በሁለቱ አገራት መካከል እርቀ-ሰላም መውረዱ ከልጆቻቸው ጋር በቀላሉና በፍጥነት መገናኘት እንደሚያስችላቸው ኤርትራውያን አዛውንች ተናገሩ፡፡

53
አዲስ አበባ አምሌ  5/2010 በሁለቱ አገራት መካከል እርቀ-ሰላም በመውረዱ ከልጆቻቸው ጋር በቀላሉና በፍጥነት እንዲገናኙ የሚያስችላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ኤርትራውያን አዛውንቶች ተናገሩ፡፡ አስታያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የ72 እና የ73 ዓመት አዛውንቶቹ አቶ አብርሃም ገብረእግዚ እና አቶ ዮሴፍ ወልደሚካኤል እንደተናገሩት ለዓመታት የተለዩአቸውን ልጆች ለመጠየቅ ከኤርትራ ተነስተው አዲስ አበባ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። ሁለቱ አገራት ሰላም እንዲሆኑና ከናፈቋቸው ልጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ በየዕለቱ የሚያደርጉት የጸሎት ምላሽ እርቆባቸው አገር ዞረው አዲስ አበባ ከገቡ ሁለት ወር አልሞላቸውም። በደካማ ጉልበታቸው ከአገር አገር እየተዘዋወሩ አዲስ አበባ ለመድረስ ከወራት በላይ የፈጀባቸውን ጊዜ፣ ያወጡትን ገንዘብና ድካም አምላክ ይቁጠረው ይላሉ። የዘመናት ጸሎታቸው በአምላክ ፈቃድና በቁርጠኛ አመራር ዛሬ ምላሽ አግኝቶ በሁለቱ አገራት መካከል እርቀ-ሰላም በመውረዱ መደሰታቸውን ሲቃ በተናነቀው ድምጽ ይናገራሉ። ዛሬ አገር ለአገር ዞረው ሳይሆን በኢትዮጵያ አውሮፕላን አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ልጆቻቸውን ይዘው ኤርትራ ሊገቡ መሆኑን ሲያስቡት ደግሞ ደስታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን በደስታ ስሜት ውስጥ ሆነው በእንባና በሳቅ ታጅበው ይናገራሉ። "የዓመታት የጸሎታችን ምላሽ አግኝቷል፤ ደስ ብሎናል" ብለዋል። ከሁለቱ አገራት ጸብ በፊት አዲስ አበባ በተደጋጋሚ የሚመጡት ሁለቱ ኤርትራውያን ጓደኛሞች ከቤተሰቦቻቸው አልፈው አገርና ምድሩ ይናፍቀን ነበር ብለዋል። ዛሬ ለሁለቱም ለአገራት ወንድማማች ህዝቦች "የንጋት ጸሃይ ወጣ" የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በቀጣይ እጅና ጓንት ሆነው ለአገራቸው ሰላምና ብልጽግና እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሁለቱን አገራት ሰላም ከማረጋገጥ ባለፈ ለጎረቤት አገራትና ለአፍሪካ ሰላም ሰፊ ስራ እንደሚሰሩ እምነታቸውን ገልጸው፤ ፈጣሪም እንዲያግዛቸው ጸሎት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ኤርትራውያኑ ወጣት ቶማስ ፍስሃዬ እና ዝግባለ መረሳ በበኩላቸው "የሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ተራርቆ የነበረውን ህዝብ ከማቀራረብ ባለፈ ወጣቱ ተዘዋውሮ እንዲሰራ መልካም አጋጣሚ  ይፈጠራል" ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም