ቻይና ለልማት ስራዎች 250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጠች

71
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 ቻይና በኢትዮጵያ የልማት ስራዎችን ለመደገፍ 250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ሰጠች። የብድር ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂና ፈርመዋል። ውይይቱን የተከታተሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እንዳሉት ብድሩ የተገኝው በመቀሌ የመጠጥ ውሃ እጥረትን ለመፍታት የተቀረፀውን ፕሮጀክት ለማሳካት ነው። ፕሮጀክቱ የመቀሌን የመጠጥ ውሃ ችግር በመፍታት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል። ብድሩ ወለድ አልባና ቀላል ብድር ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ቻይና በአዲስ መልክ ለአፍሪካ አገራት ከምታበድረው ገንዘብ ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ እንደሚይዝ ተገልጿል። በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት 100 ሚሊዮን የቻይና ገንዘብ (ዩዋን) የሚያወጣና ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል የእርዳታ እህል ለመለገስ ስምምነት መፈረሙን አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም