የአፍሪካ ቻይና የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር ሊጠናከሩ ይገባል--አምባሳደሮች

78

አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ወጣቶች ቻይናን በሚመለከት የተዛቡ መረጃዎች መደናገር እንደሌለባቸው በቻይና የኢትዮጵያና ሩዋንዳ አምባሳደሮች ተናገሩ።

በቻይና አፍሪካ የንግድ ካውንስል ፈተናዎች፣መፍትሄዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ትናንት ምክክር  ተደርጓል።

አምባሳደሮቹ  በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከቤጂንግ ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንደተናገሩት የአፍሪካ ቻይና ግንኙነት ቀጣይነት ባለው መሰረት ላይ የቆመ ነው።

"ከቻይናና ከሌሎች የኢኮኖሚ አጋሮች ጋር በአጋርነት መስራታችንን እንቀጥላለን። የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልም ሆነ ከኮቪድ-19 ማብቃት በኋላ ኢኮኖሚውን ለመታደግ ዘላቂነት ያለው ጥረታችንን በማስተባበር እንሰራለን።በአፍሪካ ቻይና እንዲሁም በአፍሪካና በኢትዮጵያ መካከል ጠንካራ ትብብርና ህብረት አለ" ብለዋል።

በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለው ትብብር ጥልቅ መሰረት መያዙንና ከማምረቻ ዘርፍ እስከ መሰረተ ልማት ግንባታ የዘለቀው ግንኙነት ወደ ማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ፣ትምህርትና የበይነ መረብ ኢኮኖሚ ንግድ መሸጋገሩን አምባሳደር ተሾመ ተናግረዋል።

አፍሪካ በወረርሽኙ ብትጠቃም አሁንም በመካከለኛና በረዥም ዘመናት አመርቂ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚረዳ ብቃት አንዳላት የተናገሩት የኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌስሊ ማስዶርፕ ናቸው።

''በአፍሪካ ያለው ሕዝብ መካከለኛ የዕድሜ ጣሪያ 19 ሲሆን፤ በአውሮፓ ግን 43 ዓመት ነው።አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ለዚህ ሰብዓዊ ካፒታል የሚያስፈልገውን የልማት ትጥቅ ማቅረብ ነው።ለምሳሌ ቴክኖሎጂን ማቅረብ ለቻይና የሰራውን ተዓምር ለአፍሪካ ይሰራል።" በማለት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የወጣት አፍሪካውያን የኢንተርኔት ተደራሽነት በመጨመሩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ጨምሯል።በዚህም የአፍሪካ ፖለቲከኞች ወጣቶችን የሚያስተምሩ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው ተብሏል።

"ቻይና ባለፉት 40 ዓመታት ራሷን ለዚህ ያበቃችበትን መንገድ ወጣቶቹ መማር አለባቸው።አፍሪካውያንም ይህንን ማድረግ እንችላለን።ወጣቶቹ የመጪዋን አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የአሁኗን አፍሪካ ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ አለባቸው።ወጣቶቻችን በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው በመሆኑ ጊዜያቸውን ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ማሳለፍ አለባቸው" ብለዋል አምባሳደር ተሾመ ።

በቻይና የሩዋንዳ አምባሳደር ጀምስ ኪሞዮ በበኩላቸው ለአፍሪካውያን ወጣቶች ቻይናን አስመልክቶ ''ትክክለኛ መረጃ ''ሊሰጣቸው  ይገባል ባይ ናቸው።

"አንዳንድ ጊዜ ከተሳሳቱ ቦታዎች ቻይናን የተመለከቱ የተሳሳቱ መረጃዎች ይለቀቃሉ።ወጣቶቹም ይህንኑ በማንበብ ሰለባ ይሆናሉ።ይህንን ለመከላከል እኛ ለወጣቶቻችን ትክክለኛ የሆነ መረጃ መስጠት ይጠበቅብናል ። ምክንያቱም ቻይና ከፍ አድርጋ የምትናገረው ስለ ትብብርና  በጋራ ስለምንጓዝበት መፃኢ ጊዜ ነው።ይህ ደግሞ ለወጣቶቹ በጣም ጠቃሚ መረጃ ነው"ብለዋል

የአፍሪካ ቻይና ግንኙነት መፃኢ ጊዜን ለማስተካከል ቁልፉ ያለው በወጣቶቹ እጅ መሆኑን የጉባዔው ታዳሚያን በአንድ ደምጽ መስማማታቸውን የሲ.ጂ.ቲ ኤን ዘገባ ያሳያል።

በተለይ የኢንተርኔትና የዲጂታል ኢኮኖሚ ተደራሽነቱን በሙሉ አቅም ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም