በዞኑ 12 ሺህ ሄክታር ግጦሽና ሰብል ከአንበጣ መንጋ ነጻ ሆነ

85

ማይጨው፣ ነሐሴ 20 /2012 (ኢዜአ) በትግራይ ደቡባዊ ዞን 12 ሺህ ሄክታር የግጦሽ መሬትና የሰብል ማሳ ከአንበጣ መንጋ ነጻ መደረጉን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የአንበጣ መንጋው ከአንድ ሳምንት በፊት በ9 ሺህ ሄክታር ግጦሽ መሬትና በ3 ሺህ ሄክታር የሰብል ማሳ ላይ ተከስቶ ነበር ።

በመምሪያው የተባይ መከላከል ባለሙያ ወይዘሮ ፍሬ ካልአዩ ለኢዜአ እንደገለጹት መንጋው 1 ሺህ 800 ሄክታር ላይ ለምቶ በነበረ የጤፍ፣ ስንዴና ገብስ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል ።

“በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 13 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በዘመቻ በተካሄደ ባህላዊና ዘመናዊ የመከላከል ስራ አካባቢውን ከመንጋው ጥቃት ነጻ ማቀድረግ ተችሏል” ብለዋል ።

በአንበጣ መከላከሉ ስራ  268 ሊትር ጸረ- ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉንም ጠቅሰዋል ።

የአንበጣ መንጋው አሁንም ዋነኛ ስጋት በመሆኑ አርሶአደሩ ለማሳው እለታዊ ቅኝት እንዲያደርግ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ባለሙያዋ አስረድተዋል ።

በራያ አዘቦ ወረዳ መቻሬ ቀበሌ  አርሶአደር ሰሎሞን ከላሊ ጭስና የሚረብሽ ድምፅ በመጠቀም የአንበጣ መንጋውን ከማሳቸው ላይ ማባረር እንደቻሉ ተናግረዋል ።

መንጋውን በባህላዊ መንገድ ብቻ ለመከላከል አስቸጋሪ ስለሚያደርገው መንግስት በቂ ኬሚካል እንዲያቀርብላቸው መፈለጋቸውንም  አመልክተዋል።

"ጅራፍ በማጮህና በጭፍጨፋ ማሳዬንና አካባቢውን ከአንበጣ መንጋው ነጻ አድርጊያለሁ" ያሉት ደግሞ በራያ አላማጣ ወረዳ የጋርጃሌ ቀበሌ  አርሶ አደር መረሳ አማረ ናቸው።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን በተያዘው  የመኸር ወቅት ከሚለማው 143 ሺህ ሄክታር ማሳ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም