ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ነባሩ አዋጅ ማሻሻያ እየተደረገበት ነው – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

763

አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2010 ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተጠናከረ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ነባሩን አዋጅ የማሻሻል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የወንጀልና አደገኛ ዕጽ መከላከል ጽህፈት ቤትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አዋጅ ቁጥር 909/2007 ለመተካት በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ አቶ ተካ ገብረጻድቃን በዚሁ ወቅት አንደገለጹት፤ ከሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እንቅስቃሴ መጨመር ጋር ተያይዞ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ማሻገር ወንጀሎች እየተስፋፉ መጥተዋል።

ወንጀሉን በመቆጣጠርና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ፣ በወንጀሉ በመሳተፍ የሚጠረጠሩ ሰዎችን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል፣ ምርመራዎችን የማደራጃት፣ ክስ የመመስረትና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁንና ከወንጀሉ አሳሳቢነት፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ካለው ችግር፣ እንግልት፣ ከወንጀሉ ውስብስነትና ባህርይ አንጻር የተሰሩ ስራዎች አጥጋቢ እንዳልሆኑም ገልጸዋል።

ስለሆነም የወንጀል ተግባሩን በተጠናከረና በተደራጀ ሁኔታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከዚህ ቀደም ይሰራበት የነበረውን አዋጅ ቁጥር 909/2007 መተካት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህም እስካሁን ወንጀሉን ለመከለላከልና ለመቆጣጠር መንግስት በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ተከላካይ ግብረ-ሀይልን በማቋቋም ከአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰራውን ስራ ያጠናክራል ተብሏል።

የህግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት፣ ወንጀሎች ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራት፣ ተጎጂዎችና ከስደት ተመላሾች ላይ የሚሰሩ ስራዎች እንዲጠናከሩና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ተግባራት እንዲከናወኑ ለማድረግ እንደሚያስችል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ተናግረዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ማስረጽ ባለሙያ አቶ ደመወዝ አማን በበኩላቸው አሁን እየተሰራበት ያለው አዋጅ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር የማሻገር ወንጀልን ከመከላከልና ከመቆጣጣር አንጻር ክፍተት እንደነበረበት አስታውሰዋል።

”በተለይ አዋጁ ስደትና ፍልሰትን አንድ አድርጎ ማየቱ፣ ከዋናው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጋር የግልጽነት ችግር መኖሩ፣ ስለ ዋስትና መብት ግልጽ ድንጋጌ አለመኖሩ በክፍተት ከሚጠቀሱ መካከል ናቸው” ብለዋል።

በዋናው ወንጀል አድራጊና በተባባሪው ሰዎች መካከል የተለያዩ የቅጣት መጠን እንዲኖር መደረጉ፣ ፖሊስ በምርምራ ወቅት ስለሚኖረው ጥበቃ፣ በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ወንጀል የተፈጸመበትን ንብረት የማስተዳደር ጉዳይ ሌላው በክፍተት የተለዩ ጉዳዩች ናቸው ።

በመሆኑም አሁን ተሻሽሎ የሚተካው አዋጅ በወንጀል ምርመራ፣ መከላከልና የክስ ሂደት ትክክለኛ ፍትህ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ በነገው እለት የሚቀጥል ሲሆን ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ጠቃሚ ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል።