ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ገበታ ለሀገር" የተሰኘ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይፋ አደረጉ

110

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 10/2012 ( ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ "ገበታ ለሀገር" የተሰኘና በኢትዮጵያ የተለያዩ ሶስት አካባቢ ዎችን ማልማት የሚያስችል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይፋ አደረጉ።

በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኘው ጎርጎራ፣ በአሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ እና በደቡብ ክልል የግልገል ጊቤ ሃይል ማመንጫ አካባቢ የሚገኘው ኮይሻ ናቸው።

ለሥራው የሚሆኑና ከመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተውጣጣ ኮሚቴም ተዋቅሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ''ከቢሮ እስከ ሀገር'' በሚል መነሻ ከቤተ አዲስ አበባን ውብ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ከተማዋን የመቀየሩ ተግባር አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

አዲስ አበባን ብቻ በመቀየር ያሰብነውን ሀገራዊ ብልጽግና ማምጣት አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን በመገንዘብ ደረጃ በደረጃ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችን እናለማለን ብለዋል።

የ''ገበታ ለሀገር'' ዓላማ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ የቱሪስት መስህቦችና ሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ቦታዎችን ማዘጋጀት መሆኑንም ተናግረዋል።

በአንድ ጊዜ በርካታ ልማት መጀመር እንደማይቻል ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የጠቀሱት።

በቀጣይ የተለያዩ ሀብቶችን በማሰባሰብና ልምዶችን በመጠቀም እንደ 'አክሱም' ባሉ ጥንታዊ ከተሞች ላይም መሰል ልማት ለማድረግ ውጥን እንዳለም አስረድተዋል።

ይህን ለማድረግ ያለመ ጥናት መደረጉን በመጠቆም።

በ''ገበታ ለሀገር'' መርሃ ግብር የግል ባለሀብቶችን ጨምሮ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በማሳተፍ ሶስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ  መታቀዱንም ነው ይፋ አድርገዋል።

ይህን ለማሳካት ደግሞ  ለግል ባለሀብቱ ባለ 10 ሚሊዮን የከበረ ልዩ ራት (VVIP) እና ባለ አምስት ሚሊዮን ልዩ ራት (VIP) እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል።

ባለሀብቶች በተናጠልም ሆነ በጋራ በመሆን በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር  በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ብልጽግና አሻራቸውን እንዲያኖሩም ዶክተር ዓቢይ ጠይቀዋል።

ለዚህም የሚዲያ ተቋማት፣ ምሁራንና ኅብረተሰብ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከመንግሥት መደበኛ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውጭ ራሳቸውን ችለውና የመንግሥት በጀት ሳይመደብላቸው እንደሚከናወኑ  አስታውቀዋል።

የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ሸገርን በማስዋብ  የተገኘው ስኬት ፕሮጀክቶቹን እውን የማድረግ አቅም እንደሚሆን ነው ያነሱት።

ከፕሮጀክቱ የተገኘውን ልምድን በሚገባ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን የሚመለከት ''የኢትዮጵያ ልክ'' በተሰኘ ርዕስ ባለፈው ዓርብ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች አማካይነት ለሕዝብ መቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም