በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን 323 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እየለማ ነው

58
ባህርዳር ሀምሌ 5/2010 በአማራ ክልል በኩታ ገጠም እርሻ አንድ ሚሊዮን 323 ሺህ ሄክታር መሬት በዋና ዋና ሰብሎች የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንየ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በኩታ ገጠም የሚለማው ሰብል በአብዛኛው ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውል ነው። እስካሁን በተከናወነው የዘር ስራ 332ሺህ 431 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በሚለሙ የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች ዘር ተሸፍኗል። በቀጣይም ቀሪውን መሬት ሳይንሳዊ አሰራሩን ተከትሎ እንዲለማ በቅርበት በሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል። በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ምክረ ሃሳቡን መሰረት ያደረገ የማዳበሪያ ግብዓት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቁመዋል። ''ኩታ ገጠም የሰብል ልማት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በጋራ ለመጠቀምና በማሳ ላይ ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ ለአርሶ አደሩ በመስጠት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው'' ብለዋል። በምርት ዘመኑ በኩታ ገጠም ከሚለማው መሬት ከ45 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በቀጣይ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ባለሙያዋ አስረድተዋል። በወንበረማ ወረዳ የዋዝንክስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አምሳሉ ቆለጭ በሰጡት አስተያየት በኩታ ገጠም የአሰራር ዘዴ ለማልማት በዕቅድ ከያዙት አራት ሄክታር መሬት ግማሽ ያህሉን በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል። ቀሪውን መሬትም በተመሳሳይ ዘዴ በስንዴ ሰብል ለማልማት ማሳቸውን አለስልሰው ለዘር ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት የተሻሻሉ አሰራሮችን ተጠቅመው በበቆሎና ስንዴ ካለሙት ሶስት ሄክታር መሬት 110 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ዓመትም በኩታ ገጠም ለሚያለሙት መሬት በምክረ ሃሳቡ መሰረት ምርታማነት ለማሳደግ 22 ኩንታል ማዳበሪያ መግዛታቸውን አስታውቀዋል። አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ ለማልማት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የጠጠር ጥጃ ጎጥ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተመስገን ደሴ ናቸው። አንድ አይነት ሰብልን ለማልማት የተዳራጁ አርሶ አደሮች ከሐምሌ 11 ጀምሮ ዘሩን በአንድ ቀን ለመዝራት የእርሻ ማሳቸውን እስከ አምስት ጊዜ አለስልሰው ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ''ሰብልን በኩታ ገጠም ማልማት ለተባይ አሰሳ፣ ለዘር ስራና የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን በጋራ ለመጠቀም ያግዛል'' ብለዋል። ባለፈው ዓመት በክልሉ በኩታ ገጠም ከለማው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ከሚጠጋ መሬት 40 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው በረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም