በአፍሪካ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ሲመልሱ ደህንነታቸው ተጠብቆ መሆን አለበት - ተመድ

104

ነሃሴ 15/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ አገራት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ሲመልሱ ጥንቃቄና ደህንነትን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አሳሰበ።

የዓለም ጤና ድርጅትና ዓለም አቀፍ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የአፍሪካ አገራት መንግስታት ተማሪዎችን ወደ ትምሀርት ገበታ ሲመልሱ ለኮቪድ-19 እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ በማድረግ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል ሲባል ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉ በተለይ በአፍሪካ የሚፈጥረው ተፅእኖ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል።

ትምህርት ቤቶች ብዙ አፍሪካውያንን ወደ ስኬት ያደረሰ መንገድና ብዙ ህጻናት በፈተናዎች ውስጥ ሆነው እንዲያድጉና እንዲጎለብቱ መጠለያ እንደሆናቸው የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስ ማቲሺዲሶ ሞኤቲ ገልጸዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን "የትውልድ ክስረት" እንዲመጣ እድል መስጠት የለብንም ብለዋል።

አገራት የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እንደከፈቱት ሁሉ ትምህርት ቤቶችንም በዛው መልክ ዳግም መክፈት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶችን ዳግም የመክፈት ውሳኔ ሊመጣ የሚችለውን አደጋና መፍትሄን ያመላከተ ሳይንሳዊ ትንተና ሊመራ እንደሚገባም ነው ሚስ ማቲሺዲሶ ያስረዱት።

ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳብ የህጻናት፣ የመምህራንና ወላጆች ደህንነት እንዲጠበቅና አካላዊ ርቀትን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወሰድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በ39 የአፍሪካ አገራት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 6 አገራት ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ለመሉ ሲከፍቱ 19 አገራት ደግሞ በከፊል መክፈታቸውን አረጋግጧል።

በ14 አገራት ትምህርት ቤት ከፍተው ድጋሚ የዘጉ ሲሆን በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም 12 አገራት ትምህርት ለመጀመር እቅድ እንዳላቸው የዳሰሳ ጥናቱ አመላክቷል።

በትምህርት ቤቶች መዘጋት በተፈጠረው መስተጓጎል ህጻናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ለጭንቀት እንዲሁም ለጥቃትና ብዝበዛ ተጋላጭነታቸው መጨመሩን ዩኒሴፍ ገልጿል።

በምስራቅና በደቡባዊ አፍሪካ አገራት በህጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት መጨመሩንም አስታውቋል።

በአፍሪካ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት የትምህርት ቤት ምገባ በመቆሙ የሚያገኙት የተመጣጠነ የምግብ መጠን ቀንሷልም ተብሏል።

በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ህጻናት ይበልጥ ተጎጂ መሆናቸውን ዩኒሴፍ አመልክቷል።

የዓለም ባንክ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፈሪካ አገራት የትምህርት ቤቶች መዘጋት በረጅም ጊዜ የሚኖራቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አመላክቷል።

በአፍሪካ ትምሀርት ቤቶችን የሚከፈቱበትን ጊዜ ማራዘም በህጻናቱና በወደፊት ህልውናቸው ላይ እንዲሁም በሚኖሩበት ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ የዩኒሴፍ የምስራቅ ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ሞሐመድ ማሊክ ፎል ገልጸዋል።

ህጻናት ከትምህርት ቤት መቅረታቸው ያስከተለውን ጉዳት መቀነስ ከተቻለና በኮቪድ-19 ወረርሽኝን ያሉ መረጃዎችን በአግባቡ አጢነን እርምጃዎችን ከወሰድን ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ይችላሉ ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የህጻናት መርጃ ድርጅት እና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ፌዴሬሽን በትምህርት ቤቶች ኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበትን መመሪያ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

መመሪያው አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ፣ የትምህርት ቀን መጀመሪያና መጨረሻ ላይ ማሻሻያ ማድረግ፣ መቀመጫዎችን ማራራቅና እጅን ለመታጠብ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን ማሟላትን ያካትታል።

የመማሪያ ክፍሎችና አጠቃላይ የትምህርት ቤቶችን ገቢ ማጽዳት እንደሚያስፈልግም አመላክቷል።

የዓለም የጤና ድርጅትና የዓለም አቀፍ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በቅርቡ በወጣቱት ሪፖርት በአፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የውሃና የንጽህና አገልግሎቶቹን አያገኙም።

ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች 25 በመቶው ብቻ መሰረታዊ የንጽህና አገልግሎት ያላቸው ሲሆን መሰረታዊ የአካባቢ ንጽህና የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ከ50 ከመቶ በታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጠቀሱትን ችግሮችና እጥረቶች ለመፍታት በፈጠራ አስተሳሰብና መዋዕለነዋይን በማፍሰስ እንዲፈታ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ሁለቱ ተቋማት አመልክተዋል።

የዓለም አገራት ኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከላከል በወሰዱት የትምህርት ቤቶችን የመዝጋት እርምጃ  ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት እንዲያቆሙ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም