላምን ለማረጋገጥ ትምህርት ይሆናል ” ብለዋል፡፡

ከማህበራዊና ፖሊቲካዊ ጠቀሜታ ባሻገር የተፈጠረው መረጋጋት በኢኮኖሚ ረገድም ለአከባቢው የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ነው፡፡

እንደ መምህር ጳዉሎስ ገለጻ የተፈጠረው ሰላም መንግስት በወሰደው የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመሆኑ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ መላው ህዝብ በአንድነትና በመደመር መንፈስ ከመንግስት ጎን መቆም አለበት፡፡