የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በምሁራንና ዲፕሎማቶች አንደበት

2846

ምህረት አንዱዓለም /ኢዜአ/

የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ከረጅም ጊዜ በኋላ በምስራቅ አፍሪካ የተካሄደ ድንቅ ውሳኔ መሆኑን ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተቀባብለው ዘግበውታል፤ ምሁራንና ግለሰቦችም በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችንና ትንታኔዎችን በመስጠት ላይ ናቸው።

ይህ ሁለቱ ሀገራት ወደ መግባባት የመጡበት ወሳኝ ሂደት አፍሪካን በጠብመንጃ አንጋችነትና በጥይት ጩኸት ስኬት ላይ ማድረስ እንደማይቻል ያሳየ ድንቅ ምሳሌ ነው ተብሏል።

የኢትዮ ኤርትራን የሰላም ስምምነትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የለውጥ ጉዞ አስመልክቶ የኬንያው ኔሽን ቴሌቪዥን (NTV) አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጨምሮ የአፍሪካ ምሁራንና ዲፕሎማቶችን አወያይቷል፡፡

ምሁራኑና ዲፕሎማቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምስራቅ አፍርካን እና የአፍሪካን ጂኦ ፖለቲካ የሚወስነውን ስምምነት ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ ጋር ማድረጋቸው እና የዚህ ድንቅ ውሳኔ ዋና ባለቤት መሆናቸው ያስመሰግናቸዋል ነው ያሉት።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ የወዳጅነት ስምምነት ከረጅም ጊዜ በኋላ የተፈፀመ አስደሳች ስምምነት ነው። ለዚህ ስምምነት እውን መሆን ቀዳሚው ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ከተወያዮቹ መካከል በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ ኢንስቲቲዩት መምህርና የዓለም አቀፍ ጥናቶች ተመራማሪ ዶክተር ኢማኑኤል ኪሲንጋኒ አንዱ ናቸው።

ምሁሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፉት ሶስት ወራት ያመጧቸው ለውጦች ለቀጠናው ጂኦፖለካ የሚኖረውን አወንታዊ ሚና ጠቅሰው የሰላም ኖቤል ሽልማት ይገባቸዋል እስከማለት ደርሰዋል።

አምባሳደር ዲና በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጀመሩት ጉዞ እንዲሳካ ባለፉት ሶስት ወራት ህዝቡን በማግባባት ረገድ የተሳካ ስራ መስራታቸውን ለተወያዮቹ አብራርተውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጀመሩት የለውጥ ጉዞ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የቀጠናውን ሀገራት የማስተሳሰርና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከሶማሊያ ጋር ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲጀመርና ይህን የሚመጥን አመራር መፈጠር እንዳለበት ከፕሬዝዳንት መሀመድ ፋርማጆ ጋር መወያየታቸውንም በማሳያነት አቅርበዋል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ሰላም አውርደው የሀገሪቱን ችግር እንዲቀርፉ ጥረት መጀመራቸውም ሌላው ለምሳሌነት የሚበቃ ተግባር ነው፡፡

ይህን ዓይነት የመደመርና ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት የማይፈልጉ ሃይሎችንም ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸውን ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት። አምባሳደር ዲና ፖለቲካ ህዝብን ለማገልገል ብቻ የሚውል መሳሪያ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የስልጣን ቆይታ ገደብ እንዲኖረው ያላቸው አቋም፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የጀመሩት ጥረትና የእስረኞች መፈታት የለውጦቹ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከተቃራኒ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ተቃዋሚ ከማለት ይልቅ ተፎካካሪ በሚል አቅራቢ መጠሪያ መጥራታቸውም ትልቅ ፖለቲካዊ መልዕክት እንዳለው ነው ያነሱት።

በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የኬሲኤ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በመከላከያና ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተመራማሪ ተመራማሪው  ፕሮፌሰር ኖህ ሚዳምባ እንዳሉት ደግሞ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት ለአፍሪካ ጦርነት እንደማይበጅ አመላካች ነው።

“በአፍሪካ ሁል ጊዜ ተኩስ አለ፤ ዓላማው ግን ጉዳት እንጅ ጥቅም አይደለም” የሚሉት ፕሮፌሰር ሚዳምባ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት አቁመው የወዳጅነት ስምምነት ላይ መድረሳቸው በአፍሪካ ጦርነትን በማቆም ወደ ሰላም የመምጣት ጅማሮ ነው” ብለዋል። “የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችም የምትመኙትን ሰላም በማግኘታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ፕሮፌሰሩ።

በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር አዚዝ አሞን ቻ በበኩላቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት መቼ እንደሚሆን ለመገመት አዳጋች እንደነበር ጠቅሰው ይህ የእርቀ ሰላም ሂደት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር እውን ሆኖ ማየታቸውን አድንቀዋል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ የረጅም ጊዜ አለመግባባት ለቀጠናው ፈታኝ እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ጥሪ መሰረት ሁለቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን በሰላምና ወዳጅነት ስምምነቱ ቋጭተውታል፡፡

የለውጡ አቀንቃኝ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ ወደ ስልጣን እንዲመጡ የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ በማስተላለፋቸውም ምስጋና ቸረዋቸዋል፡፡

የኤርትራና የኢትዮጵያ የድንበር ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ስምምነት ላይ መደረሱ ለደቡብ ሱዳንና ለሱዳን ትልቅ ትምህርት ይሰጣል ያሉት አምባሳደሩ፥ ለውሳኔው ተግባራዊነት ላሳዩት ቁርጠኝነትም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕከት አስተላልፈዋል፡፡

የደህንነትና የግጭት አፈታት ተመራማሪው ዶክተር ሙስጠፋ የሱፍ አሊ  እንደሚሉት ደግሞ በጠላትነት ከመፈራረጅ ወጥተው የጀመሩት ግንኙነት ለሁለቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም መልካም አጋጣሚ ነው።

ሁለቱ ሀገራት ከ20 ዓመት የቅራኔ ጉዞ በኋላ የጀመሩት ወዳጅነት ለደቡብ ሱዳንና ለሱዳን፣ ለሶማሊያ፣ ለኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ለቡሩንዲ ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥም ነው ዶክተር ሙስጠፋ ያነሱት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአመራር ችሎታ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻርም ሆኑ ሌሎች  የቀጠናው መሪዎች የሀገሮቻቸውን ችግር በምን መልኩ መፍታት እንዳለባቸው መልካም ተሞክሮ እንደሚያስተላልፍም አስገንዝበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሳይቀረፍ የቆየው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መቋጫ እንዲያገኝ በማድረጋቸውም ሊመሰገኑ ይገባልም ነው ያሉት ዶክተር ሙስጠፋ።

የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ኤረስተስ ምዌንቻ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ስምምነት እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑ ተገቢ እንዳልነበር አንስተው ውሳኔው ተግባራዊ መደረጉ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ጉዞ አካታችና ሁሉን አቀፍ መሆኑን አብራርተዋል። የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም እና የወዳጅነት ስምምነት በተናጠል የሚነሳ ስኬት ሳይሆን በሀገር ውስጥ ያለው የለውጥ ሂደት አንድ አካል መሆኑንም ተናግረዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ዘላቂ እንዲሆንም በሰጥቶ መቀበል የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ትኩረት እናደርጋለን ነው ያሉት።

“ስምምነቱ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦችና ቤተሰቦች እንዲወሃዱ እየተደረገ ነው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በቀጣይ ሳምንት ወደ አስመራ የበረራ አገልግሎት ይጀምራል፤ ሌሎች ስምምነቶች በተከታታይ ገቢራዊ ሲሆኑ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም ዘላቂ ይሆናል” ብለዋል። የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲመኘው እንደነበርም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ አስመራ  ባደረጉት ውይይትም በቀላሉ የድንበር ጉዳይ ላይ ሳይሆን ሌሎች የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸውን አንስተዋል። ሁለቱ ሀገራት ለህዝቦቻቸው የጋራ ጥቅም  በአንድ ላይ በሚሰሩበት አግባብ መምክራቸው የኢትዮጵያና የኤርትራን የወደፊት ግንኙነት ምሉዕ እንደሚያደርገውም እምነታቸውን ገልጸዋል። የመሪዎቹ ወደ ሰላምና ወዳጅነት መምጣት የሁለቱን ህዝቦች የትስስር ፍላጎት እውን በማድረግ ትልቅ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።

አምባሳደር ዲና እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሶስት ወራት ህዝቡ የጀመሩትን የለውጥ ሂደት ደግፎ ከጎናቸው እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተሳካ ስራ ሰርተዋል፡፡ በህዝቡና በመሪው መካከል የተፈጠረው መግባባትም  የለውጥ ጅማሮው ውጤታማ ለመሆኑ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡