ለአገሪቱ አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ስኬት በችግኝ ተከላ የጀመርነውን ተሳትፎ አጠናክረናል... በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሠራተኞች

75
ጭሮ ሀምሌ 5/2010 አገሪቱ ለምትከተለው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ስኬት በችግኝ ተከላ የጀመሩትን ተሳትፎ ዘንድሮም አጠናክረው መቀጠላቸውን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች አስታወቁ። የዞኑ መንግስት ሠራተኞች በጭሮ ወረዳ ኢፈባስ ቀበሌ በመገኘት ትናንት ችግኝ ተክለዋል። ሠራተኞቹ በዚህ ወቅት እንዳሉት በየዓመቱ በዘመቻ መልክ በተካሄደው የችግኝ ተከላ ሥራ በመሳተፍ አገሪቱ ለተያያዘችው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። ከሠራተኞቹ መካከል የጭሮ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ጽህፈት ቤት ባልደረባ አቶ ኢዮብ አዲሱ እንዳሉት በየዓመቱ በገጠርና በከተማ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ሥራ ተሳትፈዋል። የችግኝ ልማቱ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ለመገንባት ለምታደርገው እንቅስቃሴ ወሳኝ በመሆኑ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ዘንድሮም አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል። ከዓምስት ዓመት በፊት በመኖሪያ ቤታቸው በግል የተከሏቸው ችግኞች በአሁኑ ወቅት ዛፍ ሆነው በጥላነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ በአካባቢያቸው የነበረውን ሙቀት በመከላከል ነፋሻ አየር እንዲኖር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። "የችግኝ ተከላ ስራው የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ ባሻገር ለኑሮ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው" ያሉት ደግሞ የወረዳው ሠራተኛና ማህበራዊ ዋስትና ጽህፈት ቤት ባልደረባ አቶ አብዲጀባር ከማሉ ናቸው። የመኖሪያ ቄያቸው በተደጋጋሚ በጎርፍ ይጠቃ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አብዲጀባር፣ ችግኝ በአካባቢው በስፋት መትከል ከተጀመረ ወዲህ  የጎርፍ አደጋ እየተቃለል መምጣቱን ገልጸዋል። የመንግስት ሠራተኛውና ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል በችግኝ ተከላ ሥራ ያሳየውን ተሳትፎ ችግኙን በመንከባከብ መድገም እንዳለበት ገልጸው በራሳቸው በኩል ለእዚህ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በጓሯቸው የተከሉት የፍራፍሬ ችግኝ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ይርገዱ ሚሊዮን የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው። በወረዳው በተካሄደው ችግኝ ተከላ ሥራ ላይ የተሳተፉት የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ ዴሬሳ በበኩላቸው የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ ሥራ በጥራትና በተሻለ ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ሁሉም ሰው የተከለውን ችግኝ በመንከባከብ እንዲያሳድግና በእዚህም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ መሆን እንዲችል በየደረጃው ያለው ዓመራር የቅርብ ክትትል እንዲደረግ አሳስበዋል። በተያዘው የክረምት ወራት ብቻ ከ166 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በ476 ሺህ 877 ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ ለመትከል ታቅዶ ከወዲሁ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም