በምዕራብ ጉጂ ዞን 32 የኦነግ ሸኔ አባላት ከነ ሙሉ ትጥቃቸው እጃቸውን ለመንግስት ሰጡ

144

ነገሌ፤ ነሐሴ 13/2012(ኢዜአ) የጥፋት ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 32 የኦነግ ሸኔ አባላት ከነ ሙሉ ትጥቃቸው በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ እጃቸውን ለመንግስት ሰጡ፡፡

ኦሮሞን ነጻ እናውጣ በሚል ሽፋን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን የመግደል፣ የህዳሴውን ግድብን የማደናቀፍና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማትን የማጥቃት ተልእኮ ተቀብለው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

እጃቸውን ከሰጡ የኦነግ ሸኔ አባላት መካከል አቶ ገልማ ቡሌ በትግል ስም ዲናራሳ የተባሉት የጥፋት ተልእኮውን ለማሳካት ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የጥፋት መንገድን በመከተል የክልሉን ህዝብ ነጻ ማውጣት እንደማይቻል በመገንዘብ፣ ችግርም ካለም በውይይትና በድርድር በመፍታት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እጃቸውን እንደሰጡም ገልጸዋል፡፡

"እኔ ሸኔን ሽፍታ እንኳን አልልም፤ ሽፍታ ቢያንስ ስም አለው፤ ሽፍታ ተዋግቶ ገድሎ ይሞታል፤ የሸኔ ተግባር ግን የሌብነት ተግባር ነው፤ ወንድምን ከወንድም የማጋጫት ተግባር ነው። ኦሮሞ ለረጅም ዓመት ሲታገልለትና ሲመኘው የኖረውን እንዲሁም አሁን በእጁ የገቡትን ጥቅሞች ከእጁ ለማውጣት ቋንቋ ለውጠው ጫካ የገቡ ናቸው፤ ለዚህም ከህወሃት ጋር አብረው እያደረጉ ያሉ እንጂ ለምንም ስልጣን እየተፋለሙ አይደሉም፤ ለዝርፊያ እየተሯሯጡ ነው ሌባን ደግሞ መከላከል ይቻላል።" በማለት ገልጸዋል። 

ሌላው አበበ ጂሎ በትግል ስም አብዲ ሰባ የተባለው ደግሞ 'ኦሮሞ ተበድሏል' በሚል ተታሎና ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ለጥፋት ተልእኮ ኦነግ ሸኔን እንደተቀላቀለ ተናግሯል፡፡

የኦነግ ሸኔ ዓላማ የሰው ህይወት ማጥፋት፣ መዝረፍና በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረስ በመሆኑ በዚህ ተግባር መቀጠል ስላልፈለኩ እጄን ለመንግስት ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡

"እኔ መጀመሪያ አርሶ አደር ነበርኩ፤ ትምህርትም ተምሬ ወደ ቤተሰቤ ተመልሼ በመስራት ላይ እያለሁ ሸኔዎች ሲመጡ፤ በብሔሮች ግጭት ምክንያት ብለው ነው የገባንበት፤ተግባራቸው ዝርፊያና አስገድዶ መድፈር ነው እንጂ ለነጻነት አይደለም፤ ትግል ብለው አይደለም፣ ኦሮሞ አይደለም ስልጣን የያዘው፣ የሌላ ወገን ነው በማለት አታለውን ነው፤ አባትህን ጠላት ነው ግደለው ፣ ወንድምህ ጠላትህ ነው የገደለው እያሉ በማታተል ነው፤ ጉዞዋ ዓላማ ቢስ ነው፤ እንዲህ ነው ሲያታልለን የቆየው።" ይላል። 

ሌላው ኣጋ አረቦ በትግል ስም ቄራንሶ ሰባ የኦነግ ሸኔ የትግል ስልትና ዓላማ  ከኦሮሞ ባህላዊ ስርዓት ያፈነገጠና የክልሉን ህዝብ የማይመጥን በመሆኑ ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሻለሁ ብሏል፡፡

የሰው ህይወት እያጠፉና የመሰረተ ልማትን እያወደሙ ለኦሮሞ ህዝብ እታገላለሁ ማለት እራስን ማታለል ስለሆነ ከዚህ በኋላ ዳግም እንደማይሳሳትና እንደማይቀበለውም  ገልጿል፡፡

አጋ እንደገለጸው"ቡራቡሬ ልብስ ለብሶ ይመጣና እኛ ነን መንግስት ይላል፤ ባርነት ስር ነበራችሁ፤ ዛሬ ግን ነጻነታችሁን እናጎናጽፏችኋለን፤ ወደ እኛ ተመለሱ ብዙ ነገር እናደርግላችኋለን፣ ሀገራችሁን እንዳትለቁ አድርገን በደንብ እናሰለጥናችኋለን ይላሉ፤ ይኸንን አምነን ከገባንበትና ከሰለጠንን በኋላ ተመልሶ ይኸ መንግስት ሲዘርፋችሁ ሲበዘብዛችሁ የቆየ መንግስት ነው አሉን፤  ጦርነት ከሶማሌ ይነሳል፤ ከአባይም ይነሳል፣ በዚያ ጊዜ እናንተ እዚሁ ታጣቂዎችን ትዋጋላችሁ አሉን። እንዲ በማለት እኛን ካስገበረን በኋላ የልቡን ማድረግ ፈልጎ ነው።"

የኦሮሞ አባ ገዳዎችና ቃሉዎች ኦነግ ሸኔ ሰላማዊ የትግል አማራጭ እንዲከተል  ጥያቄ አቅርበው እንደነበርም  አስታውሷል፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን አሰተዳደሪ አቶ ተፈሪ ወንድይፍራው በኦሮሞ ህዝብ ስም ጫካ መሽጎ የሰው ህይወት የሚያጠፋ፣ ንብረት የሚዘርፍና የመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርስን ሃይል አንታገስም ብለዋል፡፡

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በኦነግ ሸኔ ተመልምለው በህዝብ ላይ ጥፋት ሲፈጽሙ የነበሩ ወገኖች ዓላማው ሲገባቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በገላና ወረዳ ኤሬንሳ ቀበሌ የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 32 የኦነግ ሼኔ አባላት ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ለመንግስት እጃቸውን እንደሰጡም አረጋግጠዋል፡፡

ከኦነግ ሸኔ የጥፋት አጀንዳ ተቀብለው  የሚሰማሩ የጥፋት ኃይሎችን የዞኑ ህዝብ በየቀኑ እያጋለጠና አሳልፎ እየሰጠ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም