በክልሉ ለውጡን ለመቀልበስ የሚጥሩ አካላትን ህብረተሰቡ ተከታትሎ ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል - አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

60
ባህርዳር ሓምሌ 5/2010 በክልሉ የተጀመረውን የለውጥ እንቅሰቃሴ ለማስቀልበስ የሚጥሩ አካላትን ህብረተሰቡ በሰከነ መንፈስ ተከታትሎ ለፍርድ ሊያቀርባቸው እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ። ''በክልሉ እየታየ ያለውን የለውጥ አንቅስቃሴ ለማስቀልበስ ነባር የብአዴን አባላትንና ህወሓትን በምክንያትነት መጥቀስ መሰረተ ቢስና ከእውነት የራቀ ነው'' ብለዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ነባር የብአዴን አባላት በጊዜቸው  ለክልሉ ህዝብ መስራት በሚችሉት ልክ ሰርተው አልፈዋል፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለውን ህዝባዊ መሰረት ያለው ለውጥ ለማስቀልበስ በውጫዊ ኃይሎች እያሳበቡ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ጠቀሰው መላው የክልሉ ህዝብ በንቃትና በሰከነ መንፈስ ሊከታተቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ትናንት በደብረማርቆስ ከተማ የተከሰተውን ችግር ጨምሮ እየተፈጠሩ ያሉት የንብረት ማውደም ስራዎች  የበሳል አመለካከት ውጤት ያልሆኑና ራስን በራስ የማጥፋት ድርጊቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተጀመረው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው መረጃዎችን  በስሜታዊነት ሳይሆን ከነባራዊ እውነታ ጋር ማመዛዘን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ለብጥብጥ ምክንያት ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በአንድ ቀን ከሦስት ወረዳዎች በላይ ታይተዋል ሲባል ውሸቱን በእውነታ መቀበል ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሃሰት የሚጠረጠሩት ግለሰቦችም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ አቅሙ እንደሌላቸው ህብረተሰቡ ተገንዝቦ፤ ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት የራሱን ንብረት ከማውደም እንዲቆጠብና የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ''እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የታየውን  የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በበሬ ወለደ ወሬ የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሚሯሯጡ ግለሰቦችን የጸጥታ ኃይሉና በየደረጃው ያለ አመራር ሰላም ወዳዱን ህዝብ በመሳተፍ ተለይተው ለህግ ይቀርባሉ'' ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ። አሁን በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የሰላም መደፍረስ እንቅስቃሴ እንዲረግብና የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ  የምክር ቤት አባላትም የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም