በአዲስ አበባ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ የቀጣይ ሥራችን ነው -- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

97

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 12/2012 ( ኢዜአ) አዲስ አበባ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ ለጎብኚዎች ማራኪ ለማድረግ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትጋት እንደሚሰሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ወይዘሮ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 8ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንዳሉት አገርና ህዝብን ማገልገል ከባድ ቢሆንም መታደል ነው።

አዲስ አበባ ከተማን እንደ ስሟ አበባና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በታማኝነትና በቅንነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባን ምቹና ማራኪ ለማድረግ ብዙ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ የተጀመሩትን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ቀጣይ ሥራችን ነው ብለዋል።

የከተማዋን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ መመለስ፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻልና ድህነትን መቀነስ ዘመናዊና ማራኪ ከተማ መገንባት የቀጣይ ዕቅዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ነዋሪዎችን በእኩል ዓይን በማየት ሃብትን በአግባቡ ማስተዳደርና ምዝበራን ማስወገድ ላይ በርትተን እንሰራለን ሲሉም  ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸውላቸዋል።

የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በበኩላቸው ከተማዋ የሁሉም ቤት እንድትሆን የቻሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ያለፉት ሁለት ዓመታት በከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶችና የመሰረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ "አዲሷ ተሿሚም የጀመርነውን እንደሚጨርሱ እርግጠኛ ነኝ" ሲሉም ተናግረዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ አቶ ጃንጥራር አባይን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አድርጎ በመሾም አስቸኳይ ስብሰባውን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም