ለሱዳን የለውጥ ጉዞ የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ

47

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) ''አንድ ዓመት ባስቆጠረው ለሱዳን የለውጥ ጉዞ ኢትዮጵያ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የጎላ ነው'' ሲሉ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ተናገሩ።

ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በሚመለከት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት እየተከናወነ ያለውን ድርድር እንደምትደግፍም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ረዥም ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች ናቸው።

ሱዳናዊያን የገጠሟቸውን የፖለቲካ ቀውስ ተሻግረው የለውጥ ጉዞ ከጀመሩ አንድ ዓመት ማስቆጠራቸውን አስታውሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚህ ታሪካዊ ጊዜ ጉብኝት ማድረጋቸው ልዩ ክስተት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ሱዳናዊያን ከዚህ ችግር እንዲወጡ ኢትዮጵያ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበረም አስታውሰዋል።

ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች በድርድር እንዲፈቱ በብርቱ እንደምትሻም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዶክተር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ውይይት ስለቀጠናው ሰላምና ልማት እንዲሁም ሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መመክራቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ግድቡን በሚመለከትና በሌሎች የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

በውይይታቸው ስለቀጠናው ሰላም መምክራቸውንም ገልጸዋል።

የሱዳንና የኢትዮጵያ ሁለቱ የለውጥ መንግሥቶች ለቀጠናው ልማት መልካም ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በተጨማሪ ከአገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጀኔራል አብደል ፈታ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም