የኤቲኤም ማሽኖች ችግር እስከ ነገ እንደሚፈታ ተጠቆመ

108
አዲስ አበባ ሀምሌ 5/2010 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤቲኤም ማሽን አገልግሎት ማቆምና መቆራረጥ በመግጠሙ ኅብረተሰቡ ከእሁድ ጀምሮ ቅሬታ እያሰማ ይገኛል። ችግሩ የገጠመው የኤቲኤም ማሽኖች ከእሁድ ጀምሮ አዲስ ስርዓት እየተዘረጋላቸው በመሆኑ እንደሆነ ከባንኩ ኃላፊ መረዳት ተችሏል። ችግሩን ለመፍታትም ስርዓቱን በአፋጣኝ በመጨረስ ሁሉም ማሽኖች እስከ ነገ ድረስ ወደ አዲሱ ስርዓት እንዲገቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡ የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ  እንደተናገሩት ፤ ነባሩ የኤቲኤም ስዊች (የደንበኞችን መረጃ በመያዝ የደንበኛን ጥያቄ በመቀበል የሚያስተናግደው ስርዓት) አሁን ካለውን ደንበኛና የገንዘብ ዝውውር አንጻር አዲስ ስርዓት መቀየር አስፈልጓል። አዲሱ ስርዓት ለደንበኞች በጥራትና በፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልፀው ተጨማሪ አገልግሎቶችን ማካተት የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት። አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የባንኩ የኤቲኤም ማሽኖች ከ1ሺህ 700 በላይ እንደሆኑ የገለፁት አቶ በልሁ ከነዚህ ውስጥ ከ800 በላይ የሚሆኑትን ወደ አዲሱ ስርዓት በማስገባት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት የተፈጠረው የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር አሁን እየተፈታ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ''ዛሬና ነገ የቀሩትን ማሽኖች ወደ አዲሱ ስርዓት በማስገባት ሁሉም ማሽኖች አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል'' ብለዋል። ባንኩ አዲሱ ስርዓትን በመዘርጋት ሂደት ለተፈጠረው ችግር ኀብረተሰቡን ይቅርታ እንደሚጠይቅም ነው የገለፁት። ባንኩ ከ4ሚሊዮን በላይ የኤቲኤም ተጠቃሚ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ቁጥራቸው ከ1ሺህ 700 በላይ በሆኑት የኤቲኤም ማሽኖች በቀን ከ400 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር እንደሚያካሄድም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም