የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የመለዋወጫ ዕቃ ችግራቸውን እንዲፈቱ 85 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል - ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

61

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) ከሲሚንቶ ምርት፣ አቅርቦትና የግብይት ችግሮችን ለመፍታት በተለይም የፋብሪካዎችን የመለዋወጫ ዕቃ ችግር እንዲፈታ የ85 ሚሊየን ዶላር ወጪ መደረጉን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

አዲስ የግብይት መመሪያ ሰሞኑን ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

ሚኒስቴሩ ባለፉት አራት ወራት ከሲሚንቶ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የተሰሩ ሥራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስቴሩ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።

ዋናው ችግር አቅርቦት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ፋብሪዎቹ በቀን 345 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ማምረት ሲኖርባቸው ምርታቸው ከ200 ሺህ ኩንታል ማለፍ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

እንደ ችግር የተለዩትም የመለዋወጫ ዕቃ መግዣ የውጪ ምንዛሪ እጦት፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የፀጥታ ችግር፣ የዕውቀትና የክህሎት እንዲሁም የትራንስፖርት ችግር መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተረጋጋ የአሰራር ሥርዓት አለመኖር፣ የሥርጭት ሥርዓቱ ሕገወጦች የበረከቱበት መሆኑ እንዲሁም ሕገወጥ ማከማቻዎችና ምርት መደበቅ የመሳሰሉ ችግሮች መታየታቸውን ጠቁመዋል።

ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ መቆየታቸውን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

''ከድንጋይ ከሰል ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታትም በአገር ውስጥ ለማምረት ተሞክሯል'' ያሉት አቶ መላኩ፤ የኤሌክትሪክ ችግር በተወሰነ ደረጃ መቅረፉንና የፀጥታ ችግርም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ፋብሪካዎች የመለዋወጫ ችግራቸውን እንዲቀርፉ 85 ሚሊዮን ዶላር ለዕቃ ግዢ እንዲውል መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

የሲሚንቶ ሥርጭት ችግርን ለመፍታት አዲስ የግብይት መመሪያ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ማሰራጨት እንዲገቡ መደረጉንና የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲሚንቶ በአግባቡ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ችግሩን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሁን ኢትዮጵያ በዓመት የሚያስፈልጋት የሲሚንቶ መጠን 11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ሲሆን ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ነው።

ይህንን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ጥቅምት ድረስ የፋብሪካዎች አማካይ የማምረት አቅምን ወደ 63 በመቶ አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ ታቅዷል።

ከጥቅምት በኋላ ደግሞ ይህንን አቅማቸውን ወደ 85 በመቶ የማድረስ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ''እስከዛ ግን ችግሩ እንዳይባባስ ሲሚንቶ ከውጪ እንዲገባ ይደረጋል'' ብለዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ከዚህ ጎን ለጎን በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ደግሞ አዳዲስ ፋብሪካዎችን መገንባትና ነባር ፋብሪካዎችን የማስፋፋት ሥራ ይሰራልም ብለዋል።

እነዚህ ሂደቶች የሚሳኩ ከሆነ ደግሞ በረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ ሲሚንቶ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ትችላለች ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም