የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስራ ፍቅርና ልምድ እንዲኖራቸው እየረዳቸው መሆኑን በኢሉአባቦር ዞን ወጣቶች ገለጹ

842

መቱ አምሌ 5/2010 በክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸው የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች በማቃለል የስራ ፍቅርና ልምድ እንዲኖራቸው እየረዳቸው መሆኑን በኢሉአባቦር ዞን  ወጣቶች ገለጹ።

ከ110ሺህ የሚበልጡ  ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሰማራታቸው ተመልክቷል።

በመቱ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ ካሉት  መካከል የወለጋ ዩኒቨርስቲ የሶስኛ ዓመት ተማሪ ፍራኦል ጉዲና አንዱ ነው።

ተማሪ ፍራኦል ለኢዜአ እንደተናገረው በከተማዋ የአቅመ ደካማዎችን  ቤት በመጠገን፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና በችግኝ ተከላ ስራዎች እየተሳተፈ ይገኛል።

“ይህም አገልግሎት ያለኝን አቅምና እውቀት ለሌላው ለማካፈልና ማህበራዊ ኃላፊነቴን ለመወጣት ብሎም የስራ ፍቅርና ልምድ እንዲኖረኝ ረድቶኛል” ብሏል፡፡

ወጣቶች እንዳሉት በእረፍት ጊዜያቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸው የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች ከማቃለል ባለፈ የስራ ፍቅርና ልምድ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።

በየዓመቱ በበጎ ፈቃድ  በሚያበረክቱት  አገልግሎቶች ከህብረተሰቡ  ዘንድ ምስጋና ማግኘታቸው ለተሻለ ስራና ውጤት መነሳሳት እንደፈጠረላቸው የተናገረው ደግሞ  ሌላው የከተማዋ ወጣት ምስጋና ገሬ ነው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እንደ ባህል በመውሰድ የሚሰጡትን አገልግሎቶች በዓይነት ለማሳደግ በቀጣይ ጠንክሮ ለመስራት ፍላጎቱ መሆኑንም ገልጿል።

ሌላው የዘንድሮ የበጎ ፍቃድ ተሳታፊ የዳሪሙ ወረዳ ዱጳ ቀበሌ ወጣት መረራ አመና በበኩሉ  “በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየታየ ያለውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እድገቱን ለማፋጠን ባለኝ አቅም ሁሉ እሰራለሁ” ብሏል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ወጋ እንዳመለከቱት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጨምሮ ከ110 ሺህ በላይ  ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለማሳለፍ በ13 ወረዳዎች ተሰማርተዋል።

በሁለት ወራት ቆይታቸውም የአሜሪካ መጤ ተምች በመከላከል፣ለአርሶ አደሩን ማሳ በማረስ፣የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ደም በመለገስና በሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች  ህብረተሰቡን ለማገዝ እየተንቀሳቀሱ ነው።