በዞኑ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላት ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ ተገለጸ

1261

ደሴ ሀምሌ 5/2010 በአካባቢያቸው ከተገነቡ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ተገቢውን አገልግሎት እንደማያገኙ በደቡብ ወሎ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

የደሴ ዙሪያ ወረዳ  አርሶ አደር ሃሰን አራጋው ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢያቸው የተገነባ ማሰልጠኛ ቢኖርም ምርታማነት የሚያሳድግ እውቀት እያገኙበት አይደለም፡፡

ማዕከሉ  የሙያ ማሻሻያ ስልጠና የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ የማዕከሉ አጥርና  ቤቶቹ ፈራርሰው የእንስሳት መዋያ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከል በአካባቢያቸው ቢገነባም  የስራ ባህል፣ የአመራረት ብቃትና የተሻሻሉ የግብርና አስራሮችን እውቀት እንዲቀስሙ የሚያደርገው እንቅስቀሴ  አጥጋቢ እንዳልሆነ የገለጹት ደግሞ የኩታበር ወረዳ አርሶ አደር እሽቱ ሃሰን ናቸው፡፡

ለማዕከሉ ስራ ማንቀሳቀሻ የሚመደበው በጀት በምን ስራ ላይ እንደዋለ የሚረጋገጡበት ግልጽ አሰራር  ባለመኖሩ ሃብቱን ለብክነት መጋለጡንም ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ሁሴን መሐመድ በበኩላቸው “የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላቱ ሙያዊ ማሻሻያና አዳዲስ አሰራሮችን ማሳያ ጣቢያዎች ናቸው “ብለዋል።

ሆኖም በዞኑ  በተለያዩ ጊዜያት ከተገነቡት 479 የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያለው 31 ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም  አርሶ አደሩ ያነሳቸው ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውን ያመለከቱት ቡድን መሪው አብዛኛዎቹ ማዕከላት አገልግሎት የማይሰጡት በተግባር የተደገፈ ማስተማሪያ የሚሆን በቂ የሰርቶ ማሳያ እና የምርምር ቦታ ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም  ባለሙያው በሚፈለገው ደረጃ ክትትልና ድጋፍ ባለማድረጉ ማዕከላቱ  የሚገባቸውን ጥቅም ሳይሰጡ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

እነዚህን ችግሮች በመገምገም ለማስተካከል የክልሉ መንግሥት ትኩረት በመስጠቱ ማዕከላቱን የማጠናከር ስራ ከመጪው ዓመት ጀምሮ

እንደሚካሄድ ጠቅሰው በቂ ቦታ በመስጠት ማዕከላቱ ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጡ ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡