የተፈጠረው ሰላም ከቤተሰቦቻችን ጋር ለመገናኘት መነሳሳት ፈጥሮብናል... ኤርትራዊያን ስደተኞችና ኢትዮጵያዊያን

48
ሽሬ እንዳስላሴ ሓምሌ 5/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም መውረዱ ለበርካታ ዓመታት የተለያዩትን ቤተሰብ ለማግኘት መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ኤርትራዊያን ስደተኞችና ኢትዮጵያዊያን ገለጹ። በሁለቱ አገራት መካከል ከሃያ ዓመት በላይ የነበረው ውዝግብ ተወግዶ በአሁኑ ወቅት ሰላምና ፍቅር በመንገሱ የቤተሰብ ናፍቆታቸውን ከወዲሁ በስልክ መወጣት እንደጀመሩም ተናግረዋል። ፊልሞን ተስፋ የተባለ ኤርትራዊ ስደተኛ እንዳለው ለበርካታ ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል ነግሶ የቆየው ውጥረትና የጦርነት ስጋት ተወግዶ በአሁኑ ወቅት የሰላም አየር መንፈስ መጀመሩ ለሁለቱም ህዝቦች ዘረፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግሯል። " የቤተሰቦቼን የዓመታት ናፍቆት ለመወጣት ስልክ መደወል ጀምሪያለሁ” ያለው ወጣቱ ሁለቱ አገራት ወደ ሰላም መምጣታቸውን በቴሌቪዥን መስኮት ድንገት ሲመለከት የተለየ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገራትና ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለዓመታት የቆየው የጥላቻና የመራራቅ መጥፎ ስሜት ተወግዶ ሰላምና ፍቅር ሲያብብ በማየቱ ልዩ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል። " በአሁኑ ወቅት በስልክ ያገኘሁት ወንድሜን በቅርቡ በአካል እንደማገኘው ጽኑ እምነት አለኝ ” ሲልም ገልጿል። " ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደሰላም በመምጣታቸው ዛሬ ታላቅ ወንድሜን በስልክ አግኝቼዋለሁ፤ ከቀናት በኋላ ደግሞ በአካል ሄጄ እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ " ያለው ደግሞ ሌላው ኤርትራዊ ስድተኛ ወጣት ዘመንፈስ ኃይሉ ነው። በሁለቱ መንግስታት የተጀመረው በጎ የሰላምና የፍቅር ግኑኝነት በህዝቦች መካከልም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመሪዎች የዘለለ ግንኙነት መመስራት እንደሚገባ ተናግሯል። ከቅሬታና ተለያይቶ ከመኖር የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩን ከሁለቱ አገራት ያለፉት ዓመታት ታሪክ በመማር ቀጣይ የጀመሯቸውን የሰላም ጉዞ ለማጠናከር ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አመልክቷል። በአገራቱ መካከል ዳግም ሰላም መስፈን ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በተጨማሪ በድንበር አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎችና በስደት ለሚኖሩ ኤርትራዊያን ልዩ ትርጉም ስላለው አገራቱ የደረሱበትን ስምምነት እንደሚደግፍ ገልጿል። የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪና የ64 ዓመቷ ወይዘሮ ሮማን ገብረአብ በበኩላቸው፣ "በእዚህ ዕድሜዬ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ውዝግብ ተወግዶ በምትኩ ሰላምና ይቅርባይነት ተተክቶ ማየቴ ትልቅ ፀጋ ነው" ብለዋል። በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው ሰላም ከሃያ ዓመት በላይ በአካል ያላገኟቸውን ታናሽ ወንድማቸውን በስልክ ለመገናኘት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የፍቅር፣ የሰላምና የይቅር ባይነት መርህ ለዓመታት በአገራቱ መካከል የነበረውን ቅራኔ በመፍታት አዲስ ግንኙነት እንዲጀምሩ ማድረጉንና ይህም ተስፋቸውን እንዳለመለመው አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም