የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች በንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት መቸገራቸውን ገለፁ

76
ጊምቢ አምሌ 5/2010 በንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት መቸገራቸውን የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ የነዋሪዎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የኦሮሚያ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታውቋል፡፡ ቅሬታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ በንቲ ደበላ እንደገለፁት በከተማው በተከሰተው የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት አገልግሎቱን የሚያገኙት በሳምንት አንድና ሁለት ቀን ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ንጽህናውን ያልጠበቀ ወራጅ ውሃ ለመጠጥነት በመጠቀም እሳቸውን ጨምሮ ቤተሰባቸው ለጤና ችግር መጋለጣቸውን ገልፀዋል፡፡ የቀበሌ 01 ነዋሪ ወይዘሮ ማርታ ዩሐንስ በበኩላቸው በከተማው ''በተከሰተው የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር በሳምንት በምናገኘው አነስተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ የልጆቻቸውን ንፅህና ለመጠበቅ፣ የቤት ውስጥ ስራን ለመስራትና ንፁህ ውሀ ለመጠጣት አልቻልንም'' ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተሰባቸው ለውሀ ወለድ በሽታ መጋለጣቸውን ተናግረዋል ። ችግሩን አስመልክቶ ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ አስታውቀዋል፡፡ በ02 ቀበሌ የሆቴል ባለቤት ወይዘሮ ኢዲሴ ደለቴራ በበኩላቸው "የንፁህ መጠጥ ውሀ እጥረቱ ለደምበኞቻችንና ተገልጋዩች ተገቢውን አገልግሎት እንዳንሰጥ እንቅፋት ሆኖብናል" ብለዋል። የከተማው ውሀ አቅርቦትና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ጉዲና ኮሉ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ችግሩ የተከሰተው ነባሩ የውሃ ኘሮጀከት አቅርቦት ከፍላጎት ጋር ባለመመጣጠኑ ነው፡፡ ከ15 ዓመት በፊት ለ15 ሺህ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባው የውሃ ኘሮጀክት አሁን ላለው ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪ ማዳረስ ባለመቻሉ የተከሰተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመደበው በጀት ጌሌል ወንዝ ላይ በ2002 ዓ. ም. የካቲት ወር የተጀመረው ፕሮጄክት በሶስት ዓመታት ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ተስፋ ቢደረግበትም ከታሰበው በላይ መጓተቱን ገልፀዋል። የኦሮሚያ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገዘኻኝ ለሜቻ በበኩላቸው በ2002 የተጀመረው የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ኘሮጀክት በ2005 መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም ለአምስት ዓመት መጓተቱን ገልፀዋል፡፡ "የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎቹን ዝርጋታ ለማከናወን የከተማው መሬት አቀማመጥ አመቺ አለመሆን፣ ከተዘረጋ በኋላ በየቦታው በሚያጋጥም የመሬት መንሸራተትና ውሃውን የሚገፉ ፓምፖች በየጊዜው መበላሸታቸው ለፕሮጄክቱ ግንባታ መጓተት መንስኤ ነው" ብለዋል። "ቱቦዎቹን ጨምሮ በተደጋጋሚ በሚበላሹት ፓምፖችና የፕሮጄክቱ ዲዛይን ዙሪያ እየተደረገ ያለው ጥናት በሚቀጥለው ሳምንት ስለሚጠናቀቅ ችግሩን ተረድተን ለረዥም አመታት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየውን ይህንኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ለመቅረፍ የመፍትሄ ሐሳብ እናገኛለን" ብለዋል። በጌሌል ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ይኸው የንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጄክት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጨርስ የገለጸው የቢሮው ምክትል ኃላፊ  እስከ አሁን ከ162 ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀ ለማወቅ ተችሏል። ስራ ሲጀምርም በቀን ከሶስት ሺ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሀ በማምረት እስከ 120ሺ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት አስተማማኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም