ኬንያና ጋና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ለመተግበር የመጨረሻውን ስምምነት አጸደቁ

84
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 ኬንያና ጋና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ለመተግበር የመጨረሻውን ስምምነት ያጸደቁ የመጀመሪያዎቹ አገራት ሆነዋል። አገራቱ በተወካዮቻቸው አማካኝነት የስምምነቱን የመጨረሻ ክፍል ዛሬ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተፈራርመዋል። የአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ ይረዳል የተባለው ይህ ነጻ የንገድ ቀጠና ስምምነት ባለፈው መጋቢት በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ጉባሄ ላይ በ44 የህብረቱ አባል አገራት መፈረሙ ይታወሳል። ስምምነቱን ወደ ተግባር ለማስገባት ቢያንስ 22ቱ አገሮች በራሳቸው ህግ አውጪ አካል ማጽደቅ የሚገባቸው ሲሆን የመጀመሪያዎቹ የሆኑት ኬንያና ጋና ዛሬ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተፈራርመዋል። በአፍሪካ ህብረት የንግድና የኢንዱሰትሪ ኮሚሽነር ሚስተር አልበርት ሙቹንጋ አገራቱ አሁን የሚፈርሙት ከራሳቸው የውስጥ ህግ ጋር በማጣጣም ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን ለማሳየት ነው ብለዋል። ሌሎቹ አገሮችም እንደሚፈርሙት ተስፋ አለኝ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ቀጣይ ፈራሚዋ ሩዋንዳ እንደሚትሆን ይጠበቃል ብለዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣዮቹ 12 ወራት ቢያንስ የ22 አገራት ስምምነት ተቀብለን ወደ ተግባር እንገባለን ብለዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በበኩላቸው የስምምነት ፊርማው ነፃ ንግድ ቀጠናውን ለመተግበር "ህጋዊ መሰረትና አገራቱ ያላውቸን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው" ብለዋል። ሌሎች አገራትም ስምምነቱን በፍጥነት መፈረምና ወደ ተግባር እንዲገባ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና በአፍሪካ አጀንዳ 2063 ከተያዙ ግንባር ቀደም ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፥ አፍሪካን በኢኮኖሚ ውህደት ብልፅግናቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ እድል ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም