የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት እንዲጠናከር እንደግፋለን፡- የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት

1154

ጂግጂጋ ሀምሌ 5/2010 የኢትዮጵያና የኤርትራ  መሪዎች  የጀመሩት የፍቅር እና የአንድነት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የሁለቱ መሪዎች የወሰዱትን የእርቅ ሰላም ወሳኔ ከዳር እንዲደርስ  የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

የክልል ምክር ቤቱ አባል አቶ ሙክታር መሐሙድ በሰጡት አስተያየት” የሁለቱ መሪዎች የጋራ ውሳኔ መሰረት ጦርነትን በማስወገድ በልማት እና በሰላም አብሮ መስራትን ያረጋገጠ ተግባር በመሆኑ ከልብ እንደግፋለን” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ከተማ  በኤርትራ መንግስትና ህዝብ የተደረገላቸው አቀባበል ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

” ሁለቱ መሪዎች የህዝቦችን የጋራ ጥቅም በማስቀደም ያለፈውን ጥፋት እና ቂም በቀል በመተው የወደፊት የጋራ እድሎችን በማመላከት ያደረጉት ስምምነት የሚያስደስት ነው ” ብለዋል፡፡

በአስመራ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአቀባበል ሂደት በቴሌቭዥን በቀጥታ መከታተላቸውን በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላው የምክር ቤቱ አባል  አቶ አብዲላሂ አብዲ ጉብኝቱ የሁለቱን ህዝቦች ያስታረቀ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳመለከቱት ዶክተር አብይ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ለዓመታት የነበረውን ጥላቻ በመቀየር በፍቅር እና በመተባበር እንዲቆሙ መንገድ ከፍተዋል፡፡

” በዚህ ተግባራቸው ዶክተር አብይ ከኒልሳን ማንዴላ ቀጥሉ ሁለተኛው አፍሪካዊ የኖፒል ቢስ ተሸላሚ ያደርጋቸዋል ብዬ አምናለሁ ”  ብለዋል፡፡

ሁለቱ ህዝቦች በኃይማኖት፣በባህል እና በስነ ልቡና የሚያስተሳሰራቸው ጉዳዮች  እንዳሉ  ጠቅሰው አሁን የተደረሰው ስምምነት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ ለመጠቀም እና አብሮ ለማደግ ጎልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ  መሪዎች  የጀመሩት የፍቅር እና የአንድነት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ስምምነታቸው ከዳር እንዲደርስ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውቀዋል፡፡