ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአራት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

88

አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2012(ኢዜአ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የግሪክ፣ ጀርመን፣ ሱዳንና ሞሪታኒያ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ ተቀበሉ። 

በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጀማል ኤል ሻኪ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፤ "በቆይታዬ የሁለቱን እህት አገራት ግንኙነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እሰራለሁ" ብለዋል።

የጀርመኑ አምባሳደር ስቴፋን ኦውር በበኩላቸው የቅርብ ግዜ እቅዳቸው ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት መደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ለማገዝ ደግሞ ሀገራቸው የ120 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

ድጋፉ የቫይረሱ ስርጭት በተለይ በቴክስታይል ዘርፍ ላይ የሚያስከትለውን ስራአጥነትን በመከላከል ለኢኮኖሚ መረጋጋት የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪ በድጋፉ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪ በቆይታቸው ረዥም ዘመን የተሻገረውን የኢትዮ-ጀርመን ሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ነው ያወሱት።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የግሪክ አምባሳደር አና ፋሮና የሞሪታኒያ አምባሳደር ካህጂቱ ምባረክም በቆይታቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነትይ ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጠናው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ህብረት ያላትን አቋም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከአራቱም አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻ ማስታወቃቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ለውጥ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ  ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቷ በአጭር ጊዜ  ውስጥ የሹመት ደብዳቤያቸውን ተቀብለው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ይሁንታ መስጠታቸው እንዳስደሰታቸው አምባሳደሮቹ መግለጻቸውንም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም