የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም በድሬዳዋ የህግ ታራሚዎች ጠየቁ

49
ድሬደዋ ሀምሌ 5/2010 እየተፈጸመባቸው ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም በድሬዳዋ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ጠየቁ፡፡ በድሬዳዋ ሁሉን አቀፍ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች  ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በማረሚያ ቤቱ አንዳንድ አመራሮችና አባላት ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሞባቸዋል ፡፡ አለአግባብ  እየተጠሩ  በመደብደባቸው በጨለማ ቤት ውስጥ በሰንሰለት ለረዥም ጊዜ እግራቸው በመታሰሩ በሰውነታቸው ላይ ጠባሳና  ህሊናቸውም መጎዳቱን ገልጸዋል፡፡ ከተራሚዎቹ መካከል ቶማስ ሙስጠፋ ለአራት ዓመታት በጨለማ ቤት መታሰሩን ጠቅሶ በጠባብ ቤት ውስጥ እስከ 12 ሰዎች ታጭቀው እንደሚኖሩ ተናግሯል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ  የመጸዳጃ ቤቱ ለመጠቀም አዳጋች ከመሆኑም በላይ  በቂ ውሃም ባለመኖሩ ቆይታቸው ፈታኝ እንደሆነባቸው ገልጿል፡፡ "የህግ ጥሰት ተፈጽሞብናል ብለን አቤቱታ ስናቀርብ የተለያዩ ሰበቦች እየተፈለጉ ወደ ቃሊቲና ዝዋይ እንወሰዳለን፤ እንደበደባለን" ፤ ያለው  ደግሞ ታራሚ ጀይለን መሐመድ ነው፡፡ ሌላው ታራሚ በፍቅር አዳነ በበኩሉ "የአመክሮ ጊዜ ስንጠይቅ እንከለከላለን፤  የዝውውርና የህክምና  መብቶች እየተጣሱ ናቸው" ብሏል፡፡ የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ ደህንነት ኃላፊው ፈራጅም ሻሪም እሳቸው በመሆናቸው በአድሎ እንደሚያደረሱባቸው ነው ያመለከቱት ፡፡ "ወደ ማረሚያ ቤቱ ከመምጣቴ በፊት በፖሊስ ጣቢያ ስምንት  ወራት ታስሬ ነበር፤ ይህን የእስር ጊዜዬን ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚያመጣልኝ በመጥፋቱ ሊፈቀድልኝ አልቻለም፤ ፖሊስና ማረሚያ ተቀናጅተው በመስራት የታራሚውን መብት ሊያስጠብቁ ይገባል " ሲል ሌላው ታራሚ  ኢሊያስ  ተስፋዬ ገልጿል፡፡ ታራሚ ይርጋለም አስራት በሰጠው አስተያየትም  ፖሊስ ሰድበሃል ተብሎ ጭለማ ቤት እንዲገባ በመገደድና  በድብደባ ብዛት በመማረር እራሱን ያጠፋ እንዳለ ተነግሯል፡፡ "ለህጻናት ተመጣጣኝ ምግብ ከማጣት በቀር የሴቶች ማረሚያ ቤት አያያዝ ጥሩ ነው"  ያለችው ታራሚ  እስታሄል ፌይሰል ከሁለት ጨቅላ ልጆቿ ጋር ማረሚያ ቤት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ማረሚያ ቤቱ ህጻናቱ የተሻለ ምግብ የሚያገኙበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁማለች፡፡ ታራሚዎቹን  በመወከል የተናገሩት ታራሚ  ቴዎድሮስ ታደሰ በማረሚያ ቤቱ ድብደባ ፣ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዳለ፣  የአመክሮና የይቅርታ አሰራር እንደሚጣስ ገልጿል፡፡ አንዳንድ የፍትህ አስከባሪዎች የታራሚዎችን አካል መጉዳት፣ የህክምና በደል ፣በቅርቡ ደግሞ  የምግብ አቅርቦቱ መበላሸት ጨምሮ ሌሎችም የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ ታራሚዎቹ ሰብአዊ መብቶቻቸውን የጣሱና ለአካል ጉዳት የዳረጓቸው ሰዎች ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡም ጠቁመዋል፡፡ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሁሉን አቀፍ ማረሚያ ቤት አመራሮች መካከል ዋና ሱፐር ኢንተንዴንት ገብረሥላሴ ስብሃቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "ማረሚያ ቤቱ በ2009ዓ.ም. የወጡ የአመክሮ፣ የዝውውር፣ የዲሲፕሊን፣ የቤተሰብ ግንኙነት መመሪያዎች ተከትሎ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል፡፡ የታራሚዎች ፍላጎትና ጥያቄ ከመመሪያዎቹ ጋር የሚስማሙ ባለመሆናቸው መመሪያዎቹን ታራሚዎች እንዲያውቁት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ "እኔ ወደ አመራር የመጣሁት በ2008 ዓ.ም. ነው፤ ተቋማችን በሁሉም መንገድ የተሟላ ባይሆንም እኔ እስከማውቀው  በድብደባ ጥርሱን ያጣ አንድ ሰው ብቻ አውቃለሁ፤ ችግሩን የፈፀመው ከስራው ለጊዜው እንዲታገድ ተደርጓል ፤ከዚህ ውጪ የለም " ብለዋል፡፡ የተሃድሶ ልማት ዘርፍ ማስተባበሪያ ኃላፊና የአስተዳደሩ ተወካይ ዋና ሱፐር  ኢንተዴንት ኃይሉ ለገሰ  ለጋዜጠኞች ሟቾቹ ራሳቸውን  እንዳጠፉ የሚገልፅ የህክምና የምስክር ወረቀት አሳይተዋል፡፡ ታራሚዎቹ ያቀረቧቸውን ዓይነት ኢሰብዊ ድርጊት ተፈጽሞ ከሆነ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ተገቢው እርምት እንደሚወሰድ የተናገሩት ዋና ሱፐር  ኢንተዴንት ኃይሉ ፤ ሁሉም ከህግ በታች በመሆኑ ተጠያቂነትን አንግቦ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከህክምና ፣ከመኝታ፣ ከምግብ አቅርቦትና ከህጻናት አልሚ ምግብ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡ "በአዲሱ ዓመት ወደ ተገነባው ዘመናዊ ማረሚያ ቤት ሽግግር ስለሚደረግ የሚነሱ ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ይፈታሉ "ብለዋል፡፡ እርስ በርስ በሚፈጠር ግጭት ሳቢያ አጥፊውን ወደ ማግለያ ቤት እንደሚልኩ ጠቅሰው ጥበትን ለማስቀረት አዳዲስ ክፍሎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ነው የገለፁት፡፡ የጋዜጠኞችን ጉብኝት ተከትሎ በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን የተመራ የአስተዳደሩ ካቢኔና የድርጅት አመራሮች  ታራሚዎችን ተመልክተዋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም