በኢትዮጵያ 43 በመቶ የሚሆነው መሬት የመረጃ ምዝገባ ተካሄዷል

89

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ 43 በመቶ የሚሆነው መሬት የመረጃ ምዝገባ የተካሄደበት መሆኑን የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ። ቀሪውን የአገሪቱ የመሬት መረጃ በመጪዎቹ 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መዝግቦ ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተጠቁሟል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በገጠርና በከተማ የተሟላ የመሬት መረጃ መኖሩ ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው።

የገጠር መሬት መረጃ ተመዝግቦ አርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መያዙ ይዞታውን በአግባቡ እንዲያውቅ ከማድረጉ በላይ መሬቱን እንዲንከባከብና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የሚያስችለው መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የከተማ መሬት መረጃ መመዝገብ ለከተማ ማስተር ፕላን ዝግጅትና ለሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የጠቆሙት።

በመሆኑም በገጠርና በከተማ የሚካሄደውን የመሬት ምዝገባ የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሲደግፍ መቆየቱን ዶክተር ቱሉ አስታውሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ በገጠርና በከተማ የመሬት መረጃ እያመረተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የመሬት መረጃ ምዝገባ በአራት ክልሎች መካሄዱን ጠቁመው፤ በአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ የመረጃ ምዝገባ መካሄዱን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ ያሉ ቢሮዎች መረጃውን በመውሰድ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠት መጀመራቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በዲጂታል ኢንፎርሜሽን መልክ በአየር ፎቶግራፍ የተደገፈ የመሬት መረጃ ምዝገባ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

የአየር ፎቶ ግራፍ ሽፋኑን በማሳደግ የመሬት መረጃ በከፊል የተመዘገበባቸውና ምንም ያልተመዘገበባቸው ክልሎች ላይ በስፋት እንደሚሰራ ዶክተር ቱሉ ጠቁመዋል።

የመሬት መረጃ ምዝገባ ሽፋኑ በአሁኑ ወቅት 43 በመቶ መሆኑን ገልጸው፤ ቀሪውን 57 በመቶ ከአምስት እስከ አስር ባሉት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተለያዩ የከፍታና የቶፖግራፊ እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ገጽታዎችን የሚያሳይ የመሬት መረጃ እያመረተ እንደሚገኝ ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም