ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ እየተደረገ ነው

561

አዲስ አበባ አምሌ 5/2010 በጌዲኦና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች ድንበር አካባቢ በተከሰተ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊው እርዳታ እየተደረገ መሆኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ድንበር አካባቢ በተፈጠረው አለመግባባት በጌድኦ ዞን ከ845 ሺህ 653 በላይ ተፈናቃዮች አሉ።

እነዚሁ ዜጎች በ77 ጣቢያዎች በሶስት ክላስተር የተጠለሉ ሲሆን አስፈላጊው የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።

በተመሳሳይ በምእራብ ጉጂ ዞን 185 ሺህ ተፈናቃዮች መኖራቸውንና በ26 ጣቢያዎች መጠለላቸውን ኮሚሽኑ አመልክቶ በሁለቱም ቦታዎች ያሉ ዜጎችን ለመርዳት ብሔራዊ የአደጋ ስጋት የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች በስፍራው ተገኝተው የእርዳታውን ሂደት እየተከታተሉ መሆኑን አመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማስተባበሪያ ማዕከል መቋቋሙንም አስታውቋል።

ማዕከሉ ለነዚሁ ዜጎች ወጥነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የተገለጸው።

በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎች 12 ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በስፍራው መገኘታቸው ነው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያስታወቀው  ።