የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ አገራዊ ለውጡንና አንድነቱን በመደገፍ ለመስራት ዝግጁ አይደለም ተባለ

95
አዲስ አበባ  ሃምሌ 5/2010  የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጄንሲ አገራዊ ለውጡንና አንድነቱን በመደገፍ ለመስራት ዝግጁ አይደለም ተባለ። ኤጀንሲው የአምስት ዓመት የስራ አፈጻጸም ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ካቀረበ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት ተቋሙ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል። የህዝብ ፍላጎትና ችግር እንዳይነገር የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ አመራሮች አፈና እንደሚያደርጉ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። በተለይ የምክር ቤቱ ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንደተናገሩት፤ በኤጀንሲው የሙያ ነጻነት ባለመኖሩ ጋዜጠኞች ደመወዝ እየቀነሱ ጭምር ተቋሙን እየለቀቁ ነው። ጋዜጠኞች ደክመው ያመጧቸውን የህዝብ ቅሬታ ዘገባዎች በአመራሮች ተቆራርጠውና ተዛብተው እንደሚቀርቡና ሳይተላለፉ እንደሚቀሩ አባላቱ ገልጸዋል። ''በኤጀንሲው የሚተዳደሩት አዲስ ቴሌቪዥን፣ አዲስ ልሳን ጋዜጣና ኤፍኤም 96.3 ሬዲዮ ለህዝብ ቅርብ የሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን አያስተናግዱም'' ብለዋል አባላቱ። የአመራሮች፣ የሙስና አድሎ ችግሮች በጋዜጠኞች ላይ በሚያደርሱት ጫና ዘገባዎች እንዳይተላለፉ ማድረጉ ሚዲያው ተደማጭና ህዝባዊ ወገንተኝነት እንዳይኖረው ማድረጉን ጠቁመዋል። የምክር ቤቱ ማህበራዊ ቋሚ ኮሚቴ ከሰራተኞና ከአመራሮች ጋር ውይይት አድርጎ እንዳረጋገጠው ኤጀንሲው በአስፈጻሚ አካላት ተጽዕኖ ስር በመውደቅ ነጻነቱን ያጣ ተቋም ሆኗል። የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጄንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መብራቴ ሀይሌ በምክር ቤቱ አባላት 'የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጄንሲ አገራዊ ለውጡንና አንድነቱን በመደገፍ ለመስራት ዝግጁ አይደለም' በሚል የተሰነዘረው አስተያየት ትክክል መሆኑን ገልጸዋል። ሚዲያው ለህዝብ ሆኖ በነጻነት ዘገባዎችን እንዲሰራ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም  ክፍተቶች መስተዋላቸውን ገልጸዋል። የኤጀንሲው ሰራተኞች እስከ 2ሺህ ብር ድረስ ደመወዝ እየቀነሱ ወደሌላ ተቋም እንደሚሄዱም አረጋግጠዋል። ምክትል ስራ አስኪያጁ ችግሩን ለመፍታትና በአገሪቱ የተጀመረውን የመደመር እሳቤ ለማጎልበት በቀጣይ ጊዜ እንደሚሰራም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም