ኦነግ ለሰላም ውይይቱ ስኬታማነት ግዜያዊ የተኩስ አቁም አወጀ

120
ሐምሌ 5/2010 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተጀመረውን የሰላም ውይይት ለማሳካት ግዜያዊ የተኩስ አቁም ማወጁን ገልጿል። በግንባሩ ሊቀመንበር የሚመራ የልዑካን ቡድን ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባደረገው ውይይት ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄዱንና ለሰላማዊ ትግል ዝግጁ  መሆኑን  ግንባሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል። በመንግስት እና በግንባሩ መካከል የተጀመረውን የሰላም ንግግር መንግስታት፣ ህዝቦችና ሰላም ወዳዶች የሚሹት መሆኑን ግንባሩ በመግለጫው ገልጿል። የተጀመረውን የሰላም ንግግር ወደፊት ለማራመድና ለማሳካት ይረዳል በሚል እምነት በጊዜያዊነት ተኩስ ማቆሙንም አስታውቋል። ይህ የተኩስ ማቆም አዋጅም የተጀመረው ንግግር የሚጠበቀውን ፍሬ  አፍርቶ በቀጣይ ግንባሩና መንግስት በጋራ የተኩስ ማቆም አዋጅ  ያውጃሉ የሚል እምነት እንዳለውም  ነው የተገለፀው፡፡ የግንባሩ የነፃነት ሰራዊትም የተላለፈውን አዋጅ በያለበት ተግባራዊ እንዲያደርግም የግንባሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መመሪያ ማስተላለፉን መግለጫው ያስረዳል። የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ማንኛውም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል። በዚሁ መሰረት የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ አመራሮች ለሰላማዊ ውይይት ሀገር ውስጥ  ገብተዋል። ጥሪውን ተከትሎም ግንቦት 7 ማንኛውንም ሰላማዊ ያልሆነ ትግል ማቆሙን  ሰሞኑን ገልፆ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ኦነግ፣ኦብነግና ግንቦት ሰባትን ከአሸባርነት ዝርዝር ውስጥ መሰረዙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም