አረንጓዴ ልማትን በማስፋፋት የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን በዘላቂነት መጠበቅ ይገባል... ኢንስቲትዩቱ

77

ሐዋሳ፣ ነሐሴ 20/2012 (ኢዜአ) በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች አረንጓዴ ልማትን በማስፋፋት የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን በዘላቂነት መጠበቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት አሳሰበ።

የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞችና የስራ ኃላፊዎች በሲዳማ ክልል ቦና ወረዳ በሚገኘው የሎጊታ ፏፏቴ አካባቢ  የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አከናውነዋል።

በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለኢዜአ እንዳሉት  በሀገር  ደረጃ የታቀደውን አረንጓዴ ልማት ለማሳካት ተቋሙ በተለያዩ  የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ላይ ችግኝ በመትከል ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

 ዘንድሮ 5 ቢሊዮን ችግኝ በሃገሪቱ ለመትከል የተያዘውን እቅድ መሳካት መቻሉን  ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ 200 ሚሊዮን ችግኝ እንዲተከሉ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በሲዳማ ክልል በመገኘት ችግኝ መትከላቸውን ገልጸዋል። 

በተከላው 100 የሚሆኑ የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች፣ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው  እነዚህ ተጓዦች ከችግኝ ተከላው ባለፈ ለጥናትና ምርምር ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን የመሰብሰብ ዓላማ አንግበው መምጣታቸውን  አስረድተዋል።

 በተለይ የሲዳማ ክልል ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም ያላቸው በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዳሉት የተናገሩት አቶ ገዛኸኝ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳራቸው በዘላቂነት ሊጠበቅ ይገባል ብለዋል። 

በዚህ ረገድ እንደ ሃገር እየተተገበረ ያለውን የአረንጓዴ ልማት ሥራን በየደረጃው ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ባለሙያዎችን በመመደብ የአካባቢውን የቱሪስት ሀብት አጥንቶ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና ለማስተዋወቅ ጥረት ያደርጋል ብለዋል። 

የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀጎ አገኘሁ በበኩላቸው የኢንስቲትዩቱ ማህበረሰብ በአካባቢው ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖራቸው አመስግነው ክልሉ አዲስ የተደራጀ በመሆኑ ከተቋሙ የቴክኒክና ሌሎችንም ድጋፍ እንደሚሻ ገልጸዋል። 

ቢሮው እንደ ሀገር የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ ግብ ለማሳካት የድርሻውን ከመወጣቱም  ባሻገር በተያዘው የበጀት በዓመት የቱሪስት መዳረሻዎች አረንጓዴነታቸው ተጠብቆ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትና ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የቦና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሾንኮራ ሾዴ በወረዳው ካሉ ፏፏቴዎችና መስህቦች በተጨማሪ ከ900 ሄክታር በላይ ጥብቅ ደን እንዳለ አስረድተዋል።

 በፏፏቴው አካባቢ ሎጅ ገንብተው ለቱሪስት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አቶ አማኑኤል አስናቀ በሰጡት አስተያየት ለደን ልማት ትኩረት በመስጠት በሎጁ ዙሪያ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ አካባቢው ሳቢና ማራኪ በማድረግ ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል። 

ይህንን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በሎጁ ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የዕፅዋት ዓይነቶች በመኖራቸው የአካባቢው ሥነ ምህዳር ተጠብቆ ለዱር እንስሳትና አዕዋፍ መኖሪያ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም