አስፈፃሚ አካላትን መከታተል እና ሪፖርቶችን ማጣራት የሚያስችል አዲስ አሰራር ሊዘረጋ ነው

53
አዲስ አበባ አምሌ  5/2010 አስፈፃሚ አካላትን መከታተልና ሪፖርቶችን ማጣራት የሚያስችል አዲስ አሰራር እንደሚከተል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ። አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ዛሬ ለጋዜጠኞች አንደተናገሩት በቀጣዩ አመት አስፈፃሚ አካላትን የሚከታተሉበትና ሪፖርቶችን የሚያጣሩበት አዳዲስ አሰራሮች ይተገበራሉ። በመለኪያ መስፈርት ላይ መስርቶ አስፈፃሚውን አካል የመቆጣጠርና የመከታተል ስራ ይሰራልም ብለዋል። የመለኪያ መስፈርቶች እንደተዘጋጁና ሪፖርቶች ሲቀርቡ ክርክር ተደርጎባቸው በድምፅ ብልጫ የሚፀድቅበት አሰራር እንደሚጀመር ተናግረዋል። የሪፖርቶችን እውነትነት ለማጣራትም ከቋሚ ኮሚቴዎች ጋር የሚሰራ የባለሙያዎች ቡድን እንደተደራጀ ገልፀዋል። ሪፖርት በየሩብ አመቱ ከሚቀርብ ይልቅ በየወሩ እንዲቀርብ ይደረጋልም ብለዋል። መረጃዎች በመረጃ ቴክኖሎጂ፣በሞባይልና ህትመት ውጤቶች ለህዝብ የሚደርሱበት አሰራሮችም ይዘረጋሉ። ቋሚ ኮሚቴዎች በእውቀት ላይ ተመስርተው አስፈፃሚ አካላትንና ፕሮጀክቶችን እንዲገመግሙ የሪፎርም ስራዎች እተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። አባላቱ ከተወካዮቻቸው ጋር የሚገናኙት በአመት ሁለት ጊዜ በመሆኑና ይህም በቂ ባለመሆኑ የመረጃ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሁሉም ባለበት ጥያቄውን የሚያቀርብበትና ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር ይጀመራልም ብለዋል። የምክር ቤቱ አባላት በምክር ቤቱ የእረፍት ጊዜ የተጀመሩ ሀገራዊ ለውጦች ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ከህዝቡ ጋር እንደሚመክሩም አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልፀዋል። ለውጡ በአጭር ጊዜ የሚታይ ውጤት እንዳመጣ ሁሉ ለውጡን የሚገዳደሩ ተግዳሮቶች እንደሚታዩ ጠቁመው የምክር ቤቱ አባላት በለውጡ ሂደት ችገሮቻቸውን ከሀዝብ ጋር ለመለየት ይሰራሉ ብለዋል። ''ተጨማሪ ለማግኘት ያለንን ማጣት የለብንም'' ያሉት አፈ ጉባኤዋ  ፍላጎትን በሀይል ለማስከበር ከመጣር ይልቅ ስርዓት ባለው መንገድ መወያየት እንደሚገባ አሳስበዋል። የምክር ቤቱ አባላትም የህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ህዝቡን ባሳተፈና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማሳካት የህብረሰተቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ከህዝቡ ጋር ይመክራሉ ብለዋል። በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረትና ሀዝቡ ሰላሙንና ፀጥታውን ራሱ እንዲጠብቅ የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚካሄዱ፣በየአካባቢው ያሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለይተው እንደሚመለሱ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም