የኢትዮጵያን የብልጽግና ዓላማ እውን ለማድረግ የአዕምራዊ ንብረት ስርዓቱን ማዘመን ይገባል

83

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የብልጽግና ዓላማ እውን ለማድረግ የአዕምራዊ ንብረት ስርዓቱን ማዘመን እንደሚገባ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በአሥር ዓመት የልማት መሪ ዕቅዱ ላይ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የዕቅዱ የትኩረት መስኮች በሚል ከተለዩት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የዳበረ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ጥበቃ፣ የተጠናከረ የአዕምሯዊ ንብረት ልማት፣ ብቁ የሰው ሃብት ልማትና የላቀ የዲጂታል አገልግሎት ማስፈን የሚሉት ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ''አገር የሚበለጽገው በእርሻ፣ በኢንዱስትሪና በንግድ መሻሻልና በፈጠራ ሥራ ነው።

ይህን ለማሻሻል ደግሞ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ላይ የላቀ ሥራ ማከናወን እንደሚገ አመልክተዋል።

''ኢትዮጵያ የምትፈልገውን የብልጽግና ዓላማ እውን ለማድረግ የአዕምራዊ ንብረት ስርዓቱን በማዘመን የፈጠራ ሥራዎች የሚጠበቁበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል'' ብለዋል።

በመድረኩ ከባለድርሻ አካላት የተነሱ ሃሳቦችን በመሪ ዕቅዱ ላይ በማካተት ዕቅዱን የማዳበር ሥራ እንደሚሰራም አቶ ኤርሚያስ የገለጹት።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የሳይንስና ኢኖቬሽን ዘርፍ አማካሪ አቶ አብዱራዛቅ ኡመር በሰጡት ሃሳብ፣ በተቋሙ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ መስራት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

"ጽህፈት ቤቱ የመረጃ ስርዓቱን ካዘመነና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ አሰራሮችን ከተከተለ የዕቅዱን ግብ ለመምታት ያስችለዋል" ሲሉም አክለዋል።

ጽህፈት ቤቱ በአስር ዓመት የመሪ እቅዱ ወዳሰበው ግብ ለመድረስ ከዚህ ቀደም ከነበረው አካሄድ በተለየ መልኩ መጓዝ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ በግል የአዕምሯዊ ንብረት አማካሪ የሆኑት አቶ ወንደሰን በለጠ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ልምዱ የላላ መሆኑን አስታውሰው፣ "በቀጣይም ውጤታማ ለመሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በተጠናከረ መልኩ መስራት አለበት" ብለዋል።

በፈጠራ ባለቤትነት፣ በንግድ ምልክቶች፣ በቅጂና አመሳስሎ በመስራት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቀነስና በመግታት የተሻለ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ መፍጠር እንደሚገባም በመድረኩ ተወያዮች ተነስቷል።

በአሥር ዓመቱ የዘርፉ ዕቅድ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ጥበቃ ስርዓትን በማጠናከር አገራዊ የኢኖቬሽን እንቅስቃሴን መደገፍ በትኩረት የሚሰራበት ነው።

ዲጂታል የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ልማትና የመረጃ ስርዓት ገንብቶ በመጠቀም ቀልጣፋና ተደራሽነትን ማስፈን በዕቅዱ እንደ ዋና ዓላማ ከተቀመጡት መካከል ናቸው።

በዕቅዱ በአዕምሯዊ ንብረት የአገር ውስጥ ፈጠራን ለማጎልበትና የአገር በቀል እውቀት ልማት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል።

በመድረኩ የኪነጥበብ ስራዎችን በተመለከተ ከቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጋር ተያይዞ የዘርፉ ባለሙያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን በግብዓትነት አንስተዋል።

ለአሥር ዓመቱ የዘርፉ የልማት ግብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን ይህም በዕቅዱ ሊሰሩ ከታቀዱት ፕሮጀክቶች አኳያ በቂ አለመሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም