የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል 11 የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሔደ ነው

87

ጎንደር ነሃሴ 10/2012 (ኢዜአ) በሳይንሳዊና ሀገር በቀል እውቀት ተመስርቶ የኮቪድ 19 ስርጭትን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ማህበረሰባዊ ተሳትፎና ክፍተቶች ላይ ያተኮሩ 11 የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ የጎንደር ዩንቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሶስት ወራት ባካሄዳቸው 5 የምርምር ውጤቶች ላይም በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች የኦን ላይን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቪዲዮ ኮንፍረስ አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተካሄዱት ምርምሮች የበሽታውን ስርጭት በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ማህበረሰባዊ ተሳትፎና ክፍተቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡

ስለ በሽታው የማህበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ፣ ርቀትን በመጠበቅና የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምቦሎች የመጠቀም ባህል እንዲሁም እጅን አዘውትሮ የመታጠብና የግል ንጽህና አጠባባቅ በጥናቶቹ ተካተዋል።

በጥናትና ምርምሮቹ የሃይማኖት ተቋማትና የሃይማኖት መሪዎች የበሽታውን ስርጭት በመካላከልና በመቆጣጠር ረገድ ስለሚኖራቸው ሚና፣ ተሳትፎና ውጤታማነት ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ኮቪድ19 በማህበረሰቡ ላይ እያሳደረው ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዲሁም በግለሰቦች የእለት ተእለት ህይወት ውስጥ ሊፈጥር ስለሚችለው ስነ ልቦናዊ ጭንቀትና ውጥረት አሉታዊና አዎንታዊ ግኝቶች ተመላክተዋል።

“ዩኒቨርሲቲው ከሚያካሂዳቸው 11 የጥናትና ምርምር ሥራዎች ውስጥ የመጨረሻ ደረጃ ላይ በደረሱት 5 ምርምሮች ከመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ 48 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ባለፈው ሳምንት በቪዲዮ ኮንፍረስ ግምገማ አካሂዷል” ብለዋል፡፡

“በግምገማው የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት በቀጣይ መረጃዎቹን በማደራጀትና በመተንተን መንግስት የኮቪድ 19ኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ዘመቻ በግብአትነት እንዲጠቀምበት ለማድረግ እየተሠራ ነው”ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዘዳንቱ እንደተናገሩት፤ የምርምር ሥራውን ለማካሄድም ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ በመበጀትና ከ100 በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራንን በማሳተፍ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

የዩንቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎች በተጠናቀቀው በጀት አመት አካሂዷል።

የኮሮና በሽታን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሠሩትን ጨምሮ በበጀት ዓመቱ ለተከናወኑ ለሁሉም የምርምር ሥራዎች ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

በኮሮና በሽታ ሳቢያ ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ማህበረሰባዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑም ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ከ300 በላይ አልጋዎች ያሉት ማእከል በማደራጀት ቫይረሱ የተገኘባቸው 120 የህብረሰብ ክፍሎች የህክምና ክትትልና ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም