በድሬዳዋ ለህዳሴው ግድብ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመሰብሰብ ወደ ስራ ተገባ

95

ድሬዳዋ ነሐሴ 11/2012(ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ወደ ስራ መገባቱን የድሬዳዋ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ  አቶ ገበየሁ ወጋየሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የግድቡ የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌቱ በየደረጃው በሚገኘው የድሬዳዋ ነዋሪዎችና አመራር ውስጥ መነቃቃት  ፈጥሯል፡፡

መነቃቃቱን ተከት በአስተዳደሩ በተያዘው የበጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል  ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ከቦንድ ግዥና ስጦታ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የሚመሩ 13 የሥራ አስፈጻሚና 10 ንኡሳን ኮሚቴዎችና ተዋቅረው ወደ ስራ መግባቱን አመልክተው "ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለመድረስ 85 ተቋማትም የሥራው አካል ሆነዋል "ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ የህዝብ ተሣትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ከድር ጁሃር ግድቡ በሀገሪቱ የተሻለ ዕድገትና ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲመጣ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ለግድብ ግንባታ  ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት 82 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን በማስታወስ በተያዘው የበጀት ዓመት ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ  እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ከአስተዳደሩ ነዋሪዎች መካከል በንግድ ስራ የተሰማሩት  አቶ ካሚል አህመድ በሰጡት አስተያየት ለግድቡ ግንባታ ካለፉት ዓመታት በበለጠ  በቀጣይም  ቦንድ ለመግዛት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የበለጠ ድጋፍ እንድናደርግ አነቃቅቶናል" ያሉት ደግሞ የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት አቶ ደረጃ ኃይሌ ናቸው፡፡

ግድቡ እስኪጠናቀቅ  የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ የለገኦዳ ጉኑንፈታ ቀበሌ የህዝብ ተወካይ ወይዘሮ ኑሪያ ሃሚዶ ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም