የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ሠራተኞች የ3 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ

74

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ሠራተኞች ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ የሚውል የሦስት ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ፡፡

ሠራተኞቹ በመዝናኛ ክበባቸው አማካኝነት ቦንድ የገዙበትን የሦስት ሚሊዮን ብር ቼክ ዛሬ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስረክበዋል።

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶከተር ኤባ አባተ እንዳሉት ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የተቋሙ ሠራተኞች የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል።

ግድቡ የአገሪቱን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያግዝና በተለይ ለጤናው ዘርፍ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

"የኃይል መቆራረጥ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱ በየዕለቱ የሚስተዋል መሆኑን መረዳት ይገባልም " ብለዋል።

ዶክተር ኤባ የጥናት ውጤቶችን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት፣ እንደ አውሮፓወያን አቆጣጠር በ2019  ለኃይል አቅርቦት እንጨትን በማገዶነት በመጠቀም 67 ሺህ ዜጎች በሳምባ ምች፣ በሳንባ ካንሰርን፣ በልብ ሕመምና መሰል በሽታዎች ሕይወታቸው አልፏል።

"በቤት ውስጥ አየር መበከልና ተያይዘው በሚከሰቱ በሽታዎች ምክንያትም ባለፉት 30 ዓመታት ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ለሞት እንደተዳረጉም ጥናቶች ያመላክታሉ" ብለዋል።

በመሀል ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች ሳይቀር በላቦራቶሪዎቻቸው፣ በቀዶ ሕክምናና በክትባት ክፍሎቻቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በመሆናቸው በኃይል መቆራረጥ ሕሙማን ለአደጋ የሚጋለጡበት አጋጣሚ እንዳለም አመልክተዋል።

የዜጎችን የልማት ጥያቄ ለመመለስና እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኢኒስቲትዩቱ ሠራተኞችና ኢኒስቲትዩቱ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማመን ይህን ድጋፍ ለማድረግ መነሳታቸውን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና የጽሕፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ኃይሉ አብረሃም፣ ኢኒስቲትይቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ያለበትን አገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አስታውሰዋል።

"ከዚህ ጎን ለጎን ይህን መሰል ተግባር መፈጸሙ የሚያስመሰግነው ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብና የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል አተኩራ እየሰራች መሆኑን ጠቁመው፣ "ኢኒስቲትዩቱ እነዚህን ሁለት ተግባራት በአንድ ጊዜ ማስኬዱ ለልማትና ለአገር ፍቅር ያለውን ስሜት ያሳያል" ብለዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመንግሥት ሠራተኛውና የተቋማት አስዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግድቡን ለማጠናቀቅ 39 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ለዚህም የኅብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ኃይሉ እንዳሉት የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ሙሌት መጠናቀቅ በፈጠረው መነሳሳት ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ 117 ሚሊዮን ብር ገቢ ከተለያዩ አካላት ተሰብስቧል።

ከተሰበሰበው ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 51 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በ8100 የተገኘ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም