ማንም ሰው ሌላ ሰው ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቀኝ ይችላል ብሎ መጠበቅ የለበትም --- ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም

99

አዲስ አበ፣ ባ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ) ማንም ሰው ሌላ ሰው ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቀኝ ይችላል ብሎ መጠበቅ የለበትም ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገለጹ።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭትን አስመልክቶ የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ሰዎች የት እንደሚሄዱ፣ በሚሄዱበት ቦታ ምን እንደሚያደርጉና ከማን ጋር እንደሚገናኙ የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች በጥሞና ማየት እንዳለባቸውም ዶክተር ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

"ምክንያቱም እነዚህ ውሳኔዎች የሕይወትና የሞት ውሳኔዎች ናቸው" ብለዋል።

አንድ ሰው በምርጫው በራሱ ሕይወት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ባይችልም የሚወስነው ውሳኔ በሚወደውና ከዚህ በፊት በማያውቀው ሰው ላይ የሕይወትና የሞት ልዩነት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በቅርብ ሣምንታት ውስጥ በምሽት ክበቦችና ለማኅበራዊ ጉዳዮች ተብለው በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዳግም ማገርሸቱን ዶክተር ቴዎድሮስ አመልክተዋል።

የቫይረሱ ሥርጭት ቀንሶ በነበረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መጥቷል።

"አሁንም ብዙ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ መሆናቸውን ሁላችንም ልናስታውስ ይገባል" ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

የቫይረሱ ሥርጭት እስካለ ድረስ ሁሉም ሰው ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

"ዋናው ጉዳይ ትክክለኛ ውሳኔዎችን መወሰንና ጥሩ ምርጫዎችን ማድረግ ነው" ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ ሰዎች አሁን ያሉበትን ሁኔታም በአግባቡ ማጤን እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በሚኖሩበት አካባቢ ትናንት ምን ያህል ሰው በኮሮናቫይረስ እንደተያዘ ያውቃሉ? ያንን መረጃ የት ማግኘት እንደሚቻል ዕውቀቱስ አላቸው? በቫይረሱ የመጋለጥ ዕድልን ለመቀነስ ምን ማድረግ እንደሚገባስ?

ራስን ለመጠበቅ ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ አንድ ሜትር ይርቃሉ? እጅዎችን አሁንም በመደበኛ ሁኔታ እየታጠቡ ነው ወይ? በአካባቢያቹ ያሉ የጤናና የመንግሥት ተቋማት የሚተላፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ሲሉ ዶክተር ቴዎድሮስ ጥያቄ አዘል ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ማንም ሰው ሌላውን ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቀኝና ደህንነቴን ሊያረጋግጥልኛል ይችላል ብሎ መጠበቅ እንደሌለበትም ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በመልዕክታቸው "ሁላችንም ራሳችንና ሌላውን ከኮሮናቫይረስ የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን" ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሣምንት በፊት "የኮሮናቫይረስ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠፋ ይችላል" ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዓለማችን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ24 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ መሆኑንና ከ837 ሺህ በላይ ሰዎችም ሕይወታቸው ማለፉን ከአሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይኽው የመረጃ ቋት እንደሚያሳየው ከ16 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

በአፍሪካ እስከ ትናንት ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል መረጃ ያሳያል።

ከ954 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

በኢትዮጵያም እስካሁን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 48 ሺህ 140 የደረሰ ሲሆን 758 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 17 ሺህ 415 መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም